>

ጥንድ የጥበብ ገበሬዎች! (ተቦርነ በየነ)

ጥንድ የጥበብ ገበሬዎች!
ተቦርነ በየነ
      አበበ መለሰ እና ይልማ ገብረአብ በኢትዮጲያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ መተኪያም መለኪያም በቀላሉ የማይገኝላቸው እንደወይን እየቆዩ በሄዱ ቁጥር ጣእሙ የሚጨምር ተወዳጅ  ስራ የሰሩ መልካም የጥበብ ገበሬዎች ናቸው። በተለይ ላለፉት 35 ዓመታት የኢትዮጲያን ሙዚቃ ተሸክመው  ዘመን እንዲሻገር ትልቅ ዋጋ ከከፈሉት የጥበብ ሰዎች መካከል አበበና ይልማ ቅድሚያውን ይይዛሉ።ከሰባዎቹ መጀመሪያ እስከ ሰማኒያዎቹ አጋማሽ ድረስ ለወጡ ስኬታማ ድምጻዊያን የሞያው ውሃ ልክ ሆነው ያቆሟቸው እነዚህ ጥንድ የጥበብ ገበሬዎች ናቸው።
         የኢትዮጲያ ሙዚቃ እንደዛሬው ዘፋኙ በ 4 ጋርድ ሙዚቃው በአንድ ኦርጋን የመታጀብ ደረጃ ከመድረሱ በፊት አበበ መለሰ፣ ይልማገብረአብ እና ሮሃ ባንድ በጋራ   የከፈሉት ዋጋ ጥሩ ስራ በዘመን የማይገደብ ለመሆኑ ምስክር ነው።
       ስለ ታላቁ ይልማ ገብረዓብ  የገጣሚነት ብቃትና ችሎታ የተወሰነ ነገር ለማንሳት እሞክራለሁ። ይህም ውስን ዳሰሳዬ በኔ የግዜና የአቅም እጥረት የተገደበ እንጂ የይልማ የብቃት መለኪያ ተደርጎ እንዳይቆጠርብኝ አደራዬ ጥብቅ ነው። ታላቁ
ገጣሚ ይልማ ከጻፈውም ከሚጽፈውም በላይ ብዙ ነው። ትልቅ ነው።
         ከተወዳጁ ገጣሚ ይልማ ገብረአብ  ጥልቅ የንፅፅር ስንኞች ውስጥ በኤፍሬም ታምሩ የ1978 ስራዎች ውስጥ የተካተቱትን በጥቂቱ ልግለፅ።
       በዚህ የኤፍሬም አልበም ውስጥ ወለባ በተሰኘ ዘፈን ውስጥ ከተካተቱት ስንኞች መካከል አንዱ የንጽጽር ግጥም እንዲህ ይላል።
             “የአጋም እሾህ በቅሎ እግሬን ቢወጋው
               አንቺ ብትለይኝ እቴ በነጋው
              ለእግሬም ሀኪም አልል ላንቺም አማላጅ
              እሾህን በእሾህ ነው ሴትን በሴት ልጅ ይላል።
     በህክምና ከበሽታው መድሃኒት እንደሚሰራ ሁሉ በዚህ ስንኝ ውስጥም ንጽጽሩ በግልጽ ተቀምጧል።
በዚሁ ስራ ውስጥ ስለፍቅሩ ፅናት የጠቀሳቸውን እማኞች በመጥራት እንዲህ ይላል።
         “ስላንቺ እያ ሰብኩኝ ቆሜ ለማደሬ
          ኮከብ ጨረቃ ነው እማኝ ምስክሬ ይላል።
ለማንም በማያዳሉና ያዩትን እውነት ብቻ በሚመሰክሩ ከእኛ ጋር ማን ወቶ ነበር ብለው ማየት በሚችሉት አስመሰክራለሁ በሚል ነው የፍቅሩን ፅናት የገለፁው
      ወደ ሌላው ሳልፍ
“ሃላ እንዳይቆጭሽ” አልበም ከወጣ ከአንድ አመት በሃላ አንድ አደጋ ደርሶ ነበር። ወሩ ሚያዚያ ነበር። ከሸራተን ቁልቁል ወደ ፍል ውሃ የሚመጣ የሙሽራ መኪና አደጋ ደርሶበት ሙሽሮቹ የሞቱበትን አሳዛኝ ዜና ስሰማ የዚህ ታላቅ ደራሲ ስንኝ ምስሉ (ክሊፑ) ተከሰተልኝ።“ሰው መሰረቱ” በሚለው ዘፈን ውስጥ ይህን አደጋ የሚገልጹ ስንኞች አገኘሁ።
