>

የወሎ ህዝብ ይቅርታና የአጤ ዮሐንስ ጭፍጨፋ (ኤርሚያስ ቶኩማ)

የወሎ ህዝብ ይቅርታና የአጤ ዮሐንስ ጭፍጨፋ
ኤርሚያስ ቶኩማ
የወሎ መዲና የሆነችው ውቧ ደሴ ከተማ የተቆረቆረችው በንጉስ ሚካኤል (መሀመድ አሊ ዘወሎ) ሳይሆን ቀደም ብላም ስመገናና ከተማ እንደነበረች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ በ697 ዓመተ ምህረት የአርመንያ ዜጋ የሆኑ ክርስቲያኖች በወቅቱ አረቦች ያደርሱባቸውን የነበረውን ወረራ ለመከላከል ወደኢትዮጵያ እንደተሰደዱ እና ወይራ አምባ የአሁኗ ደሴ ላይ እንደሰፈሩ በአንድ ወቅት የአርመን ኤምባሲ ያሳተመው ፅሁፍ ያስረዳል ይህንን ፅሁፍ ብሔራዊ ቤተመዛግብት ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡ እነዚሁ የአርመን ዜጎች ከደሴ በተጨማሪ ወጣ ብላ ከምትገኘው ሀይቅ ከተማ ላይ በሚገኘው ሐይቅ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በርካታ የስነፅሁፍ ስራዎች እንዳሏቸውና ስለወይራ አምባ በፅሁፎቻቸው እንደገለፁ ያስረዳል፡፡ በመካከለኛው ዘመን ላይ የወሎ ቄሶችና የሸዋ ቄሶች ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅት የሐይቅ እስጢፋኖስ ዲያቆን የነበረው ተስፋእየሱስ ኋላም ይኩኖአምላክ ተብሎ የገዛው ከሐይቅ እስጢፋኖስ ውጭ መኖሪያው ወይራምባ (ደሴ) እንደነበረ ዶክተር ሀብተማሪያም አሰፋ የኢትዮጵያ የታሪክ ጥያቄዎችና መልሶች ብለው ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ ይጠቅሳሉ፡፡ ደሴ ወይራምባ በግራኝ አህመድም ዘመን ለግራኝ አህመድ ተከታዮች መቀመጫ የነበረች ታላቅ ከተማ ነች፡፡ ደሴ ወይራምባ የሚለውን ስም ትታ ደሴ በሚል መጠራት የጀመረችውም በልጅ ኢያሱ አባት በንጉስ ሚካኤል ሳይሆን በአፄ ዮሐንስ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስ ጎጃምና ወሎን ለመግዛት በተንቀሳቀሰበት ወቅት የጎጃም ህዝብን በተለይም የኦርቶዶክስ ቅባት ተከታዮችን ከወሎ ደግሞ ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ እልቂት መፈፀማቸው አይረሳም፤ አፄ ዮሐንስ የወሎ ሙስሎሞች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ካካሄዱ በኋላ ወይራምባን ተቆጣጥረው ስሟን ወደደሴነት እንደቀየሩት ይነገራል ደሴም ወይራምባ የሚለውን መጠሪያዋን ትታ እስካሁንም ድረስ ደሴ እንደተባለች አለች፡፡ ወሎን በስራ ምክንያት ከወልደያ እስከ ወረኢሉ ከዋድላ ደላንታ እስከ ራያ ቆቦ፤ ከላስታ እስከ የጁ ከቦረና እስከአምባሰል ቁንጅናና ኢትዮጵያዊነትን የመጎብኘት እድል አግኝቻለው፡፡ ወሎ ላይ እንግዳ የሚባል ነገር የለም፤ የየትኛውም እምነት ተከታይ ሁን ከየትኛውም ጎሳ ና ለእነርሱ ሰው መሆንህ ብቻ ነው የሚታያቸው፤ ኢትዮጵያዊነቱን ያልተቀማ ህዝብ በብዛት የሚገኘው ወሎ ነው፡፡ ለዚህም ነው ስለወሎ ስሙን የማላውቀው ገጣሚ እንዲህ ሲል የተቀኘው
.
የዘር አምባጓሮ የኃይማኖት ንትርክ ወሎ መች ለመደ: 
ሥሙ ምስክር ነው ፋጤ ገብረማርያም ሙህዬ ከበደ::
ወሎ በደርግና ከዚያም ቀደም ብሎ አሥራ ሁለት አውራጃዎች (ዋግ – ላስታ – ራያ  – የጁ – አምባሰል – ዴሴ ዙሪያ – አውሳ – ቃሉ – ቦረና – ወረኢሉ – ዋድላ ደላንታ እና ወረሂመኖ ) ነበሯት፡፡ ዛሬ ወሎ የሚባለው ክፍለሀገር ድንበሩ በትግራይ ወንበዴዎች ለትግራይና ለኤርትራ ተቆርሶ ተሠጥቶ ትንሽ ግዛት ቢሆንም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የሚኖሩባት የትልቋ ኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆን የምትችል ኢትዮጵያዊነት በብዛት የሚዛቅባት ድንቅ ግዛት ነች፡፡
.
