>

ለአንድ ብሄር ምን ያህል መሬት ይበቃዋል? (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

 

ለአንድ ብሄር ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?)

ያሬድ ደምሴ መኮንን

 

(ክፍል 1)

 

ቶልስቶይ ለአንድ ሰዉ ምን ያህል መሬት ይበቃዋል የሚል አጭር ልብ-ወለድ አለችዉ፡፡ማለዳ ጀምበር ስትወጣ ከተነሳበት ቦታ ጀምሮ ቀኑን ሙሉ በእግሩ ተጉዞ አቅሙ የፈቀደዉን መሬት አካሎ፣ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት ወደተነሳበት ቦታ ለመድረስ ከቻለ ያ በእግሩ ዞሮ ያካለለዉ መሬት በሙሉ በ1000 ብር ብቻ የእርሱ እንደሚሆን ስለተነገረዉ pakhom የተሰኘ ገበሬን እጣ ፋንታ ይነግረናል ቶልሰቶይ፡፡ይህ pakhom የተባለ ስስታም ገበሬ በጉዞዉ ወቅት የሚያየዉ መሬት በሙሉ የሚያሳሳና የማይታለፍ ስለሆነበት ያየዉን መሬት በሙሉ ለራሱ ለማድረግ ጓጉቶ ቀኑን ሙሉ ያለምንም ረፍት ያላቅሙ ሲሮጥ ልቡ ከድታዉ በመሞቱ፣ ሁለት ሜትር ባልሞላ መሬት ላይ ቀብሩ ተቆፍሮ ግብአተ መሬቱ ተፈጸመ ይለናል ቶልስቶይ፡፡ለሰዉ ልጅ የሚያስፈልገዉ መሬት ይሄዉ መቀበሪያዉ ብቻ ነዉ ማለቱ ነዉ፡፡

ከያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ቡድን የመሬት ስስት በስተጀርባ ሞት አድፍጧል!! እንደ ቶልስቶዩ ገጸ ባህሪ በመሬት ስስት ጉምዥት ላሃጫቸዉን እያዝረበረቡ ያሉ የብሄር ጠበቃ ነን ባዮች ግን ከመሬት ስስታቸዉ ጀርባ ያደፈጠዉን ሞት ለማየት ፈጽሞ አልቻሉም፡፡

እና እኔም በቶልስቶይ መንገድ ሄጄ ለአንድ ብሄር ምን ያህል መሬት ይበቃዋል ስል ለመጠየቅ ተነሳሁ፡፡ለነገሩ እኔ ብቻ ሳልሆን የብሄራችን ተቆርቋሪ ነን ብለዉ የሚያስቡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖችም ይሄን ላንድ ብሄር ምን ያህል መሬት ይበቃዋል የሚለዉን ጥያቄ ሽህ ጊዜ ደጋግመዉ ራሳቸዉን ሊጠይቁ ይገባል፡፡እነዚህ የየብሄሩ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች የእነርሱ ብሄር ምን ያህል ስኩየር ኪ.ሜ መሬት ቢኖረዉ ይሆን በቂ መሬት አለን ብለዉ አርፈዉ የሚቀመጡት? እዉነት ግን አንድ ብሄር ምን ያህል መሬት ቢኖረዉ ይሆን በቃኝ የሚለዉ?

አሁን ካለዉ የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት 284,537.84 ስኩዬር ኪ.ሜ የሚሆነዉን ቦታ የሚወስደዉ የኦሮሚ ክልል ቢሆንም ይሄ ሰፊ መሬት ግን ለኦሮሞ ህዝብ አልበቃዉም ይሉናል የኦሮሞ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች፡፡በኦነግና ጄሌዎቹ ስሌት የኦሮሚያ መሬት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ከዚህም ይገዝፋል፡፡ወሎ፣ጎጃም፣ሸዋ፣…በጠቅላላ የኦሮሞዎች ነዉ፡፡እንደ ኦነጎች አመለካከት የኦሮሞዎች ያልሆነ መሬት ኢትዮጵያ ዉስጥ ተፈልጎ አይገኝም፡፡ የኦነግ የግማሽ ክፍለ ዘመን መዝሙርም የሚለዉ ይሄንኑ ነዉ፡፡jaalatus jibbitus abban biyyaa oromoodha!! (ጃለቱስ ጂቢቱስ አባን ቢያ ኦሮሞዻ!!) ወደድሽም ጠላሽም አገሩ የኦሮሞዎች ነዉ!!

