>
5:13 pm - Saturday April 19, 8070

አገሬ በቂ ቂም አላት !  (ዳንኤል ክብረት)

አገሬ በቂ ቂም አላት !
 ዳንኤል ክብረት
            
* ” መንግሥታዊ ስሜታዊነት ከስሕተት ወደ ጥፋት መሸጋገርን ያስከትላል ” 
ከአዲስ አበባ ተወስደው ‹ጦላይ› አሉ የሚባሉት ወጣቶች ጉዳይ ለውጡን ከማጠልሸት ያለፈ ጥቅም የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ መንግሥት የሚመሰገነው ታጋሽና ሆደ ሰፊ ሆኖ ለሕግና ለሕጋዊ ሥርዓት ብቻ ሲቆም ነው፡፡ መንግሥታዊ ስሜታዊነት ከስሕተት ወደ ጥፋት መሸጋገርን ያስከትላል፡፡ ለመሆኑ ወጣቶቹን ወደ ጦር
ማሠልጠኛ ጣቢያ ለመውሰድ ወሳጁ አካል ሕጋዊ ሥልጣን።አለው? ክስ ሳይመሠረት የፈለገው ያህል ጊዜ እንዲያስቀምጥ ማን አሠለጠነው? የትምህርት ሚኒስቴርን ሥልጣን ወስዶ ሥልጠና እንዲሰጥ ለፖሊስ ማን ፈቀደለት? የሥልጠናውን ካሪኩለም ማን ይሆን ያጸደቀው? አንድ ሰውስ ሳይፈቅድና ሳይመዘገብ እንደ ብሔራዊ ውትድርና ዘመን በግድ ለመሠልጠን ይገደዳል? የልጆቹ ጤና፣ ነጻነት፣ መብትና የኑሮ ሁኔታ ለምን ከቤተሰብ ተደበቀ? የሰብአዊ መብት ኮሚሽንስ ምነው ዝም አለ? ተፈጠሩ የሚባሉ ስሕተቶችን የማረሚያ መንገዱ በራሱ ስሕተት መሆን የለበትም፡፡
በምንም መልኩ ጨለማን በጨለማ ማብራት አይቻልም፡፡  ማኅበራዊ ቂም የሚፈጠረው በብዙኃን ላይ በሚደረጉ ሕጋዊ ያልሆኑ ተግባራት ምክንያት ነው ፡፡ በአንድ በኩል በታሠሩት ልጆች ላይ፣ ሁለተኛ በቤተሰቦቻቸውና በቅርብ ወዳጆቻቸው ላይ፣ ሲያልፍም ነገሩ በተሠወረብን በእኛ ላይ የሚፈጠረው ማኅበራዊ ቂም እንደሚጋገር እንጀራ እየሰፋ የሚሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ የተፈጠሩ በቂ ቂሞች ስላሏት ተጨማሪ አያስፈልጋትም፡፡ ልጆቹን ልቀቋቸው፤ ጉዳዩንም ዝጉት፡፡
Filed in: Amharic