>

ብዙ ፍላጎቶች ቢኖሩም ነገርግን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ትቀጥላለች !!! (ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ)

ብዙ ፍላጎቶች ቢኖሩም ነገርግን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ትቀጥላለች !!!
ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ
 
*  ብሄራዊ ዕርቅን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ ዝርዝር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል
 * ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ብሄራዊ ዕርቅን በተመለከተ በመላው ኢትዮጵያ ህግን የማወቅ፣ መብትና ግዴታን የመለየት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች የተካተቱበት ዝርዝር ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቁ፡፡
* ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው ዕለት በጀርመን ፍራንክፈርት ኮሜርዝ ባንክ አሬና ስታዲየም ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን ላቀረቡት ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
* በሀገሪቱ ካለው የሰላም ሁኔታ ጋር በተያያዘ፣ ስለህግ የበላይነት፣ ስለምርጫ ቦርድ፣ ስለዜጎች መፈናቀል፣ በፌደራልና በክልሎች ስላለው ጉዳይና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
* ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም ጃፓን በአንድ ወቅት በአውሎ ንፋስ በተመታችበት ወቅት መልሰን ለመገንባት ዕድል አገኘን ማለታቸውን አስታውሰው፥ እኛም ሀገራችንን ለመገንባት አሁን ያሉትን ችግሮች እንደዕድል የምናስብ ከሆነ ተሻግረን እናልፋቸዋለን ብለዋል፡፡
* ኢትዮጵያ ከሰባት ወር በፊት እንደሀገር ከፍተኛ መናጥ ውስጥ ወድቃ እንደነበር አስታውሰው፥ ዛሬን ከዚያ ጊዜ ጋር አታመሳስሉት እንዲሁም የነገው ደግሞ እጅግ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
* የህግ የበላይነትን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ የዘረፉ ሌቦች በህግ ፊት ማቅረብ ለኛ ግዴታ ብቻ ሳይሆን መሰል ተግባር እንዳይፈጸም ማስተማሪያም ጭምር ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
* አንድነትን በተመለከተ የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደሩ ኃይሎች በዘመናት መካከል የነበሩ ቢሆንም አንዳቸውም ማደናቀፍ ያለመቻላቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብዙ ፍላጎቶች ቢኖሩም ነገርግን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
* ስለመደመር በተነሳላቸው ጥያቄ በቅርቡ በመጽሐፍ መልኩ በዝርዝር እንደሚያቀርቡ ይፋ አድርገዋል፡፡
* የፌደራልና የክልል መንግስታትን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ፌደራሊዝም የመተዳደሪያ እንጂ የመለያያ መንገድ አይደለም የተከሰቱ ችግሮችም የለውጥ ጊዜ መንገራገጭ አድርገን ብንወስዳቸው ይሻላል ብለዋል፡፡
* ክልል ብቻ ክፍለሀገር ብቻ ይሁን የሚሉ አስተሳሰቦች በመካረር ሳይሆን በመመካከር ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው ያሉ ሲሆን ዛሬ መመለስ የሚቻለውን ምላሽ እየሰጠን ለነገ የሚሆነውን ሰክነን እየመለስን እንሄዳለን ብለዋል፡፡
* ከትጥቅ መፍታት ያለመፍታት ጋር በተያያዘ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ መሳሪያ ይዞ ወደ ሀገር ቤት አልገባም ብለዋል፡፡
* ነገርግን አሁን ያለው መሳሪያ በተለያየ መልኩ በህገወጥ መልኩ የገቡ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኦነግ አመራሮች ጋርም ችግሩን ለመፍታት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
* ምርጫ ቦርድን በተመለከተም ማናችሁም በማትገምቱት መልኩ እየተደራጀ ነው ብለዋል፡፡
* ከተለያዩ ሀገራት ጋር ተደርገዋል ስለተባሉ ስምምነቶች የተነሱላቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚደብቁት አንዳችም ነገር ያለመኖሩን አንስተው ከግብጽ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር አዲስ የተፈራረሙት ስምምነት ያለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
* በኢትዮጵያ ከ60ዎቹ ጀምሮ ጦርነቱን የሚቆሰቁሱት ኃይሎች ሳይሆኑ የሚሞቱት ተራው የገበሬ ልጅ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
* ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከዚህ ቀደም ከነበረው ከ334 በመቶ በላይ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
* የዓለም ባንክም ትናንት ይፋ ካደረገው የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እና ብድር በተጨማሪ ከሦስት ወራት በኋላም ሌላ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
* ቋንቋን በተመለከተ ጣልያን በ1930ዎቹ ያስጠኑትን ጥናት በማስታወስ ሊወሩን ቢመጡም ዛሬ እኛ ከያዝነው የተሻለ ሐሳብ አቅርበው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

* በመጨረሻም ኦሮምኛ የፌደራል መንገስቱ ቋንቋ እንዲሆን አማራው መታገል አለበት አማርኛ ይበልጥ እንዲሻሻል አሮሞው መሞገት ይገባዋል ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡ ምንጭ:- አብርሃምፈቀደ

Filed in: Amharic