>
5:13 pm - Tuesday April 18, 0682

በተለያዩ አከባቢዎች ለሚቀሰቀሱ ግጭቶች ህወሓቶች እና አክቲቪስቶች ተጠያቂ ናቸው! (ስዩም ተሾመ)

በእርግጥ የአፓርታይድ ስርዓት በህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ተገርስሶ ወድቋል። ነገር ግን የአፓርታይድ ስርዓት ከወደቀ በኋላም ስሩ ሙሉ በሙሉ እስኪነቀል የሚያደርሰው ጉዳት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከሚያደርሰው በላይ የከፋ ነው። ከዚህ አንፃር በደቡብ አፍሪካ የነበረው የጸረ-አፓርታይድ ትግል የመጨረሻ አመታት ዛሬ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በግልፅ ለመረዳት ያግዛል። በመጀመሪያ ግን በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ስለነበረው የፀረ-አፓርታይድ ትግል ስልትና አካሄድ ተመሳሳይነት እንመልከት።

የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ በዘር ሀረግና በቆዳ ቀለም ነጮች፥ ጥቁሮች፥ ሕንዶችና ቅይጦች (colored) በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ሆኖም ግን፣ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ ሲካሄድ የነበረው በዋናነት በጥቁሮችና በነጮች መካከል ነው። የአፓርታይድ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮችን የፖለቲካ የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ 70% የሚሆኑትን ጥቁሮች በጎሳና ብሔር መከፋፈል አለበት።

በዚህ መሰረት፣ የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብን በጎሳና ብሔር ለአስር ክልሎች ከፋፍሏቸዋል። እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን አለው። ነገር ግን፣ የአንዱ ክልል ነዋሪ በሌላኛው ክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሕግ የተከለከለ ነበር። ይህ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አጀንዳና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው የታለመ ነው።

የአፓርታይድ ስርዓት የአነስተኛ ብሔርን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ሕዝቦች በጎሳና ብሔር በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው። አሁን በኢትዮጲያ ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ከነበረው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። የህወሓት/ትግራይ የበላይነትን ለማስቀጠል በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በመለያየት ላይ የተመሰረተ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው የመብትና ነፃነት ጥያቄያቸውን በጋራ መጠየቅ ሲጀምሩ የአፓርታይድ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሁን በሀገራችን ለሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት መንስዔን፣ እንዲሁም በሁለቱ ስርዓቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልፅ ይጠቁማል።

እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ አመፅና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ልክ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንደታየው እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት እርምጃ አንድና ተመሳሳይ ነበር። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለማቋረጥ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት፣ የሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እያመራ ሄደ።ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መሪ የነበሩት “Pieter Willem Botha” ልክ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ቃል ገቡ።

ይሁን እንጂ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የነጮች አፓርታይድ እና በኢትዮጵያ የነበረው የህወሓት አፓርታይድ ስር ነቀል ተሃድሶ ማምጣት ተሳናቸው። ከዚያ ይልቅ፣ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። ሆኖም ግን፣ የሁለቱም መንግስታት እርምጃ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞን ይበልጥ እንዲባባስ አደረገው። በዚህ ምክንያት፣ እ.አ.አ. በ1986 በደቡብ አፍሪካ፣ እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ።

በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሕቡዕ ሦስተኛው ኃይል (The third Force) የተባለ ፀረ-አብዮታዊ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ከክልል ሚሊሺያዎችና ልዩ ፖሊስ ኃይል የተወጣጣው ቡድን እንደ ዝምባብዌና ሞዛምቢክ ባሉ ጎረቤት ሀገራት የነበረውን የአማፂያን እንቅስቃሴ እንዲያውኩ የተቋቋሙ ነበሩ።

