>

የአዲስ አበባ ወጣቶች በሳምንቱ መጨረሻ ይለቀቃሉ!! (አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን)

የአዲስ አበባ ወጣቶች በሳምንቱ መጨረሻ ይለቀቃሉ!!

 

አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

ከአዲስ አበባ ተወስደው ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚለቀቁ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደግፌ በዲ ለቢቢሲ ገለፁ።

ወጣቶቹ የተያዙት “በጎዳና ላይ ንብረት ሲያወድሙና ሁከት ሲፈጥሩ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ መጀመሪያ ከተያዙት ተጣርቶ አሁን በማሰልጠኛ ያሉት 1174 እንደሆኑ ገልፀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት የፈፀሙት ተግባር በህግ የሚያስጠይቃቸው ቢሆንም መታነፅ እንዳለባቸው በማመን ለዚህም ከቤተሰብና ከማህበረሰብ ቀጥሎ ሃላፊነት ያለበት መንግስት በመሆኑ ይህን ተግባሩን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“ማነፅ ብቻ ሳይሆን የወጣቶቹን ማንነት በመገንዘብ ስራ የሌለው ስራ እንዲሰራ፣ ተማሪውም ትምህርቱን እንዲቀጥል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው እነዚህ ልጆች ላይ ስራ እየሰራን ያለነው”ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ይህን ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ትብብር ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊሶች ወጣቶችን በቡድን ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ስለመለቀቁ ለኮሚሽነሩ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር።

ምንም እንኳ እሳቸው ተንቀሳቃሽ ምስሉን ባይመለከቱትም ቦታው ተገልፆ ትክክለኛ መረጃ ከደረሳቸው ተግባሩን በፈፀሙት አካላት ላይ ተጣርቶ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።

መሳለሚያ ሞቢል አካባቢ ለግንቦት ሰባት መሪዎች አቀባበል ሲደረግ ሰንደቅ አላማ በመስቀልና ባነሮችን በመለጠፍ ይንቀሳቀስ ነበር።

ያሳደጉትና የክርስትና ልጃቸው በአመፅ ሳይሆን የግንቦት ሰባት መሪዎች አቀባበል ላይ ባደረገው ተሳትፎ ከዚያም የቡራዮውን ግድያ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣቱ መታሰሩን አቶ ዘመነ ሞላ ለቢቢሲ ይገልፃሉ።

ከዚህ ውጭ ልጃቸው ሰላማዊ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ያሳደጉት ልጃቸው ወጣት ፍስሃ ደምስ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን እናቱ እንደሌለችና የሚኖረው ከአቅመ ደካማ አያቱ ጋር እንደነበር አቶ ዘመነ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደገለፁት የታሰረው ወደ ቤቱ የሚወስድ መንገድ ላይ አመሻሽ ላይ ነው።መጀመሪያ ወደ ተወሰደበት ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ሲጠይቁ ጦላይ መወሰዱን መስማታቸውንና ከዚያ በኋላ ያለ ምንም መረጃ ቤተሰብ ስቃይ ላይ እንዳለ ይገልፃሉ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ጅምላ የመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። በማህበራዊ ሚዲያው የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ የሚል ዘመቻም በመካሄድ ላይ ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጅምላ አስሮ ስልጠና ማስገባት የህግ አግባብነት እንደሌለው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የህግ ባለሙያና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ መንግስት እነዚህን ወታደሮች አስሮ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመላኩ የጣሳቸው ህጎች አሉ ትላለች።

“ተግባሩ በትንሹ አራት የህገ መንግስቱን አንቀፆች ይጥሳል።የታሰሩ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት ፣ የተጠረጠሩ ሰዎች መብትና ከዚያም ጋር ተያይዞ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች በትንሹ አንድ አራት የህገመንግስቱ አንቀፆች ተጥሰዋል። የወንጀል ስነስርዓት ህጉንም ብንመለከት እዚያ ላይም የተጣሱ ነገሮች አሉ” ትላለች።

እሷ እንደምትለው በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ መንግስት ሰዎችን ሰብስቦ ካሰረ ያሰረበትን ምክንያት ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍቃድ መጠየቅ ይኖርበታል። በወሰደው እርምጃ የቀማው የግለሰቦችን ነፃነት በመሆኑ ይህን ደግሞ ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ ማድረግ አይቻልም።

ስለዚህም ግለሰቦቹን ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣የተከሰሱበትን ምክንያት አለማወቃቸውን እንዲሁም የዋስትና መብታቸውን መነፈጋቸው በሃይማኖትና በዘመድ መጎብኘት አለመቻላቸውን የመሰሉ ነገሮች ሲታዩ በእርምጃው ብዙ የመብት ጥሰቶች እንዳሉ ታስረዳለች።  ምንጭ:- ቢቢሲ አማርኛ 

Filed in: Amharic