>

የአብይ መንግስት ኦጋዳንን በህዝብ ውሳኔ ለማስገንጠል ከስምምነት ደረሰ!!! (ቢቢሲ አማርኛ)

የአብይ መንግስት ኦጋዳንን በህዝብ ውሳኔ ለማስገንጠል ከስምምነት ደረሰ!!!

 

ቢቢሲ አማርኛ

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርና የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ያደረጉትን ድርድር ተከትሎ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የግንባሩ የውጭ ግንኙነት ፀሐፊ አቶ አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም ከኢትዮጵያ መንግሥት ስለደረሱበት ስምምነት አስመልክቶ ለቢቢሲ ሶማልኛ እንደገለፁት፤ የሶማሌ ህዝብ ዕጣ ፈንታውን በነፃነት ራሱ መወሰን እንዳለበ ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው።

ህዝቡ መብቱን በመጠቀም የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት በተጨማሪ ግንባሩም የሚታገልለትን አላማም በሰላም እንዲያስቀጥል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

“በዚህም መሰረት የራስን ዕድል በራስ መብትን ለመወሰን ህዝበ- ውሳኔ እንዲካሄድና ህዝቡ ከኢትዮጵያ መገንጠል ከፈለገ ያ መብት እንዲከበር፤ መቆየትም ከፈለገ ያ ውሳኔ እንዲከበርለት ውሳኔ ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

ህዝበ ውሳኔውንም ለማስፈፀምም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ኮሚቴ እንደሚመሰረትም አስታውቀዋል።

ለበርካታ ዓመታት በምሥራቃዊው የሃገሪቱ አካባቢ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ወደ ሃገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ መወሰኑ ለሃገሪቱ ሰላም በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ለሶማሌ ክልል ሰላም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኦብነግ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ትግል ያደርጉ ከነበሩ አማፂ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1984 ነበር የተመሰረተው። ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ሦስት የፖለቲካ ቡድኖች ከሽብር ቡድን ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው ውሳኔ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ በውጪ የሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።

አማፂው አብነግ የኦጋዴን ሕዝብ ብሎ የሚጠራውን በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው የሶማሌ ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር በፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።

ኦብነግ ከምስረታው አስራ አራት ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ጋር በመዋሃድ የሶማሊ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን መስርተው ነበር።

ምን መቼ ሆነ?

ሚያዚያ 1996 ዓ.ም፡ የተቃዋሚ የሆነው ሬዲዮ ነፃነት ኦብነግ በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ላይ በፈፀመው ጥቃት በርካታ ወታደሮችን መግደሉን ዘገበ።

መጋቢት 1998 ዓ.ም ፡ የኦብነግ መሪዎች ከዴንማርክ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ያሉ ሶማሌዎች ላይ በመንግሥት ይፈፀማል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስረድተዋል። የዴንምርክ ባለስልጣናትም ያለው አስተዳደር ዴሞክራሲን የማይተገብር በመሆኑ ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን እርዳታ አቋርጠዋል።

ጥር 2001 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት አስተላለፈ።

ጥቅምት 2002 ዓ.ም ፡ የኦብነግ ኮምኒኬሽን ሃላፊ ሁሴን ኑር የፑንትላንድና ሶማሊላንድ አስተዳደሮች ከኢትዮጵያ ሸሽተው የሄዱ ሶማሌዎችን አሳልፈው ለኢትዯጵያ መንግሥት ይሰጣሉ ሲል ከሰሰ።

ነሐሴ 2002 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርቧል የሚለውን ዘገባ አስተባበለ።

ጥር 2003 ዓ.ም ፡ ከ400 የሚበልጡ የግንባሩ አመራሮችና አባላት ከእስር ተለቀቁ።

ሰኔ 2003 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ በኢትዮጵያ መንግሥት ተፈረጀ።

ጥር 2004 ዓ.ም ፡ ግንባሩ እንግሊዝ ውስጥ ባወጣው መግለጫ መንግሥት አጠቃላይ የሆነና በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት በገለልተኛ ስፍራ ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆነ ኦብነግ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ።

ጥቅምት 2005 ዓ.ም ፡ ኦብነግ መስከረም ላይ በኬንያው የመከላከያ ሚኒስትር ሞሃመድ ዩሱፍ ሃጂ አደራዳሪነት ናይሮቢ ውስጥ ከመንግሥት ጋር ሲያደርገው የነበረው የሰላም ድርድር ተቋረጠ።

ጥር 2008 ዓ.ም ፡ ኦብነግ በሶማሌ ክልል በሚካሄደው የነዳጅ ዘይት ፍለጋ የክልሉን ህዝብ ያላሳተፈ በመሆኑ የህዝቡን ጥቅም የሚያስከብር እርምጃ እንደሚወስድ በፍለጋው ላይ የተሰማሩን የውጪ ኩባንያዎችን አስጠነቀቀ።

ግንቦት 2009 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱን ቡድኖቹ ባወጡት መግለጫ አሳወቁ። ሁለቱ ቡድኖች ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ ለሦስት ቀናት ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ነው ውሳኔያቸውን ያሳወቁት።

ነሐሴ 2009 ዓ.ም ፡ የሶማሊያ መንግሥት የኦብነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አብዲካሪም ሼክ ሙሴን (ቀልቢ ደጋ) በሰሜን ሶማሊያዋ ከተማ አዳዶ ውስጥ ይዞ ለኢትዮጵያ መንግሥት መስጠቱን አረጋገጠ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት ውይይት መጀመራቸውን ተከትሎ የኦብነግ ምክትል ሊቀመንበርና ቃል አቀባይ ሙሃመድ ኦስማን አዳኒ ግንባራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ተናገሩ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ በአወዛጋቢ እርምጃ በፕሬዝዳንት ፎርማጆ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠው የኦብነግ የጦር አዛዥ አብዲካሪም ሙሴ (ቀልቢ ደጋ) ተለቀቀ።

ሰኔ 2010 ዓ.ም ፡ የኢትዮጵያ ካቢኔ አርበኞች ግንቦት 7ን እና ኦነግን ጨምሮ ኦብነግን የሃገሪቱ ፓርላማ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲያስወጣ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ አቀረበ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ግንባሩን የሽብር ቡድን ነው የሚለውን ውሳኔውን ውድቅ እንዲያደርግና ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ ስለሰጠው የጦር አዛዡ በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅ ሃሳብ አቀረበ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ጅግጅጋ ውስጥ የተከሰተውን ግጭት አውግዞ ሁሉም ወገኖች ከኃይል ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የሰላም ጥሪን ተከትሎ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚሆን የተናጠል ተኩስ አቁም አወጀ።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ አስር የሚደርሱ የኦብነግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በማዕከላዊ ሶማሊያ ጋልሙዱግ በሚባለው ስፍራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ ኦብነግ ሙስጠፋ ኦማር የሶማሌ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበለው ገልጾ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ አስጠንቅቋል።

ነሐሴ 2010 ዓ.ም ፡ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሃመድ ኦማር በቁጥጥር ስር መዋል እንደሚደግፍና ይህም ፍትህን ለማስፈን የተጀመረ ትክክለኛ እርምጃ ሲል ገልጾታል።

የኦብነግ መሪዎች

ሊቀመንበር ኡትማን አድም ሙሃመድ ኡማር (ከጥቅምት 2002 ጀምሮ)

ምክትል ሊቀመናብርት፡ አዳኒ ሙሃማድ ኦስማን፣ ኦማር ሙሃመድ ኢስማኤል

የኮምኒኬሽን ላፊ፡ ኑር ሁሴን

Filed in: Amharic