የአፋር ክልላዊ መንግስት 72,052.78 ስኩየር ኪ.ሜ ቢሸፍንም፣ አንዳንድ የአፋር ሽማግሌዎች ግን የአፋር ግዛት አሁን ያለዉ ብቻ አልነበረም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡አፋሮች በኦሮሞዎችና በሱማሌዎች በኃይል እየተገፉ መጥተዉ አሁን ያሉበት ቦታ ላይ ተወስነዉ ለመቅረት ቢገደዱም የአፋሮች ግዛት ግን ከአሁኑ ጋ ሲነጻጸር እጅግ በጣም ሰፊ ነበር ይላሉ አዛዉንቶቹ፡፡በአፋር ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተዘጋጀዉ አፋር በታሪክ አምድ በተሰኘ መጸሃፍ ላይ የአፋር መልክዓ ምድራዊ ወሰኖች በሁለት ገልፍ (ባህረ ሰላጤዎች) እንደሚዋሰንና አንደኛዉም ገልፍ ከዙላ ጀምሮ እስከ ታጁራ ያለዉን የጅቡቲን አልፎ እሰከ ሱማሌ እንደሚደርስ ይገልጻል፡፡እስከ 20ኛዉ ምዕተ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የአፋር ወሰን ዜይላ ድረስ ይደርስ እንደነበር ይሄዉ መጸሃፍ ያትታል፡፡

ሶማሌችም ከዚህ በላይ የጠቀስነዉ የአፋሮች የቀድሞ ግዛት ታሪክ የእነሱ እንደነበር ሽንጣቸዉን ገትረዉ ይከራከራሉ፡፡የሶማሌ ክልላዊ መንግስት 279,252 ሰኩየር ኪ.ሜ የቆዳ ስፋት እንዳለዉ ቢታወቅም ይህ ሰፊ መሬት ግን አላረካዉም፡፡አሁን የፈራረሰችዉ ሶማሊያ መሪ የነበረዉ ዚያድ ባሬ የሶማሌ ድንበር አዋሽ ሰባት ኪሎ ድረስ ነዉ ብሎ ተነስቶ ይህንኑ ሃሳቡን እዉን ለማድረግ ጦር ማዝመቱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነዉ፡፡

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት 53,638 ስኩየር ኪ.ሜ ስፋት አለዉ፡፡ Ethiopian government portal ላይ ያገኘሁት መረጃ የክልሉን የቆዳ ስፋት ወደ 80000 ከፍ ያደርገዋል፡፡የ1968 የህወሃት ማኒፌስቶ የትግራይ መሬት በደቡብ ኣላዉሃ፣በሰሜን መረብ ሲያካልሉት፣ በምእራብ በኩል ደግሞ ወልቃይትና ጸለምትን ያካትታል ሲል ይገልጻል፡፡ጥቂት የማይባሉ የትግራይ ምሁራንም የትግራይ የቆዳ ስፋት ይህ ብቻ እንዳልሆነ በየአደባባዩ ሲከራከሩ ይሰማል፡፡በ18ኛዉ ክፍለ ዘመን ትግራይ አሁን ካላት ስፋት አምስት እጥፍ ትገዝፍ እንደነበር ምለዉ ተገዝተዉ የሚናገሩት እነዚህ የትግራይ ልሂቃን  እስካሁን ወደ ትግራይ መጠቃለል የነበረባቸዉ ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ያልተጠቃለሉ ቦታዎች ጎንደርም ወሎም ዉስጥ በብዛት እንዳሉ አጽንዖት ሰጥተዉ ይናገራሉ፡፡ከ1943 እስከ 1948 ዓ.ም ባለዉ ጊዜ ዉስጥ የቀዳማይ ወያኔን አመጽ ተከትሎ፣ አጼ ኃይለስላሴ ትግራይን ለማዳከም በማሰብ ራያና የምእራብ ትግራይ ቦታዎችን በወሎና በጎንደር ክፍለ ሃገር እንዲካተቱ ያደረጉት ሆን ብለዉ ነዉ ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

እንደነዚህ ልሂቃን አባባል ያኔ የነበረዉ የትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አሁን ካለዉ አምስት እጥፍ የሚተልቅ ከነበረ፣ የትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት 268,190 ስኩየር ኪ.ሜ ይሆን ነበር ማለት ነዉ፡፤ይሄም በኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉ 9 ክልሎች ትግራይ ኦሮሚያንና የሶማሌ ክልልን በመከተል በቆዳ ስፋት በሶስተኝነት ለመቀመጥ ያስችለዉ ነበር፡፡

