>
5:13 pm - Friday April 18, 0758

ያልተበቀልናቸው!!! እውነተኛ ታሪክ (እንዳለጌታ ከበደ)

ያልተበቀልናቸው!!! እውነተኛ ታሪክ
እንዳለጌታ ከበደ
ቃልኪዳንን ያወቅኳት በጓደኛዬ በማኅደረ ታሪኩ አማካይነት ነው፡፡ ስልክ ቁጥሬን ከእሱ ከወሰደች፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ከደወለችልኝ በኋላ፣ በአካል ለመገናኘት በቃን፡፡
ቃል ኪዳን የኪነጥበብ ሰው መሆን እየፈለገች፣ መድረስ የምትፈልግበት ቦታ እንዳትደርስ ብዙ እንቅፋት በመንገዷ ተጋርዷል፡፡
ማኅደረ፣ ሊታዘንላት የሚገባና መንገድ የጠፋባት ልጅ መሆኗን ነግሮኛል፡፡ በአካል ሳገኛትም የገባኝ እውነት ይሄ ነው፡፡ ቃልኪዳን የማየት ችግር አለባት፡፡ ግን ችግር ያለባት አትመስልም፡፡ ዓይኖቿ ያሳስታሉ፡፡ የሚያዩ ይመስላሉ፡፡ መነጽር አትጠቀምም፡፡ ዘንግ አትይዝም፡፡ እጇን ይዘው የሚመሩ፣ ወደምትፈልግበት የሚያደርሱ ብዙ ወዳጆች አሏት፡፡
ንቁ ናት፤ ቀልጣፋ፤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ አብረዋት ካሉ ሰዎች ጋር የወዳጅነትን መንፈስ በቶሎ መፍጠር የምትችል፡፡ ከእኔ ጋር አራት ኪሎ፣ ማለዳ ካፌ ተቀጣጥረን በተገናኘንበት ጊዜ፣ የሰነበተ ወዳጅነት ያለን እንጂ የዕለቱን ዕለት የተዋወቅን አንመስልም ነበር፡፡ ሳቋ ሞቅ ያለ ነው፤ ፈገግታዋ የደመቀ፡፡ ጠይም ናት፤ ባለመካከለኛ ቁመትና ለጥቂት ከቅጥነት ያመለጠ ሰውነት ያላት፡፡
ማኅዲ እንደነገረኝ ቃልኪዳን የደረጃ ተማሪ ናት፡፡ አጥንታ አይደለም፡፡ ደብተር ላይ መተከል አልወድም የምትለው ነገር አላት፡፡ የሰማችውን ስለማትዘነጋ ነው የደረጃ ተማሪ የሆነችው፡፡ እኔ ሳገኛት 17 ዓመቷ ነበር- የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ…
ጮክ ብላ አታወራውም እንጂ አባቷ ስመጥር ድምጻዊ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በህይወት ዘመናችን ከምናደንቃቸው ዘፋኞች መካከል አምስቱን እንድንጠራ ብንጋበዝ፣ የእሷ አባት የመጠቀስ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ድምጻዊ ግን ‹ልጄ ናት!› አይልም፡፡ ከሚስቱ ሰርቆ ነው የወለዳት፡፡ ታደንቀው ከነበረ፣ ከአንዲት የአዲስ አበባ ልጃገረድ የወለዳት ይህቺ ሴት፣ መልኳ እሱን ነው የሚመስለው፡፡ ጓደኞቹ፣ ወዳጆቹ እና አንዳንድ የማይመለከታቸው ሰዎች ሁሉ ይህንን ምስጢር ያውቃሉ፡፡ ያቀርቧታል፤ ያጫውቷታል፤ ያበረታቷታል፡፡
እሷም ዘፈን ትወዳለች፤ የአባቷን ዘፈኖች አስመስላ ታንጎራጉራለች፡፡ መድረክ ላይ አይደለም፡፡ ደስ ሲላት፣ ደስታ የሰጣትን ሰው የምታመሰግነው፣ ከዋለላት ውለታ ጋር ተዛማጅነት ያለውን አንድ ዘፈን በመዝፈን ነው!
