>
5:14 pm - Thursday April 20, 2558

የዐብይ አሕመድ አገዛዝ ወደ አፓርታይድነት እየተቀየረ ነው! (አቻምየለህ ታምሩ)

የዐብይ አሕመድ አገዛዝ ወደ አፓርታይድነት እየተቀየረ ነው!
አቻምየለህ ታምሩ
የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ሕጋዊ ምርመራ ሳያካሂድና  በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያልተባሉ ንጹሐ ዜጎችን   እንደከብት ከየመንገዱ እየለቀመ  በማሰር የለየለት አገዛዝ ሆኗል። ትናንትና ዛሬ ደግሞ  የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ከአገዛዝነት ወደ አፓርታይድነት እየተቀየረ እንደሆነ የሚያሳይ እርምጃ በሰላማዊ ዜጎች ላይ  ወስዷል።
በትናንትናው እለት ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉና ቁጥራቸው ያልታወቀ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታስረው በዛሬ እለት ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ለማወቅ ተችሏል። ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ የቀረበበት ክስ «አዲስ አበባ በራሷ ልጅ ትተዳደር ብለሃል» የሚልና «የአዲስ አበባን  ወጣቶች እያደራጀህ ነው» የሚል ነው። ይህ ማለት  ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉና ሌሎች የአዲስ አበባ ልጆች  በትናንትናው እለት በፖሊስ የታሰሩት አዲስ አበባ በራሷ ልጆች ትተዳደር በማለታቸውና የአዲስ አበባን ልጆች ማደራጀታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው ነው።
የሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(2) አዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንደሚኖረው ይደነግጋል። እነ ሄኖክ  አክሊሉ ግን የታሰሩት በሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(2)  የተቀመጠውን መብት በመጠየቃቸውና  አዲስ አበባ የአዲስ አበቤ ትሁን ለምን ትላላችሁ  ተብለው ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት በበቀለ ገርባ የሚመሩ አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች  «አዲስ አበባ  ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም የኦሮምያ አካል ስለሆነች»  የኦሮምያ አካል ለማድረግ እንደሚታገሉ መግለጫ አውጥተው ነበር። የሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(5) ግን አዲስ አበባ የኦሮሞያ አካል ናት አይልም። በሌላ አነጋገር እነ በቀለ ገርባ  አዲስ አበባ  ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም የኦሮምያ አካል ናት ያሉት  የሕገ መንግሥት ተብዮውን  አንቀጽ 49(5) ተላልፈው ነው።
እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ፍትሕ ካለ በወንጀል ተጠርጥሮ መታሰር ያለበት  በሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(5) ላይ የተቀመጠውን በመተላለፍ «አዲስ አበባ  ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም የኦሮምያ አካል ናት» ያሉት እነ በቀለ ገርባ እንጂ  በሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(2)  የተቀመጠውን «አዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን አለው» የሚለውን «ሕገ መንግሥታዊ» መብት የጠየቁት እነ ሄኖክ አክሊሉ መሆን የለባቸውም! እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። በሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(5) ላይ የተቀመጠውን የተላለፉት እነ ኦቦ በቀለ በሰላም እየኖሩ  ሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(2) ላይ የተቀመጠው ይከበር ያሉት እነ ሄኖክ አክሊሉ ታስረዋል።This looks like apartheid, walks like apartheid, behaves like apartheid; it’s apartheid!
ሌላው በሄኖክ አክሊሉ ላይ የተመሰረተው ክስ የአዲስ አበባን ወጣት እያደራጃችሁ ነው ተብለው ነው። የሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 31 «ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው።» ይላል። ባለፈው ቅዳሜም አዲስ አበባ የምንኖር  የኦሮሞ ተወላጆች ነን ያሉ ሰዎች  «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚል ማኅበር ለማቋቋም የምሥረታ ውይይት ማድረጋቸውን  ውይይቱን  የዘገበው የኦ.ኤም.ኤን ጣቢያ አስታውቋል። «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚል ማኅበር ለመፍጠር የአዲስ አበባ ኦሮሞዎች እንዲደራጁ ተፈቅዶ የተቀሩት የአዲስ አበባ ተወላጆች ለመደራጀት ሲንቀሳቀሱ የሚታሰሩ ከሆነ ይህም ሌላኛው አፓርታይድ ነው።
ሶስተኛው በዐቢይ አገዛዝ እየታየ ያለው  የአፓርታይድ ምልክት በሲዳማ፣ በወላይታ፣ በጉራጌና እና በቀቤና የዞንና የወረዳዎች የበላይ አመራሮች ላይ የወሰደው አቋምና ቡራዩና ሻሸመኔ ላይ የተካሄደውን የዘር ጥቃት ተከትሎ ያሳየው አድሏዊነት ነው።  እንደሚታወቀው ዐቢይ አሕመድ በደቡብ ክልል  የተካሄደውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና እና ቀቤና ዞንና ወረዳዎች የበላይ አመራሮች በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን እንዲለቁ ጠይቆ ነበር። ሆኖም ግን ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ በቡራዩና በሻሸመኔ ሲካሄድ በሲዳማ፣ በወላይታ፣ በጉራጌና እና በቀቤና ዞንና ወረዳዎች የበላይ አመራሮች ላይ ያሳየውን አቋም ማሳየት አልቻለም። ይህ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው። ዞሮ ዞሮ ይህም  ያው የዘር መድሎ ወይንም አፓርታይድ ነው። ወያኔን የአፓርታይድ አገዛዝ እንለው የነበረው በሌላው ላይ የሚፈጽመውን የራሴ በሚላቸው የወርቅ ዘሮች  ላይ ባለማድረጉ ነበር።
ስለዚህ የዐቢህ መንግሥት ልክ እንደ ፋሽስት ወያኔ የአፓርታይድ አገዛዝ ሁሉ የአፓርታይድ አገዛዝ ለመፍጠር መንገዱን እያጋመሰው ነው ማለት ነው። ምክንያቱም በሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(5) ላይ የተቀመጠውን የተላለፉት እነ ኦቦ በቀለ በሰላም እየኖሩ  ሕገ መንግሥት ተብዮው አንቀጽ 49(2) ላይ የተቀመጠው ይከበር ያሉት ከታሰሩ፤ የአዲስ አበባ ኦሮሞዎች «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚል ማኅበር እንዲፈጥሩ ተፈቅዶ የተቀረው የአዲስ አበባ ተወላጅ ግን የአዲስ አበባ ማኅበር ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የአዲስ አበባን ወጣቶች እያደራጃችሁ ነው ተብሎ የሚታሰር ከሆን ይህ ግልጽ የሆነ የዘር መድሎ ነው። ይህ ደግሞ አፓርታይድ ነው። ምክንያቱም It  looks like apartheid;  it walks like apartheid; it  behaves like apartheid; it’s apartheid!
Filed in: Amharic