>

ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ታጣ!!! (መሳይ መኮንን)

ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ታጣ!!!
መሳይ መኮንን
 
የጌታቸው ረዳ አመክንዮ ውሃ አይቋጥርም።
ኢህአዴግ የአማራ ክልልን ከፈጠረ ወልቃይት በአማራ ክልል ውስጥ ይሁን ማለት ህገመንግስቱን ማፍረስ ማለት ነው ይልሃል። በእርግጥ አሁን በብሄር የተዋቀሩት ክልሎችን የፈጠረው ኢህአዴግ በመሆኑ ጌታቸውን አንሞግተውም። ክልል የተሰኘው የአፓርታይድ ጽንሰሀሳብን ወደመሬት የቀየረውን መዋቅራችሁን የእኔ ነው ብሎ የሚነጥቃችሁ ሌላ ሀይል አይኖርምና በዚህ እንዳይሰጉ። የባለቤትነት መብታችሁ እስከወዲያኛው ተከብሮላችኋል። 
 
ኢትዮጵያ ላይ የተተከለው ክልላዊ መዋቅር አቶ ጌታቸው እንዳንቆለጳጰሱትና ደረታቸውን ነፍተው፡ እጃቸውን እያወራጩ እንደተናገሩለት የሚያስመካ አልነበረም። በእሳቸው ወይም በህውሀት መዝገበ ቃላት ውስጥ በእርግጥ ልክ ይሆናል። ክልል ማለት ታቅዶና ተሰልቶ፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው፡ ስትራቴጂክ አዋጭነታቸው የተመረጡ አከባቢዎችን አግብስብሶ በትግራይ ክልል ስር እንዲሆኑ ማድረግ፡ ሌሎችንም የህውሀትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት በሚያረጋግጥ፡ ኢትዮጵያዊ ቀለምን በሚያጠፋ፡ የዘርና የጎሳ አደረጃጀት ላይ የተቸነከረ ክልላዊ ድንበርና ወሰን በማበጀት ማዋቀር ማለት ነው። ይህ በህወሀት ቁመና ልክ የተሰፋውን ክልላዊ አወቃቀር ህጋዊና ህገመንግስታዊ ነው የሚለው መከራከሪያ ህወሀት መንደር ሊያሳምን ይችል ይሆናል። 
 
የወልቃይቶችም ሆኑ ራያዎች መሰረታዊ ጥያቄ የማንነት ነው። ጥያቄው በዚህኛው ክልል እንጠቃለል በሚል ዝንጥል ምክንያት ተጀቡኖ መገልጽ የለበትም። በየትም ክልል ይሁን በየት በቅድሚያ የማንነት ጥያቄ ይመለስ ነው። እስቲ በቅድሚያ ወልቃይትም ሆነ ራያ ትግራይ ውስጥ ይቆዩና ማንነታቸው ይመለስ። የወልቃይትን ማንነት መመለስ ህገመንግስቱን የሚያፈርስ ከሆነ ለምን እንክትክቱ አይወጣም?! ደግሞ የህወሀት ፕሮግራም ለሆነ ህገመንግስት።
 
ወልቃይቶች ”ስነልቦናችን የአማራ፡ ቋንቋችን አማርኛ፡ ለቅሶ ዘፈናችን አማርኛ ነው፡ በግድ ትግሬ ሁኑ እንዴት እንባላለን” ነው መሰረታዊ ጥያቄአቸው። ህወሀቶች ወኔ ካላቸውለወልቃይቶች በቅድሚያ እዚያው ትግራይ ክልል ውስጥ እያሉ ማንነታቸውን ያክብሩላቸው። ከዚያ ይልቅ ግን ቅዳሴ ሳይቀር በትግርኛ አድርጉት የሚለው ከዘር ማጽዳት መገልጫዎች አንደኛውን እየፈጸሙ ናቸው። ትግርኛ የማይናገረውን የራያ ተወላጅ ትግርኛ እንዴት እስከአሁን አለመዳችሁም የሚለው የህወሀት የቅኝ አገዛዝ መሰል ፖሊሲ በቅድሚያ ይወገድና ሰለቀጣዩ መነጋገር የሚቻል ቢሆን አንድ ነገር ነው::
 
የጌታቸው ” ክልል አደርገን የፈጠርናችሁ እኛ ነን። በከለልናችሁ ረግታችሁ ኑሩ፡ አርፋችሁ ተቀመጡ” ዓይነት መለኮታዊ ስልጣን የተላበሰ ዲስኩር ዓላማው የማንነት ጥያቄን በአንድ ክልል ውስጥ የመጠቃለል ያለመጠቃለል ጉዳይ አድርጎ ለማድበስበስ የሚደረግ ተራ የስነልቦና ጨዋታ ይመስላል። በአንድ መድረክ ላይ የህወሀት ከፍተኛ ካድሬ የተናገሩት የህወሀትን ፍላጎት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ”በትግራይ ክልል ውስጥ መኖር ካልፈለጋችሁ መሬቱን ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ” ነበር ያሏቸው ወልቃይቶችን። ህወሀት መሬቱን እንጂ ሰዉን አልፈለገም። የራያም ተመሳሳይ ነው። 
 
ወደ አፋር ዓይናቸውን ያማተሩትና ማዕድንኑና የጨው ምርቱን ለመቆጣጠር እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩት ህወሀቶች ዞን ሁለት የተሰኘውን የአፋር ክልል አከባቢ ወደትግራይ ለመጠቅለል እያሴሩ እንደሆነ አውቀናል። ክልል የሚለውን የሰው ልጅን እንደእንስሳ በአንድ አከባቢያዊ ወሰን የሚገድብ መዋቅር የተከሉት ለራሳቸው በሚጠቅምና በዘላቂነት የበላይነታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ መሆኑ እሙን ነው። ለ100 ዓመት አልመው ሩቡን እንደተሻገሩ ተቀጨባቸው እንጂ።
 
እናም አቶ ጌታቸው ረዳ የፈጠራችሁት ክልል የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎታል። ክልል ብላችሁ ያጠራችሁትን ከመሞታችሁ በፊት አፍርሱት። እንደተከላችሁት ንቀሉት። ቢያንስ በዚህ ውለታ መዋልም አንድ ነገር ነው። ማፍረሱም በእናንተው ያምራልና። የነጠቃችሁትን ማንነት ለሚጠይቁት መልሱላቸው። ከዚያ ውጪ ጨዋታው አብቅቷል። ወደ ኋላ የሚቀለበስ የህዝብ ጥያቄ ከእንግዲህ አይኖርም። ከቤተመንግስት ተገፍትራችሁ፡ በመቀሌ ተገድባችሁም ”መለኮታዊ” ስልጣን የጨበጣችሁ ያህል መንጠራራት ከፌንጣ ቁጣ አያልፍም። ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ታጣ እንደተባለው።
Filed in: Amharic