      ባለም ላይ ጊዜ ነው ሁሉን የሚያደርገው
      ተዝካሩን ያወጣል ሰውስ በሰረገው
የስነ ፅሁፍ ሰው ተንባይ መጭውን አመልካች መሆን አለበት ለሚለው አባባል በቂ ምስክር የሆነኝ የዚህ ገጣሚ ስንኝ አንዱ ይህን ይመስላል።
      የታላቁ ገጣሚ ይልማ ገብረአብ ጥልቅ ስንኝ ወደ ሚዳሰሱበት ወደ ፀጋዬ እሸቱ ስራዎች ላምራ።
መረዳዳት ቢኖር በተሰኘው ፀጋዬ፣ አረጋኸኝ፣ ነዋይ በጋራ ባወጡት አልበም ከተካተቱት የፀጋዬ እሸቱ ስራዎች ውስጥ “ጥንትም ላይሆንልሽ” የተሰኘ የዚህ ታላቅ ደራሲ ስራ
ይገኛል። በዚህ ስራ ውስጥ ትልቅ መልእክት አለ። በተለይም ስለቅንነት ፣ልዩነትን በፍቅር ስለመፍታት፣ ልዩነታችን ሌላውን በማጥፋት ወይም በማስወገድ ሳይሆን የተሻለ ፍቅርና
መተሳሰብን በማሳየት የተሻለ ፍቅርን ያ ሳለፍንበትን ጊዜ አስበን መልካም መመኘት ይገባል የሚል ስንኝ ተካቷል።
           “አንዱ ብሩን ሲቸር ሌላው ጌጥ ያመጣል
              የኔ ልብ ሃብታም ነው እምነቱን ይሰጣል
               ዛሬም አለኝ ፍቅር የያዝኩት ሰስቼ
              መቸም በዚህ በኩል አላውቅም ደኽይቼ።
ፍቅር ፈጣሪ ነው ከፈጣሪ በላይ ምንትልቅ ሃብት አለ የሚል ትርጉም ይሰጠኛል ለኔ!
ፍቅር ና አፍቃሪነት የፈለጉትን በማግኘት ብቻ ሳይሆን በማጣትም መገለፁን በዚሁ ስራ ውስጥ እናገኛለን።
           “ዛሬ እኔን ዘንግቶ ገላሽ ሰው ቢለምድም
             ትላንት ወደሽኛል ክፉሽን አልፈቅድም”
ያለፈን ጥሩ እያሰቡ ለነገ ክፉ አለመሆን ከዚህ በላይበምን ይገለፃል?
       ሌላው ፀጋዬ፣ አረጋኸኝ፣ ነዋይ፣ ፀሐዬ በጋራ በሳተሙት አልበም ውስጥ በተካተተው የፀጋዬ እሸቱ “ወግ የለኝም” በተሰኘው ስራ ውስጥ የዚህን ታላቅ ገጣሚ ስንኝ ስንቃኝ እንዲህ ይላል።
          “ቀብሬም ስገባ ሞት የቀማኝን ሰው
          ገና ሳይወጣልኝ ጮኬም ሳልጨርሰው
               እያንሰቀሰቀኝ ያጣሁት ዘመዴ
             የርም እህል ይመኛል ሃዘንተኛው ሆዴ
 ይላል።
      ለሆድ ሁሉም ቀን አንድ ነው። የዕለት ግብሩን ከመጠየቅ የማይቦዝን ይሉኝታ ቢስ የአካላችን ክፍል ሆድ መሆኑን በሚገባ የገለፀበት ክፍል ነው።
       ወደ ሌላው ስራ ስናልፍ የሰው ልጅ አብሮ በኖረ ቁጥር
መተሳሰብን፣መረዳዳትን፣መደጋገፍን መሰረት አድርጎ መኖሩ ትልቅ ሃይማኖት ነው። አብሮመብላትን የመሰለ ትልቅ ሃይማኖት የለም ያለበትን ጥልቅ ስራውን በነዋይ ደበበ አዲስ ቤትሽ አልበም ውስጥ “ዘንድሮ” በሚለው ዘፈን ውስጥ እንዲህ በሚል ተወዳጅ ስንኝ አስፍሮታል።
       “ቢፀድቅም ቢኮነን ሁሉም እንደእምነቱ
         የሌለውን ነገር ካለው መጋራቱ
        አብሮ መብላት ነበር ለሰው ሃይማኖቱ ይላል
እውነትም ከዚህ በላይ ሃይማኖትስ ምን ህግ አለው?
