>
5:13 pm - Sunday April 18, 9288

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ
ባለፉት ዓመታት በክልላችንም ሆነ በሀገራችን ሲከሰቱ በነበሩ ግጭቶች በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ ግጭቶች ካደረሱብን ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፓለቲካዊ ኪሳራ ለመወጣት በተደረገው ትግል በመላ ሀገራችንና ክልላችን የሰላም አየር መንፈስ ጀምሯል፡፡
ይሁን እንጂ የአማራ ብሔራዊ ክልል ከትግራይ ብሔራዊ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የወልቃይትና ራያ አላማጣ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሰላም መታወክ እየገጠመ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ወልቃይት አካባቢ በማንነታችን ብቻ ጥቃት ደረሰብን ያሉ የወልቃይት አማራዎች ተፈናቅለው በጐንደር ከተማ የሰፈሩ ሲሆን በሌላ በኩል በራያ አላማጣ በተፈጠረው ግጭት በሰው ህይወትም ጭምር ጉዳት አድርሷል፡፡ በተከሰተው ግጭት በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል፡፡
የተከሰተው ግጭት መነሻው የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሲሆን ይህንን ጥያቄ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ህገ-መንግስታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ አሁንም ቢሆን መፍትሄው ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት በማድረግ ህገ-መንግስቱ ላይ በመመስረት መፍትሄ መስጠት እንጂ የሃይል እርምጃ መውሰድ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
በአንድ ክልል የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ለአጐራባች አካባቢዎች መትረፉ አይቀርምና የሰሞኑ የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ችግር ለክልላችንም ትልቅ የፀጥታ ስጋት ሆኗል፡፡
ከዚህ ሌላም አንዳንድ ወገኖች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚፈጠረው ችግር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መክሰሳቸው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ መሠረት ቢስ ውንጀላ ነው፡፡ በመሆኑም የክልላችን መንግስት ይህንንን ከእውነት የራቀ እና ኃላፊነት የጐደለውን ክስ አይቀበለውም፡፡
በአዋሳኝ ክልሎች የሚፈጠረው ግጭት የሌላ ክልል ጉዳይ ነው ብለን የምናልፈው ሳይሆን ተሻጋሪነት ያለው ሁላችንንም የሚያውክ የሰላም ጠንቅ ነው፡፡ የዜጐች ጥያቄም በህገ-መንግስታዊ መንገድ ብቻ መልስ ማግኘት ይገባዋል፡፡ በመሆኑ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ህጋዊና ሰላማዊ ጥረት ሁሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን እያረጋገጥን በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ.ም
ባ/ዳር
Filed in: Amharic