ለአብነት ያህል ከላይ ያሉትን ጥቂት ብሄሮች አነሳን እንጂ፣ የሁሉንም ብሄሮች የልብ ትርታ ለማዳመጥ ብንታደል የሁሉም ህዝብ (ብሄር) ፍላጎትና ስሜት ተመሳሳይ ነዉ ብሎ መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ባለዉና በተሠጠዉ ነገር ረክቶ የማያዉቅ ፍጡር ቢኖር የሰዉ ልጅ ብቻ ነዉ፡፡የሰዉ ልጅ ፍላጎት የትየለሌ ነዉ፤ድምበር የለዉም፡፡ዛሬም ነገም ተጨማሪ ይፈልጋል፡፡ልብን በማስተዋል ካልገሩትና በቃኝን ካላስተማሩት የሰዉ ልጅ ፍላጎት ፈጽሞ አይጠረቃም፡፡ የቶልስቶዩ ገጸ ባህሪ ለሞት የዳረገዉ ይሄዉ ገደብ የለሹ የመሬት አምሮቱ ነበር፡፡

አንድ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል እዉነት ያለ ይመስለኛል፡፡እንደ እንጉዳይ አሁን ያለበት ቦታ ላይ በቅሎ የተገኘ ብሄር ወይም ህዝብ የለም፡፡የሰዉ ልጆች ያለፈ ታሪክ በእንቅስቃሴ የተሞላ ነዉ፡፡በፍልሰት የተሞላ ነዉ፡፡እንደ አሁኑ ሃገሮች በጠንካራ ድንበር ሳይታጠሩ በፊት ጀምሮ ህዝቦች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የተፈጥሮ ሃብት ፍለጋ በቡድን ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ለእኛ ቅድመ አያቶች ደግሞ ሃብት ማለት ከግጦሽ መሬትና ከዉሃ እምብዛም የዘለለ አልነበረም፡፡

የአያት የቅድመ አያቶቻችን እግር የረገጠዉን መሬት በሙሉ “ለኔ ብቻ ይገባኛል” ማለት ከጀመርን መዘዙ ብዙ ነዉ፡፡፡የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ከተነሳ፣ ወደ ኋል ተጉዘን የታሪክ መዛግብትን ካገላበጥን ጉድ መፍላቱ አይቀርም፡፡ዛሬ የኛ ነዉ ብለን የተኮፈስንበት መሬት የዛሬ መቶ ዓመት፣ሁለት መቶ ዓመት፣ሶስት መቶ ዓመት፣አራት መቶ አመት……… የእኛ እንደነበር ማን በርግጠኝነት ይናገራል?ዛሬ የኦሮሞ መሬት የተባለዉ ከሁለት ክፍለ ዘመን በፊት የሃዲያዉ፣የሲዳማዉ፣የሶማሌዉ፣የአማራዉ…..መሬት እንዳልነበር ማን በርግጠኝነት መናገር ይችላል?

መሬት የአንድ ብሄር ንብረት ብቻ ተደርጎ መወሰዱ እስካልቀረ ድረስ ሠዎች በሰላምና በፍቅር አብረዉ ለመኖር መቸገራቸዉ አይቀርም፡፡የማህትማ ጋንዲን ዝነኛ አባባል እዚህ ላይ ልጥቀስ “መሬት የሁሉንም ሰዉ ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል በቂ ሃብት አላት፤ የሁሉንም አልጠግብ ባዮች ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል በቂ ሃብት ግን የላትም”፡፡ አዎ ኢትዮጵያም የዜጎችዋን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል ከበቂ በላይ መሬት አላት፡፡በፍቅርና በመተሳሰብ ከኖርን ሁመራ ላይ ያለዉ መሬት ለአማራና ትግሬ ብቻ ሳይሆን ለሌላዉም ኢትዮጵያዉያን በቂ በሆነ ነበር፡፡ግና የስግብግብ ጠባብ ብሄርተኞች አልጠግብ ባይነት ይሀ እዉን እንዲሆን ማድረግ አላስቻለም፡፡    

እንደ ቶልስቶዩ ገጸ ባህሪ በመሬት ስስት ጉምዥት ላሃጫቸዉን እያዝረበረቡ ያሉ የብሄር ጠበቃ ነን ባዮች ከመሬት ስስታቸዉ ጀርባ ያደፈጠዉን እልቂት ዛሬ ላይ ቆመዉ ማየት ቢችሉ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ምንኛ በታደሉ ነበር?!!

(የየክልሎቹ የቆዳ ስፋት የተወሰደዉ ከ wikipidia ነዉ፡፡)

 

Filed in: Amharic