>

የሶማሌ ክልልን ማስገንጠሉ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሰጡትን አረቦች ለማስደሰት ወይስ...? (አቻምየለህ ታምሩ)

የሶማሌ ክልልን ማስገንጠሉ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሰጡትን አረቦች ለማስደሰት ወይስ…?
አቻምየለህ ታምሩ
የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ኦብነግ «ሶማሌ ክልል»ን ከኢትዮጵያ መገልጠል እንደሚችል አስመራ ላይ ተስማምቷል! የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ዳር ድንበር የማይጠብቅ ስምምነት ከኦብነግ ጋር በማድረግ ኦብነግ ሶማሌ ክልልን መገንጠል እንደሚችል ስምምነት ላይ የደረሰው የዐቢይ አገዛዝ ትናንትና ካራማራ ላይ ኢትዮጵያውያን ሞተው መሬቱን ኢትዮጵዊ አድርገውታል ያለውን ምድር ነው። ድንቄም አገር ግንባታ!
ኦብነግ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. በሶማሊያ በወቅቱ ሞቃዲሾን ይዞ የነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የሽግግር መንግሥት አካል ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ (1724/2006) እንዳሳወቀው ሞቃዲሾን ይዞ ለነበረው ለእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ጊዜያዊ መንግሥት ድጋፍ ይሰጡ ከነበሩ አገሮች መካከል ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ተጠቃሾች ነበሩ። የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል የነበረው ኦብነግ አላማው የዚያድ ባሬን ባለ አምስት ኮከብ ታላቋን ሶማሊያን መፍጠር ነው። በሌላ አነጋገር የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ አስመራ ላይ ከኦብነግ ጋር የደረሰው ስምምነት በሳዑዲ ይደገፍ የነበረው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል የሆነው ኦብነግ የዚያድ ባሬን ህልም እንዲያሳካ ነው።
እንደሚታወቀው የኦብነግ ራዕይ ቀያሽ የሆነው ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተው ባሌን፣ ሐረርጌንና አርሲን ጨምሮ እስከ ናዝሬት ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ግዛት የታላቋ ሶማሊያ አካል ናቸው የሚል ትርክት ፈጥሮ ነው። የዚህ ራዕይ ውሉድ የሆነው ኦብነግም አላማው ያው ተመሳሳይ ነው። ጥያቄው ዐቢይ አሕመድ አስመራ ላይ ከኦብነግ ጋር ሶማሌ ክልል መገንጠል እንደሚችል የተስማማው ኦብነግ የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አባል በነበረበት ወቅት ትረዳ የነበረችዋንና ለዐቢይ አገዛዝም ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሰጡትን አረቦች ለማስደሰት ነው? ወይንስ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ? ለዚህስ ቀብድ ይሆን አረቦቹ  ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለዐቢይ አገዛዝ ሰጡ  የተባለው?
የዐቢይና የኦብነግ የአስመራው ስምምነት የኦብነግ ደጋፊው ሻዕብያና የኦብነግ ደጋፊ የሆነችው ሳዑዲ ያስማማችው የሳዑዲው የኢሳያስና የዐቢይ አሕመድ ስምምነት አካል ይሆን?
Filed in: Amharic