ፈጣሪ ታቃለህ ሣቅና ጉዳቴን
ጀሊሉ ታቃለህ መሳቅ መከፋቴን
ራሴን መቻያ አጥናልኝ አንገቴን፡፡
.
ይህ የወሎ ሼህ ሁሤን ጅብሪል አጤ ዮሐንስ በወሎ ህዝብ ላይ ለፈፀሙት ጭፍጨፋ የተነበዩት ትንቢት ነው፤ አጤ ዮሐንስ የወሎ ሙስሊሞች ላይ የፈፀሙት ጭፍጨፋ ብዙም ትኩረት አላገኘም እንጂ ከፍተኛ የጥፋት ዘመን ነበረ፡፡ እንዳውም ሼህ ሁሴን እንዲህ ሲሉ በአጤ ዮሐንስ አሽከሮች የደረሰውን በደል ይገልፃሉ፡፡
.
ደጋውም ቁንጫ ቆላውም ረምጫ
የሠይድ አሽከሮች አጣን መቀመጫ፡፡ 
.
በወሎ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውም በደል ከባድ ነበር ሐይማኖታቸውን በግድ እንዲቀይሩም ከፍተኛ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሼህ ሁሴን ጅብሪል በትንቢታቸው ሲገልፁ
.
ደረሱብን እንጂ መቼ ደረሰንባቸው
ቁረቡ ይሉናል የነፍስ አባታቸው………
.
 በማለት ቀድመው ተንብየው የወሎ ህዝብን መከራ ተናግረዋል፡፡ በአጤ ዮሐንስ ጦር ይህ ሁሉ በደል የደረሰበት የወሎ ህዝብ ግን አንድም ቀን አጤ ዮሐንስና አሽከሮቹ በድለውኛል ብሎ ከኢትዮጵያዊነቱ ገሸሽ ያለበት ቀን የለም እንዳውም አጤ ዮሐንሰ የኢትዮጵያ ንጉስ ስለሆኑ ከፍተኛ ክብር ይሠጣቸው ነበረ፤ አጤ ዮሐንስ በመተማ ከደርቡሾች ጋር ሲዋጉ ድል እንዳይሆኑ ምክር ቢጤም ሰጥተው ነበረ እንዲህ በማለት
የዮሐንስ በቅሎ ብረኪ ብረኪ
አሏህ አምጥቶብሽ የደርቡሽ ማራኪ
መተማ ላይ ወርደሽ ሳትፍረከረኪ………….
 እንዳውም አጤ ዮሐንስ የሚፈፀመው ሁሉ ለሀገር ሲል እንደሆነ ሼህ ሁሴን በትንቢታዊ ግጥማቸው ይገልፃሉ
የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮዋንስ
………. በማለት ለሀገር ብሎ አጤ ዮሐንስ አንገቱን እንደሰጠ ከገለፁ በኋላ አጤ ዮሐንሰ ኢትዮጵያን ገዝተው ያለቀባሪ መተማ ላይ በመቅረታቸው ሼህ ሁሴን በቁጭት እንዲህ ብለዋል
ጣይ መውጫ ጣይ መግቢያ የገዛው ንጉስ
ታይቀበር ቀረ አጤ ዮሐንስ
…… ብለው ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡ እነዛ የኢትዮጵያችን ልጆች የወሎ ፍሬዎች አጤ ዮሐንስ ባለማወቅ ምንም እንኳን ቢበድሏቸውም በኢትዮጵያ ታሪክ ቂም አይዙም ከኢትዮጵያዊነት ለማፈንገጥ ሲሞክሩም አይተን አናውቅም፡፡ ሼህ ሁሴን እንደሚሉት የወሎ ህዝብ ቄጤማውን በትኖ፣ አርቲ አሽቲውን ይዞ፤ ረኮቦቱን ደርድሮ እጣኑን አጫጭሶ ቡና አፍልቶ ከቂም በቀል ይልቅ በመልካም ልሳናቸው እንዲህ የሚሉ ህዝቦች ናቸው
አቦል ጀባ
ምቀኛህ አንጋዳ ይግባ
ርዝቅና ጤና ተቤትህ ይግባ
የሹም መውደድን ይስጥህ 
ከሙጢ ስጢ ከስውር መጋኛ ይሰውርህ 
……ሲል መርቆ የሚሸኝ ህዝብ ነው፡፡ ሁላችንም ከወሎ ወገኖቻችን ትምህርት ወስደን ባለፈ ነገር እርስ በእርስ ከመነታረክ በቋንቋ እና በሐይማኖት ከመከፋፈል ወጥተን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ብንነሳ ዛሬ መገኛችን እዚህ አልነበረም፡፡ የወሎ ህዝብ ለአጤ ዮሐንስ የሰጠው ይቅርታ ለሁላችንም ያስፈልጋል ሁላችንም ሳንነጋገር ይቅር ልንባባልና በአንድነት ልንቆም ይገባል፡፡ የመጠፋፋት ዘመን ሳይሆን የይቅርታ ዘመን ያስፈልገናል፡:
Filed in: Amharic