የአሰቸኳይ ግዜው ከታወጀ በኋላ ግን በደቡብ አፍሪካ ጦር ወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ተሰጥቷቸው የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን በማጨናገፍ ተግባር እንዲሰማሩ ተደረገ**። የአፓርታይድ ስርዓት በተለይ በደቡብ አፍሪካ “KwaZulu Natal” በሚባለው ክልል የታየውና ዛሬ በሶማሊ ክልል እየታየ ያለው ፍፁም ተመሳሳይ ነው።
በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ዛሬ በአንዳንድ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልሎች እየታየ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል የአርስ-በእርስ ግጭት በመፍጠር የነጮች የበላይነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደየት እየሄደች እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በደቡብ አፍሪካ በተለይ እ.አ.አ. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የጥቁር ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሕቡዕ የተሰራው ስራ እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ፍሬ አፈራ። በእርግጥ ከመርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅም። በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ ብቻ በተነሳ ሁከትና ብጥብጥ 14,000 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። እ.አ.አ. ከ1948 ዓ.ም የአፓርታይድ ስርዓትን ለመጣል በተደረገው ትግል ከተገደሉት ሰዎች ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ብቻ የተገደሉት ይበልጣል።

በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከስልጣን ከተወገደ እና የሽግግር መንግስት ከተቋቋመ በኋላ ባሉት አራት አመታት ብቻ 14ሺህ ጥቁሮች ለምን ተገደሉ? በመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች የተገደሉት በአንድ ወገን ሳይሆን በተለያዩ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል በተፈጠረ ግጭትና ብጥብጥ ምክንያት ነው። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች አፓርታይድ ከወደቀ በኋላ እርስ-በእርስ የተገዳደሉበት ምክንያት ምንድነው? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ በቀድሞ የአፓርታይዱ መሪ በነበሩት “F. W. de Klerk” እና በኔልሰን ማንዴላ መካከል የነበረውን ፍጥጫና እሰጣ-ገባ ማስታወስ ተገቢ ነው።

ኔልሰን ማንዴላ በጥቁሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭትና ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት የአፓርታይድ የቀድሞ ጄኔራሎች እና የደህንነት ሰዎች ናቸው በማለት ይወቅሳሉ። በሌላ በኩል “F. W. de Klerk” ደግሞ በኔልሰን ማንዴላ የሚመራውን ¨ANC” ጨምሮ ሌሎች የፀረ-አፓርታይድ ቡድኖችና መሪዎች ለብዙ አመታት የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ለመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና ለህግ ተገዢ እንዳይሆን በማድረግ የፈጠሩት ስርዓት-አልበኝነት ለእርስ-በእርስ ግጭትና ብጥብጥ ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ የፀረ-አፓርታይድን ታጋዮች ተጠያቂ ያደርጋሉ። በጉዳዩ ዙሪያ የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች የሁለቱም ወገኖች የተነሱት ምክንያቶች የራሳቸው እውነት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።

በተመሳሳይ ባለፉት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከታዩት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በስተጀርባ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ የቀድሞ የህወሓት ጄኔራሎች እና የደህንነት ሰዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ለውጡን ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከህወሓት ጋር በተደረገው ትግል አብዛኞቻችን ወጣቶች ለሀገሪቱ ህግና የጸጥታ መዋቅር ተገዢ እንዳይሆኑ በመቀስቀስ አሁን ላይ ለሚታየው ስርዓት አልበኝነትና ግጭት የራሳችንን ሚና ተጫውተናል። ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ የቀድሞ የህወሓት ጄኔራሎች እና የደህንነት ኃላፊዎችን እንቅስቃሴና እኩይ ዓላማ ቀድሞ የማጨናገፍ ስራ መሰራት አለበት። በተመሳሳይ የሀገራችን ወጣቶች ለህግ ተገዢ እንዲሆኑና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር እንዲሰሩ ማድረግ አለብን። በአጠቃላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ሁላችንም ተጠያቂ ነን። በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት በተቻለ መጠን ሁላችንም መረባረብ አለብን።

ማጣቀሻዎች

  • The Historical Significance of South Africa’s Third Force STOR Stephen Ellis Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299.
  • Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299)by Seyoum Teshome
Filed in: Amharic