>
5:13 pm - Sunday April 19, 2240

ለታዬ ደንደአ:-  አዎ!... ፍትህ ላይ አሻጥር አይሰራም!!

ለታዬ ደንደአ 
   
አዎ!… ፍትህ ላይ አሻጥር አይሰራም!!
ብርሀኑ ተክለአረጋይ
ለመሆኑ የአዲስ አበባ ህዝብ ወገንተኛ ሆኖ የሚያውቀው መቼ ነው? የአዲስ አበባ ህዝብ አንተን ጨምሮ ይፈቱ ብሎ ያልጮኸው? ለኦሮሚያ ወንድሞቹ በብርድ እየተንቀጠቀጠ ዳቦና ውሀ ሲያቀብል የነበረ ወጣትስ “ወገንተኛ”  መባል ነበረበት…
 ወዳጄ ሰላም ከመሆን አልፈህ ሰላም አስከባሪ መሆንህንም በፌስቡክ ብቅ ብለህ እየነገርከን ነውና
በሰላምታ ጊዜህን አላጠፋም ጓዴ እኛ ግን ሰላም አይደለንም ወንድሞቻችን ታስረውብናል ጓደኞቻችን ተገድለውብናል ጠዋት ሱሰኛ ማታ ደግሞ ሌባ እየተባልን እንሰደባለን በቃ ከፍቶናል አንዱ በገጀራ ሲስተን ሌላው በጥይት ሲቀልበን በአደባባይ በጅምላ ታፍሰን አንዱ “እየተማሩ ነው” ሌላው “እያለቀሱ ጥፋታቸውን አምነዋል” ሲለን እንደ ድፎ ዳቦ በዘረኞችና በግልብጥ አሳሪዎች መሀል እየተለበለብን እንገኛለን
 ጓዴ ይህን ፅሁፍ ስፅፍልህ የኔም ያንተም ጠበቃ የነበረው ጠበቃ ሄኖክ ታስሯል ፊት ለፊቴ እጁ ከሌላ ሰው ጋር በካቴና ተጠፍሮ ፖሊሶች በመሳሪያ አጅበውት ቆሟል ያሳዝናል ዛሬም ከታሪክ የማይማሩ አንባገነኖች ፍትህን ከአፈሙዝ ስር ለማድረግ እየጣሩ ነው ይህ ጥረታቸውም እፍረተ ቢስ አድርጎአቸው በሀገራችን ፍትህ ሰፍኖ ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር ትፈጠር ዘንድ እገዛ የሚያደርገውን የህግ ባለሙያ ወጣት እስከማፈን አድርሷቸዋል ሄኖክ የህግ ባለሙያ ብቻ አይደለም ህጋዊም ጭምር ነበር እንዳንተ የፍትህ ተቋም ባለስልጣናት ሆነው በፌስቡክ እንደ ኮማሪት ሲሳደቡና ፍትህን ረግጠው ሲያስፈራሩ የሚውሉ ሰዎች ባሉባት ሀገር  እንደሄኖክ አይነት ህግን ከማወቅ በላይ የሚያከብሩ ሰዎችን ማግኘት ብርቅ ነው ታዲያ እኔም አንተም በውሸት ክስ ፍርድ ቤት ቀርበናል ባልን ጊዜ ከጎናችን ቆሞ አሳሪዎቻችንን የሞገተ ትንታግ የህግ ባለሙያ ያለምንም ወንጀል በካቴና ተጠፍሮ ከማየት በላይ አሳዛኝ ነገር ይኖር ይሆን?
    ጓዴ በቅርቡ በተፈጠረው አለመረጋጋት እነሱው በገጀራ ተመተው እነሱው በጥይት ተመተው “ባላባት ባጠፋ ባላገር ይካስ”ብሂል የተፈፀመባቸው ለቆንጨራ ታጣቂ “ጀግኖች” እንኳን የተፈቀደውን ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት ተነፍገው በጦላይ    ወታደራዊ ካምፕ በስቃይ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በተመለከተ የተደረገውን ማህበራዊ ዘመቻ አስመለልክቶ በፃፍከው ፅሁፍ “ስለ ሌሎችም ወገኖች ማሰብ ያስፈልጋል ማዳላት ያስተዛዝባል” በማለት ዘመቻው ወገንተኛ ነው የሚል ምስል ለመሳል ሞክረሀል ለመሆኑ የአዲስ አበባ ህዝብ ወገንተኛ ሆኖ የሚያውቀው መቼ ነው?
የአዲስ አበባ ህዝብ አንተን ጨምሮ ይፈቱ ብሎ ያልጮኸው ነው? ለኦሮሚያ ወንድሞቹ በብርድ እየተንቀጠቀጠ ዳቦና ውሀ ሲያቀብል የነበረ ወጣትስ “ወገንተኛ”  መባል ነበረበት?ደግሞስ አንድ ቀን እንኳን ፍርድ ቤት ቀርበው ቀጠሮ ያልተቀጠረባቸውንና ፖሊስ በማሰቃያ ካምፕ ያጎራቸውን ወጣቶችስ “ተጣርቶ ሊለቀቁ ነው” ማለትስ ከፍትህ ባለሙያ የሚጠበቅ ገለልተኛ ሀሳብ ነው?
ግድ የለህም ወዳጄ ከሌሎች ተቋማት በላይ ገለልተኝነት በሚጠይቀውና በገለልተኝነት ለፍትህ ብቻ መወገን ባለበት መዋቅር ውስጥ ባለስልጣን ሆኖ በፌስቡክ ሲሳደቡ መዋል አያዋጣም ወንጀልም ነውርም ነው ለተረኛ አንባገነንነት አልታገልንም እኔ እስከሚገባኝ ዴሞክራሲ ማለት “ሌሎች በአንተ ላይ እንዳያደርጉብህ የምትፈልገውን አንተም በሌሎች ላይ አታድርግ” ማለት ነው ሁሉም አለኝ የሚለው ንዴት ስሜትና ግለት ሌላውም ጋር እንዳለ ማሰብ ተገቢ ነው መብት አንፃራዊ አይደለም አንዱ ሲጠይቅ ጀግና ሌላው ሲጠይቅ ጀዝባ አንዱ ሲደራጅ ሀሮምሳ ሌላው ለመደራጀት ሲሞክር ቦዘኔ የሚባልበት ምክንያት የለም እናም ወዳጄ እባክህ “አዲስ ግልብጥ አንባገነንነት”ህን ትተህ ከፍትህ ጎን ብቻ ቁም እንደምታውቀው በፍትህ ላይ አሻጥር አይሰራም ያለዚያ…… እዛም ቤት እሳት አለ!!!
Filed in: Amharic