ቃልኪዳን ቆንጆ የምትባል ዓይነት ሴት አይደለችም፡፡ ዐይኗን ያጣችው ካደገች በኋላ ነው፡፡ በርግጥ ዐይኗን፣ አባቷንና የጀርባ አጥንቷን (ስፓይናል ኮርዷን) ያጣችው በለጋ ዕድሜዋ ነው፡፡ ከባድ የሆነ ራስ ምታት ነበራትና፣ ሀኪም ቤት ሄደች፡፡ ሐኪሙም ‹ያደረባት በሽታ ከኔ ችሎታ በላይ ነው፤ መታከሚያ መሣርያውም ያለው አንድ ቦታ ብቻ ነው፤ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል! እዚያ ሂዱ!› ብሎ ሰደዳቸው፡፡
ሄደች፡፡ እናቷና የእንጀራ አባቷ እያዋከቡ ወሰዷት፡፡ ተደናግጠው፡፡ ቃልኪዳን አልጋ ትያዝ ተባለ፡፡ ያዘች፡፡
አንድ ቀን ማታ፣ ጤንነቷን ይከታተል የነበረው ነርስ፣ ሌሊት ቀስቅሶ፣ አስታማሚዋንም አስነስቶ ‹ክኒን አላት!› አለ፡፡ ቃልኪዳን ክኒን መዋጥ አትወድም፡፡ እንደማትወድ ነርሱ ያውቃል፡፡ ‹በመርፌ ይቀየርልኝ!› ብላ ወትውታውም አልሠማትም ነበር፡፡ ያን ሌሊት መጣና፣ ሁለት ክኒን ፍሬ መዳፏ ላይ ሲያኖር ግን አልተሳቀቀችም፡፡ አልተነጫነጨችም፡፡ ‹ክኒኑን ቀየራችሁት እንዴ?› አለች፤ ‹ሰሞኑን በተከታታይ ሌሊት ተነስቼ የዋጥኩት ክኒን በቀለሙም በመጠኑም ይህን አይመስልም!› አለችው በዝግታ፡፡ ነርሱ ተቆጣ፡፡ ‹የማደርገውን አውቃለሁ› አለ፡፡ ‹አሞሽ ስለነበር፣ የክኒን ጥላቻም ስላለብሽ ነው እንጂ ሰሞኑን የዋጥሽው ክኒን ይሄ ነው!› አላት፡፡ አስታማሚ ዘመድም፣ ‹ቃልዬ! ላንቺ ብሎኮ ነው፡፡ ለመዳን መታከም አለብሽ!› አለቻት፡፡
ቃልኪዳን ክኒኖቹን ዋጠቻቸው፡፡
ሌሊቱን በሙሉ ስትሰቃይ አደረች፡፡ አጠገቧ አንድ ጎልማሣ ሰው አለ፤ በጀርባ ህመም ክፉኛ የተሰቃየ፡፡ ልክ እሱ ያቃጥለኛል እንደሚለው ስትቃጠል አደረች፡፡ መተኛት ከበዳት፡፡ ኧረ ምን ሆኛለሁ? አለች፡፡ መድኃኒቱ እየሠራ ቢሆን ነው አለቻት አስታማሚዋ – ከእንቅልፏ ጋር እየታገለች፡፡ ቃልኪዳን አልቻለችም፤ ሕመሙ አልተዋት አለ፤ አቁነጥንጦ፣ አቅበጥብጦ፣ አቃጥሎና አሰቃይቶ ብቻ አልተዋት አለ፡፡ ነርሱን ካልጠራሽልኝ! አለቻት አስታማሚዋን፡፡ አስታማሚዋ አመንትታ ነበር፡፡ ሌሎች ታማሚዎችና አስታማሚዎች ግን ይህ ስቃይ ካልተገታ እረፍት አጥታ እረፍት እንደምታሳጣቸው በማመን ነርሱ ይጠራ አሉ፤ አስታማሚዋን ላኳት…
መጣ፤ ነርሱ መጣ፤ መጣና ማስታገሻ ሰጣት፡፡
ቃልኪዳን በአዲስ በሽታ ተጠቃች፡፡ ለመነሳት ሞክራ ነበር – ሽንት ቤት ለመሄድ፡፡ ግን አልቻለችም፡፡ ተንገዳግዳ ወደቀች፡፡ ወገብዋ ለሁለት የተከፈለ መሰላት፡፡ ራስ ምታቷ ከደቂቃ ወደ ደቂቃ ከፍ እያለ መጣ፡፡ አሁን እሷ ብቻ ሳትሆን መላ ቤተሰቧ በድንጋጤ ተመታ፡፡ ምን እየሆነችብን ነው አሉ፡፡ ለዶክተሮቹ ነገሯቸው፡፡