በዚሁ የነዋይ ደበበ አልበም ውስጥ ተደላድለሽ ተኚ በተሰኘው ስራ ውስጥ  ምስልና ድርጊትን ያጣመረ የተወዳጁን የይልማን ስንኝ እናገኛለን።
        “አትጨነቅ ሆዴ እንሂድ እናዝግም
           እንባ አካልን እንጂ ሃዘንን አይጠርግም።
ከልጅነት እስከ እውቀት የጠረግናቸው እንባዎቻችን ሃዘናችንን ወይስ አካላችንን ጠረጉ?
       ወደ ቴዎድሮስ  ታደሰ የይልማ ገብረአብ ተወዳጅ ስንኞች ስናልፍ፦
 ቴዎድሮስ ታደሰ  1978 ባሳተመው አልበም ውስጥ በተካተተው “መዋደዳችንን ”በተሰኘው ስራ ውስጥ ያለው ስንኝ የውበትን አላፊነት የገላን ረጋፊነት እና ጊዜያዊነት የፍቅርን ሃያልነትና ዘላቂነት የሚገልፀው ስንኝ እንዲህ ይላል።
        “ውሎ እያደር አካል ሰረገላው መሰስ ይላል
      በቁንጅና በራስ ገላ ማመኑ እንደ ሰባራ ምርኩዝ
                                                           ይጥላል
          ስለ መውደድ ደፋም ቀናም ያለ ይጠቀማል
        መቼም ቢሆን የእኩል ፍቅር የእኩል ነው
                           ደገፍገፍ እንዳረገ ይከርማል
     ሌላው የቴዎድሮስ  ታደሰና አሰፉ ደባልቄ በጋራ ባሳተሙት አልበም ውስጥ ከተካተቱት የቴድሮስ ታደሰ ስራዎች አንዱ “አጉል ተቆራኝቶኝ” ውስጥ የተካተቱት ስንኝ እንዲህ ይላል።
          “ተናደጂ ልታገስ ቁጣሽን ላብረደው
            እዳው ተችሎነው ሰው የሚወደደው
በዚህ ስንኝ ውስጥ ያለው መልእክት ለኔ እንደሚገባኝ በሚፈልጉት ውስጥ ያለን የማይፈለግ ነገር መቀበል ነው የማፈቀር መለኪያው! ለምሳሌ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲወድ እዳውን ችሎነው የወደደው። ሌላው ቀርቶ ከባንክ ስንበደር እንኳ እዳውን ችለነው የወደድነውን ብድር የምንወስደው!                  በሌላ የቴድሮስ ታደሰ የ1981 ስራ ውስጥ “የጎኔ ባላ ማገር” በተሰኘው ስራ ውስጥ “ቢቀጥንም አንገት ነው እራስን ከቻለ” ይላል።
     የስራን ታላቅነት በራስ መተማመንን ለመግለፅ ከዚህ የተሻለ ስንኝ ፈልጌ አላገኘሁም።
    ታላቁ ገጣሚ ይልማ  ሳይወዱም  ሳይመርጡም ለስደት የተዳረጉ ወገኖቹን ሀዘን እና የሀገሩን ታላቅነት በተመለከተ በብዙአየሁ ደምሴ “ሳላይሽ” አልበም ውስጥ ባለ አንድ ስንኝ ይህን ይላል።
                      ፅላቱን በፂዮን ግማዱን በግሸን
                       ሌላ ዓለም ያጣውን እኛ ጥለን ሸሸን ፤
        ስለ ይልማ የበርካታ አመታት የሙያ ብቃትና ቆይታ ሳስብ ሁሌ የምገረመው እስከዚህ ዘመን ክብሩን ጠብቆ ደረጃና አቅሙ ሳይዋዥቅ ከሙሉቀን መለሰ”ይረገም”
እስከ ቴዎድሮስ  ካሳሁን ፀባዬ ሰናይ መዝለቁ ነው። ምክንያቱም 35 ዓመት በሞያ ከነብቃት መቆየት ቀርቶ በህይወት መኖር ከባድ የሆነበት ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል። ሁሌም ይህን ሳስብ ስለ ይልማ ታላቅነት እገረማለሁ።
ይልምሽ ሽልማትህ ተሰጦህ ቢሆንም እንኳን ደስ ያለህ ማለት ተገቢነው።
ከተወልደ በየነ
Filed in: Amharic