>

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዳኛቸው ይልማ - የማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መሥራች)

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

ጉዳዩ:-የመምህራን ምልመላና ስልጠና 

ትምህርት የዕድገት መሰረት መሆኑ  እሙን ነው:: በትምህርት ሂደት ደግሞ ዋናው ተዋናይ መምህሩ ነው::
ከ1966 ዓም በፊት መምህር ለመሆን የምርጦች ምርጥ መሆንን (cream of the cream) ይጠይቅ ነበር:: በዚህም መሰረት ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ይገቡ የነበሩት ከየትምህርት ቤቶቻቸው የላቀ ውጤት ያመጡት ነበሩ:: መምህራኑም ከተማሪዎቻቸው አልፈው ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጭምር አርአያ (role models) ነበሩ:: ለዚህም ነው “የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ አገባሽ አስተማሪ” ተብሎ ይዘፈን የነበረው::
በሁዋላኛው ዘመን ግን መምህሩ መኩሪያንሳይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደረሰ:: በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ እርስዎ ተወልደው አድገው የተማሩበትን አካባቢ ጨምሮ የትምህርት ጉዳይ ኃላፊነት ይመለከተኝ ነበር:: በወቅቱ አያሌ የመንግሥት ት/ቤቶች እየተዘጉ የጣሪያቸው ቆርቆሮ እየተነቀለ በመወሰዱ ወደኅብረተሰቡ ተጠግቼ ችግሩን ለማጥናት እንቅስቃሴ ባደረግሁበት ጊዜ አንድ አዛውንት የነገሩኝን ልብ ይሏል:: የተበጣጠሰ ሸበጥ የተቀደደ ሱሪ የለበሰ በእጁ  ጫትና ሲጃራ ወደያዘ ግለስብ እያመለከቱ “ልጆቼ እንደእርሱ ከሚሆኑ ቁራን ቀርተው በሞራል ታንፀው ቡናዬን ቢያለሙልኝ ይሻላል ትምህርት ቤት ሄደው ጊዜያቸውን አቃጥለው መጨረሻቸው እንደእርሱ ከሚሆን::” አሉኝ::

ላለፉት 27 ዓመታትም የመምህሩ ጉዞ ከድጡ ወደማጡ ነው የሆነው:: ወደመምህራን ማሰልጠኛ የሚገቡት አመልካቾች በማንኛውም መመዘኛ ወደቀ/ች የሚያሰኝ ውጤት ማለትም ሴቶች 1.2/4.00: ወንዶች 1.4/4.0 በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ያመጡ ናቸው:: ከላይ አዛውንቱ በገለፁት ዓይነት መምህር ተብዬ መዘጋጀታቸው ሳያንስ የነገውን የአገር ተስፋ ሊሆን የሚችለውን ትውልድ በለጋ ዕድሜው(formation age) ሊኮተኩቱት ቀርቶ ሊያጣምሙት የሚችሉ ተገቢ ሥልጠናና ክህሎት የሌላቸው ዜጎች ናቸው ዛሬ ለመምህርነት የሚታጩት:: በእርግጥ ነው ከመከከላቸው አንዳንድ ጎበዞችም በሁኔታዎች አለመመቻቸት ውጤታቸው ዝቅ ብሎ ለመምህርነት የበቁና መልካም አፈፃፀም ያላቸው እንደማይጠፉ እሙን ነው::

ከዚህ በተጨማሪ የመምህርነት ሙያ ካለበት ከባድ ኃላፊነት አኳያ ተገቢውን ጥቅም የማያስገኝ መሆኑ ጎበዞችና በሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ላይ ልዩነት ሊያመጡ የሚችሉ ዜጎች መምህርነት ቀዳሚ ምርጫቸው አይደለም::
ስለሆነም የአገራችን ኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል በአስተማማኝ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለመምህራን ትምህርትና ሥልጠና በኣፋጣኝ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ጊዜው አሁን ነው:: የባከነው ጊዜም መካካስ የሚችለው ይህ ሲሆን ብቻ ነው::

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ይህንን መልዕክት የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ በነበርኩበት ወቅት  ኅዳር 21 ቀን 2000 ዓ.ም ለተከበሩ የወቅቱ ጠ/ሚኒስትር ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ኣሳስበናቸው ነበር:: ሃሳቡን የገዙት መስሎን የነበረና ማስተካከያም እንደሚያደርጉ ቃል ሰጥተውን የነበረ ቢሆንም  በተግባር ግን አልታየም::

ስለዚህ ኢትዮጵያችንን እርስዎ ወዳለሙላት ደረጃ ለማድረስ ሊቀድሙ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ስለሆነ ይህንን አስረግጠው በተግባር የሚያውሉበትን ዕለት እናፍቃለሁ::

አክባሪዎ

ዳኛቸው ይልማ

የማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መሥራች

Filed in: Amharic