ዶክተሮቹ መቸ እንደጀመራት ጠየቁ፤ ክኒኑን ከወሰደች በኋላ እንደሆነ ተነገራቸው፡፡ ምን ዓይነት ክኒን እንደወሰደች አጥብቀው ሲጠይቁ፣ የክኒኑ ዓይነትና ክኒን ለመውሰድ ቃልኪዳን እንዴት አንገራግራ እንደነበር ተነገራቸው፡፡ የክኒኑን ዓይነት ካወቁ በኋላ ዶክተሮቹ ስሜታቸውን መደበቅ አልሆነላቸውም፡፡ ሀዘንም አረበባቸው፡፡ ነርሱ ስህተት እንደሰራና ያልተገባ መድኃኒት እንዳስወሰዳት ተናገሩ፡፡ መድኃኒቱ የታዘዘው ለእሷ ሳይሆን እሷ አጠገብ ታሞ ለተኛው፣ በጀርባ ህመም ለተሰቃየው ሰው ተሰናድቶ የነበረ ነው፡፡
ቃልኪዳን የማየት ሃይሏ እየደከመ መጣ፡፡ ሁሉም ነገር ብዥ፣ ጭልም ይልባት ገባ፡፡ እየታወረች መሆኑንም ታወቃት፡፡ ማየት አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን፣ ዓይኗ ተከፍቶ ቀለም የማይለይና እንቅስቃሴ የማይረዳ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ በከባድ ራስ ምታት ተጠቃች፡፡ ሞቷን መመኘት ጀመረች፡፡
ቤተሰቦቿ፣ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በምን እንደሆነ ያውቃሉና፣ ሆስፒታሉን ካልከሰስነው፣ ነርሱን ፍርድ ቤት ካላቆምነው በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ፡፡
ዶክተሮቹና ነርሶቹ ግን፣ እናቷንና የእንጀራ አባቷን ደጅ ጠንተው፣ የሚያጋጥምና በቀላሉ ወደነበረበት የሚመለስ ነው የህክምና ጉድለት አሉ፡፡ በህይወት ዘመናቸው ቆጥረው የማያውቁትን ብር ሰጧቸው፡፡ ማየቷ ከህመሟም መፈወሷ አይቀርም አሉና ወደ ክስ እንዳይሄዱ ለመኗቸው፡፡
የቃልኪዳን ቤተሰቦችም፣ ከሀኪሞቹ በላይ አናውቅም አሉና በዚያ ብር ለቃልኪዳን ማባበያ ይሆናት ዘንድ ልብሶች፣ ጫማዎች ገዙላት፡፡ በዚህ ገንዘብ የሕይወታቸው አቅጣጫ ለጥቂት ወራትም ቢሆን ተቀየረ፡፡ በቀን ሶስት ጊዜ በልተው እንደሚያድሩ ሰፈርተኛው እንዲያውቅ አደረጉ፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ፣ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ አንድ ቀን፣ ቤት ውስጥ ከቤተዘመድ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ እየተደረገ ሳለ፣ ‹አንድ ጊዜ ዝም በሉ!› አለቻቸው፡፡ ምን ሰማች ብለው ፊታቸውንና ጆሯቸውን ወደሷ ሲመልሱ፣ ‹የቲቪውን ድምጽ ጨምሩት፤ ቶሎ በሉ፤ ቶሎ፤ ቶሎ!› አለቻቸው አጣደፋ፡፡
የቲቪውን ድምጽ ከፍ አረጉላት፡፡ ኢሉአባቦራ በተባለ ከተማ ሕዝባዊ አገልግሎት ስለሚሰጥ አንድ ሆስፒታል ዶክተሩ ማብራሪያ እየሰጠ ነበር፡፡
