>

የእፍርታምነት የልጅነት ጨዋታ አይነት .... (ኤሊያስ ገብሩ ጎዳና)

የእፍርታምነት የልጅነት ጨዋታ አይነት ….
ኤሊያስ ገብሩ ጎዳና
——-
ትናንት የታሰሩት አቶ ማይክል መላክ (ማይክ) እና ሄኖክ አክሊሉ (ጠበቃ) ከታች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ከታች በተጠቀሱት ሶስት ጉዳዮች ተጠርጥረው መታሰራቸውን ሰማን። የተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ በፖሊስ ተጠይቆባቸዋል፤ ፍርድ ቤቱም ፈቅዷል። ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድጋሚ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ማለት ነው።
1.የአዲስ አበባን ወጣት ማደራጀት፣
2.”አዲስ አበባን የክልል ሰው አይመራትም” በማለት ቅስቀሳ በማድረግ፣
3.”ከፍልስጤም ኢምባሲ  ጋር መገናኘትና ሥልጠና መውሰድ” በሚል።
1. በኢትዮጵያ መደራጀት እንደወንጀል የሚቆጥረው በየቱ የህግ አንቀጽ ይሆን? ወይስ መደራጀትን በህግ የሚከለክል አዋጅ በድብቅ ወጥቷል? …ህግ ስለሚፈቅድ አይደለም እንዴ ክልል ተኮር የፓለቲካ ድርጅቶች ጭምር የተመሰረቱትና እየተመሰረቱ የሚገኙት?!
2. “አዲስ አበባን የክልል ሰው አይመራትም” በማለት ቅስቀሳ ማድረግ [ከተደረገም]” እንዴት በወንጀል አስጠርጥሮ ያሳስራል?!  …ሰው ያመነበትን ለመናገር፤ ትናንት የህወሃትን ዛሬ የኦህዴድን ሰዎችን ያስከፋል አያስከፋም ብሎ ራሱን ሴንሰር ማድረግ ሊኖርበት ይሆን? …
አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ “የጠመንጃ ትግል ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ነው። ብርሃኑ ነጋ እኔን ገድሎ ስልጣን መያዝ፣ እኔም እሱን ገድዬ ስልጣን ላይ መቆየት ጊዜ ያለፈበት ፋሽን ነው።  አሁን የሚያስፈልገን የሀሳብ ትግል ነው” ሲሉ የከረሙት ውሸት ነው ማለት ነው?! ህምምም
 …አንድ ሰው/ቡድን/ድርጀት … “አዲስ አበባን የክልል ሰው አይመራትም” በማለት ሀሳቡንና እምነቱን በምክንያት በተለያየ መንገድ ለአደባባይ ቢያቀርብ፤ ይኼ ያልተዋጠለትና ያላመነበት ሰው/ቡድን/ድርጅት ደግሞ፤ “አዲስ አበባን የክልል ሰው ይመራታል” በማለት ሀሳቡንና እምነቱን በምክንያት ለአደባባይ በማቅረብ መሞገት ይችላል። የሀሳብ ትግል እንዲህ ነው!  ከትግሉ በኋላ በሰፊው ህዝብ ቅቡልነት ያገኘው ሃሳብም ያሸንፋል።
ከዚህ ውጪ፡- ለወቅቱ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ሰዎች ያልጣማቸው ሀሳብ ስለተቀነቀነ ብቻ፤ “ጊዜው የእኛ ነው። ‘ሥልጣን’ም አለኝ …” በሚልና የበታችነት ስሜት በወለደው ስንኩል ብሎም ክፋ እሳቤ ተነሳስቶ ንጹሃንን እንደጥጃ እያንጠለጠሉ ማሰር የአስተሳሰብ ልምሻነት ነው፤ የሀሳብ ቀንጨራነትን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ሳይጀምሩ ተሸናፊ መሆንንም ጭምር!
 …ሃሳብ አለኝ ካሉ፤  ሀሳብ ማቅረብ፣ በሀሳብ መወያየት፣ መከራከርና መሟገት መቻል ነው – ከቻሉ እስከጥግ ድረስ! አሊያ፣ የሀሳብ አቅምን በማወቅ አርፎ መቀመጥ ብልህነት ይሆናል።
3.”ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር መገናኘትና ስልጠና መውሰድ” እንዴት ወንጀል ሊሆን ይችላል? …ኤምባሲው ወንጀለኛ ነው ማለት ነውን? ከሆነ ለምን ሆነ? መቼስ ሆነ? በግልጽ ነው በስውር?
..ለምሳሌ፣ ከአሜሪካ ኤምባሲ፣ ከእንግሊዝ ኤምባሲ፣ ከጀርመን ኤምባሲ፣ ከኤርትራ ኤምባሲ፣ ከእስራኤል ኤምባሲ፣ ከኬኒያ ኤምባሲ፣ ከሱዳን ኤምባሲ፣  …ጋር መገናኘትና ስልጠና መውሰድ በወንጀል ሊያስጠይቅ ነው ማለት ነው?! …እንዲህ ከሆነ፣ በዋነኝነት መጠየቅ ያለበት እራሱ ገዥው ሃይል አይሆንምን?!
…አሁንም ድረስ፤ “ኢህአዴግ ሲያደርገው ጽድቅ፣ ሌላው ሲያደርገው ኩነኔ” አይነት አስተሳሰብ ላይ ተቸንክራችኋል ማለት ነውን?!
..ይኼ ደግሞ  “እኔ ብቻ አሸነፊ” አይነት ከሆነው፤ የልጅነት የእፍርታምነት ጨዋታ ጋር ይመሳሰላል። በእፍርታምነት ደግሞ ሁሌ አሸናፊነትን መቀዳጀት የለም! ያ የምትክደው ሰው/ቡድን/ ሃይል፣ እያየኸው ያወርድሃል!
Filed in: Amharic