>

በኦነግ ጉዳይ ለአብይ መንግስት የቀረበ አጣዳፊ ጥያቄ !!!! (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

በኦነግ ጉዳይ ለአብይ መንግስት የቀረበ አጣዳፊ ጥያቄ !!!!
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
የአብይ መንግስት ኦነግ ወደ ሀገርቤት ከመግባቱ በፊት ያደረጉት ስምምነት አንድ ትልቅ ክፍተት ይታይበታል። አንደኛ ስምምነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ፣ ውይይቱን ህዝብ እንዲሰማው ሆኖ፣ የስምምነቱ ነጥቦች ለህዝብ ይፋ ተደርጎ፣ በሰከነ እና በበሰለ መንገድ ነበር መካሄድ የነበረበት። ይህ አለመደረጉ አሁን ለተፈጠረው ግርታ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ለማንኛውም አቶ ዳውድ ለዋልታ በሰጡት ቃለምልልስ የስምምነታቸውን ሶስት ነጥቦች ሲጠቅሱ:
1: በኦነግና በመንግስት መካከል የነበረው ጦርነት ማብቃቱ፣
2: ኦነግ ያለምንም እቀባና እንቅፋት በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን፣ የኦነግ አመራር በተለያየ ቦታ ያሉት ወደ ሀገርቤት እንዲገቡ
3: በሰራዊት በኩል (አንዳንድ የተነጋገርናቸው ጉዳዮች አሉ በሚል ጠቅለል ባለ ሁኔታ ገልፀው) አፈፃፀሙን በተመለከተ አንድ ኮሚቴ አዋቅረን ለወደፊቱ እንዴት እንደምነሄድበት እንነጋገራለን በሚል መስማማታቸውን
4: በቀጣይ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ኦነግም መንግስትም የህግ የበላይነትን ተቀብለው አብረው የመስራት
እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርገናል አሉ።
እዚህ ላይ ቆም ብለን 3 ቁጥር ስምምነትን ስንመረምር የአብይ መንግስት ከፍተኛ ስህተት የሰራ ይመስለኛል። የኦነግ የሰራዊት ጉዳይ ላይ ቁርጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረባቸው። ከወያኔ ጋ ከ26 አመት በፊት ግጭት የተጀመረው በሰራዊት ጉዳይ ነበር። መንግስት የሰራዊቱን ጉዳይ እልባት ሳይሰጥ በይደር በማቆየቱ፣ ሰራዊቱ ትጥቅ ፈትቶ መግባት እንዳለበት በግልፅ ቋንቋ አለማስቀመጡ፣ ይህን ስምምነት በጣሱ ጊዜ መንግስት ምን እርምጃ እንደሚወሰድ፣ በኦነግ በኩል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን የሚጫወትበት አጠቃላይ የህግ ማዕቅፍ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት ምን አይነት የጋራ መድረክ ተፈጥሮ እንደሚፈታ የተብራራ እና ግልፅ የሆነ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በተጣደፈ መንገድ ከሽብርተኝነት መዝገብ መውጣቱ (ለሌሎችም ቢሆን እንዲህ ዘርዘር ያለ ስምምነት ያለ አይመስለኝም)
ከፍተኛ ስህተት ነበር።
ለዚህ ነው የዋልታው ጋዜጠኛ ትጥቅ ፈታችሁ ነው የገባችሁት ብሎ ሲጠይቅ ጃል ዳውድ በምፀት ፈገግታ ሸብቦ ሳቅ እያለ:
“ትጥቅ መፍታት የሚባል ነገር በጣም ሴንሴቲቭ ጥያቄ ነው። ትጥቅ ፈታ አይባልም፣ ትጥቅ ፈቱ መባልም አንፈልግም። ምክንያቱም ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ነገር አንዱ ትጥቅ የሚፈታ ሌላው ትጥቅ የሚያስፈታ ይመስላል፣ አይደለም! እንደሱ አይደለም የመጣነው። ባጠቃላይ ሀገሪቱ ሰላሟ እንድትጠበቅ ኦነግ ያለው ሚና፣ በዚህ ውስጥ እንዴት እንደሚሳተፍ፣ መንግስትም ደግሞ ለወደፊት ከሁሉ የበለጠ ቮይለንስ፣ መሳሪያውን፣ የሰው ሀይሉን፣ ሞኖፖሊው በከፍተኛ ደረጃ በመንግስት እጅ በመሆኑ መንግስት እነዚህን ተጠቅሞ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ዜጎችም ላይ ይሁን የፖለቲካ ቡድኖች ላይ ምንም አይነት እርምጃ እንዳይወስድ፣ ይሄንን አብረን ሰላማዊ ሂደት እንዲሆን አብሮ የመስራት፣ በዚህ ውስጥ የኛ ሚና ምን እንደሚሆን በዚህ ነው የተስማማነው እንጂ ትጥቅ አንዱ አስፈቺ አንዱ ፈቺ የሚለውን አላነሳንም ጥሩም አልነበረም ይህ ቃል።”
ቃልበቃል ነው የወሰድኩት
ከዚህ የምንረዳው አብይ ከፍተኛ ስህተት ሰርቷል አልያም ኦነግ ከስምምነት ወጥቷል ለማለት የስምምነቱ ሙሉ ይዘት መንግስትን አስገድዶ እንዲያወጣው እና የህግ ሙህራን በአለማቀፍ ደረጃ በታወቀው የትርጉም መርህ መሰረት የስምምነቱን ይዘት አብጠርጥረን በመፈተሽ ችግሩ የትጋ እንዳለ ነቅሶ ማውጣት ይቻላል።
ከሌሎች ጋርም የተደረገው ስምምነት ይፋ መሆን አለበት።
ወደ የቀረበው አስቾካይ ጥያቄ ስንመጣ:—
በህገመንግስታችን አንቀፅ 12 መንግስታዊ አሰራር በግልፀኝነት ይካሄዳል በሚለው መሰረት እኔ #ሙክታሮቪች በአስቸኳይ መንግሰት ስምምነቶችን እንዲያሳውቀኝ (እንደ አንድዜጋ) እጠይቃለሁ።
Filed in: Amharic