እሱ ሲያወራ ግን ቃልኪዳን ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ነበር እንጂ የሚለውን እየተከታተለች አልነበረም፤ ‹እሱ ነው፤ እሱ ነው፤ ይሄ ሰውዬ ነው የተሳሳተ ክኒን እንድውጥ አድርጎ ዓይኔን ያሳጣኝ!› አለች፤ በድምፁ ብቻ ለየችው፤ የት እንዳለ የሚነግራት አጥታ ነበር፤ የሠራኸውን እይ ብላ ዓይኖቿን ልታሳየው ሁለት ሶስት ጊዜ ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ሄዳ ነበር፡፡ ግን አላልተገኘም፡፡ አድራሻውን የሚሰጣት ቀርቶ ‹አውቀዋለሁ!› የሚልም አላገኘችም ነበር፡፡ ይኸው፣ ራሱ ድምፁን ይዞ፣ ከነርስነት ወደ ዶክተርነት አድጎ እዚያ ተገኘ፡፡
ድምጹን ከሰማች በሁዋላ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከአልጋዋ አልወረደችም፡፡
ቃልኪዳን፣ ዐይነሥውራን ትምህርት ቤት ገብታ፣ የቀለም ትምሕርቷን በትጋት ቀጥላ፣ የራሷንና የቤተሰቦቿንና የትምሕርት ቤቷን ስም ብታስጠራም፣ ከያዛት ከባድ የራስ ምታት ሕመም ለጊዜው እንድታገግም በማሰብ የሚሰጣትን ሕክምና ለመከታተል ብዙ ዋጋ ያስፈልጋት ነበር፡፡ ሙሉ ለሙሉ ለመዳን ውጪ አገር መሄድ እንዳለባት አንዳንድ ዶክተሮች ቢነግሯትም፣ እሷ ግን ይህን ማድረግ አልችልም ሳትል፣ ብዙ ገንዘብ ያላቸው ሰዎችን ደጅ ጠንታለች፤ እዚህ አገር የሚደረግላት ሕክምና የተሳካ ይሆን ዘንድ፣ እጃቸውን ወደኪሳቸው ከሚሰዱላት ሰዎች መካከል አንዱም አትሌት ሃይሌ ገብረሥላሴ እንደነበር ነግራኛለች፡፡
የደረሰባትን ሁሉ የሰሙ ሰዎች፣ አንዳንዶች የትምህርት ቤት የዓመት ወጪዋን፣ አንዳንዶች የዓመት ቀለቧንና አልባሳቷን ይሸፍኑላት ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ስንጨዋወት፣ መልሳ መላልሳ ‹ከጥቁር ሰማይ ስር› ስለተሰኘው መጽሐፌ ያላትን ስሜት ትነግረኝ ነበርና፣ ‹ከፈለግሽ ይህን መጽሐፍ በብሬል ቋንቋ ጽፈሽ፣ አሣታሚ አነጋግረሽ፣ የሚገኘውን ትርፍ ሙሉ ለሙሉ ልትወስጂው ትችያለሽ!› አልኳት፡፡ ደስታዋ ልክ አልነበረውም፡፡ ፋሲካ ሆነች፡፡ ለራሷ የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን፣ ለመሰሎቿም ዋጋ ያለው ሥራ እንደሆነ፣ ስሟን በታሪክ መዝገብ ላይ የሚያሰፍር ነገር በመገኘቱ ደስታዋ በዛ፡፡ እዚያው እንደተቀመጥን ስልክ ደዋወለች፤ አሳታሚዎችን አነጋገረች፡፡ ታድዬ! አለች፡፡ እቅዳችን በቀላሉ የሚተገበር መሆኑን ነገረቺኝ፡፡
ቀጥሎ ስለእሷ የሰማሁት በህመሟ ክብደት የተነሣ፣ የሚያስጨንቃት ነገር እንዳትሰራ፣ ሙዚቃ በመስማትና በመጫወት ራሷን እንድታዝናና በሀኪም ትዕዛዝ እንደተሰጣት ነው- ኮሪያ ሆስፒታል ነበር የምትከታተለው፡፡
