>
5:14 pm - Sunday April 20, 4628

ኦሮማራ የኢትዮጵያ እትብት ነው!!!  

ኦሮማራ የኢትዮጵያ እትብት ነው!!!
 
ስዩም ተሾመ
አንዳንዶች “ኦሮማራ” ሲባል የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ለማስከበር የተመሰረተ ጥምረት ወይም ትብብር ይመስላቸዋል። የተወሰኑት ደግሞ የህወሓትን የሰልጣን የበላይነት በኦሮሞ ለመተካት ይመስላቸዋል። አብዛኞች ግን “ኦሮማራ” ሲባል ከኦሮሞና አማራ የስልጣን ጥያቄ ባለፈ ሌሎች የሀገሪቱን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያገለለ መስሎ ይሰማቸዋል። ከዚህ በመነሳት ብዙዎች ስለ ኦሮማራ ጥምረት አሉታዊ የሆነ አመለካከት አላቸው። ይህ ግን ስለ ጉዳዩ ካላቸው የተዛባና ውስን የሆነ ግንዛቤ የመነጨ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ “ኦሮማራ” የሚለው ትላንት የተመሰረተ የኦሮሞና አማራ ህዝቦች ጥምረት ብቻ አይደለም።
በመሰረቱ የኦሮማራ ጥምረት የተመሰረተው ዛሬ ሳይሆን ከ300 መቶ አመት በፊት ነው። የኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበው ራሳቸውን ከቅኝ-ገዢዎች ወረራ መታደግ የቻሉት በኦሮማራ ጥምረት አሰባሳቢነት ነው። በእርግጥ የአሁኗ ኢትዮጵያ ከመመስረቷ በፊት የኦሮማራ ጥምረት ነበረ። የኦሮማራ ጥምረት ባይኖር ኖሮ ግን የአሁኗ ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር።
የኦሮማራ ጥምረት የሁለት ህዝቦች ጥምረት ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከቅኝ-ገዢዎች ወረራና ባርነት የታደገ ጥምረት ነው። ኦሮማራ ማለት የአሁኗ ኢትዮጵያ የተመሰረተችበት እትብት ነው፤ የኢትዮጵያ ነፃነት፥ የአደዋ ድል ሚስጥር ነው። ኦሮማራ የሁለት ህዝቦች ጥምረት አይደለም፣ የኢትዮጵያ እትብት ነው!!! (ስለ ኦሮማራ ጥምረት ዓላማና ግብ ከወዳጄ በፍቃዱ ኃይሉ ጋር ያደረኩትን ቃለ-ምልልስ እንድትመለከቱ ተጋብዛችኋል!)
Filed in: Amharic