ትምህርቷን ጨርሣ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብታ፣ ከፍተኛ ማዕረግ ስትመረቅ ነበር ይታያት የነበረው፡፡ሆኖም፣‹ተረጋጊ!› አሏት፣ ዶክተሮቹ፡፡ ‹እስከመቼ?› ብላ ጠየቀች፤ ‹ድነሽ እስክትነሽ፤ ጭንቅላትሽ ትምሕርትን ማስተናገድ እስኪችል…›
‹እኔኮ ስማር አልጨናነቅም!› አለች፤ ‹ቢሆንም…› አሏት፡፡ አቋረጠች፡፡
አንድ ቀን፣ ከማኅደረ ጋር የቆጥ የባጡን እያወራንና ዕውቀታችንና ዘመናችን በፈቀደልን ልክ፣ በአገራችን ታሪክና ባሕል ዙርያ እየተወያየን ሳለ፣ ‹እኔ ምልህ መቼ ነው ቃልኪዳንን የማያት? ስለእሷ ሳስብ በጣም ነው ራሴን የምታዘበው?› አልት፡፡ በዝምታና በተመለደች ሀዘን የለበሰች አተያዩ ሲያተኩርብኝ ቆየና፣ ‹‹ለምንድነው ራስህን የምትታዘበው?› አለኝ፡፡
‹ቃል ገብቼላት ነበር፤ አለንልሽ ብያት ነበረ፤ አይዞሽ ወንድም እሆንሻለሁ ዓይነት ተስፋዎች ሰጥቻት ነበር፤ በጣም አፅናንተናት ነበረ፤ ምንም አታድርጉልኝ ግን እየተገናኘን ስለ ሥነጽሑፍ ስለጋዜጠኝነት እናውራ ስትለኝ በፈለግሽው ቀን ደውለሽ ጥሪን ብያት ነበረ፤ ለጊዜው የዘነጋኋቸው ብዙ ቃልኪዳኖች ገብቼላት ነበረ፤ እኔ ግን ጠፋሁባት፤ ዛሬ ነገ ስል ስዘናጋ፣ ይሄው ወራት አለፈ፤ በቃሌ አልተገኘሁም፤ በጣም ነው የማፍረው!› አልኩት፡፡
ዝም አለ፤ ዐይኑን ከዐይኔ ሳይነቅል፡፡
‹እኔም ካገኘኋት ቆይቻለሁ!› አለ በዝግታ፡፡
‹አንተም?!›
‹አዎ፤ አልሞላልህ አለኝ!›
‹ከሚያገኟት ሰዎችስ ትገናኛለህ – ማለቴ እነዚያ የቤት ኪራይና የዓመት ቀለብ ከፍለው ከሚያስተዳድሯት ወዳጆችህ ጋር?›
‹ያገኟታል፤ በጣም ነው የሚያምማት ብለውኛል፤ በጣም ነው የምታሳዝነው፤ ምናልባት ለሕክምና ወደ ውጪ ሀገር ተልካ ይሆናል፤ ወይም ከወላጅ አባቷ ጋር ታርቃ…›
‹ደውዬላት ነበር፤ ግን ስልኳ ዝግ ነው› አልኩት፡፡
‹አዲስ ነገር ካለ ጠይቄ እነግርሃለሁ…›
ሌላ ቀን፣ አራት ኪሎ፣ ምርፋቅ በተባለ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ ቡናችንን እየጣን ሳለ፣ አሁንም ‹ኧረ የዚያች ልጅ ነገር የት ደረሰ?› አልኩት፡፡
‹ለምንድነው አጥብቀህ የጠየቅከኝ?›
‹ቃሌን በልቼ…›
አላስጨረሰኝም፡፡ አንገቱን ደፋ፡፡ የሆነ የሚረብሽ መንፈስ ሰፈረበት፡፡ ‹እንዱ፣ ከወር በፊት ጠይቀኸኝ ነበር፡፡ እንደጠየቅከኝ ወዲያው ስለሚሰማህ የጥፋተኝነት ስሜቶች ነገርከኝ፡፡ እንደዚያ ባለ ስሜት ውስጥ ሆነህ እውነቱን ልነግርህ አልደፈርኩም ነበር!› አለኝ፡፡
‹የተፈጠረ ነገር አለ?›
‹አዎን ቃልኪዳን አርፋለች…›
Filed in: Amharic