>

ፖለቲካችን የስሜት ምርኮኛ መሆኑ ብሔራዊ መተማመን ያሳጣናል!  (ያሬድ ኃይለማርያም)

ፖለቲካችን የስሜት ምርኮኛ መሆኑ ብሔራዊ መተማመን ያሳጣናል! 
ያሬድ ኃይለማርያም
ባለፉት በርካታ አመታት የአገራችን ፖለቲካ ተናዳፊ ስለነበር ብዙዎች መስሎ ማደርን ወይም ዝምታን መርጠው እንዲኖሩ አድርጓል። ጥቂቶች ብቻም ህይወታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ነጻነታቸውንም ጭምር ሰውተው አፋኝ ከሆነው ሥርዓት ጋር ሲተናነቁ ቆይተዋል። ከሥርዓቱ መዳከም ዋዜማ ጀምሮ ደግሞ አብዛኛው በዝምታ ይኖር የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ሲነቃቃ ተስተውሏል። የአገዛዝ ሥርዓቱ በለውጥ ማዕበል ተመቶ ጉልበቱ ከተብረከረከበት እና ተረቶም የነጻነት አየር መንፈስ ሲጀምር ደግሞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በአገሩ ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ መሆን ጀምሯል። ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን አንስቶ በማህበረ ድረ-ገጾችም አዳዲስ የፖለቲካ ተዋናዮችን ማየት ጀምረናል። ይህ አይነቱ የማህበረሰብ መነቃቃት እጅግ የሚበረታታ እና አገሪቱ ለጀመረችው ለውጥም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
በአንጻሩ ብዙ ውይይቶቻችን ከሃሳብ ይልቅ ስሜት፣ ከእውቀት ይልቅ ግምት ወይም መላምት፣ ከመረጃ ይልቅ ተባራሪ ወይም ያልተረጋገጠ የስሚ ስሚ ወሬ፣ ከክርክር ይልቅ ስብከትን፣ ከሃሳብ ነቀፌታ ይልቅ እርስ በርስ ስድድብን ወይም ፍረጃን ያማከሉ ሆነው እየታዩ ነው። አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመርህ፣ ከእውቀት፣ ከህግ፣ ከሞራል እና ከሥነ-ምግባር እየተጣላ በመጣ ቁጥር የስሜት ምርኮኛ ይሆናል። ስሜት ደግሞ በተጋጋመ ቁጥር ወደ ጽንፍ፤ በቀዘቀዘና በረጋ ቁጥር ደግሞ ወደ ዳተኛነት ወይም አድር ባይነት ይወስዳል። በማህበረሰብ ውስጥ ሰዎች በተለይም ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና ሊሂቃን በስሜት ሲነዱ እና ጽንፍ ሲይዙ መደማመጥ እና መከባበር ይጠፋል። ሁሉም ማዶ ለማዶ ቆሞ አድምጡኝ ባይ ብቻ ይሆናል። ሁሉም እራሱን የእውነት እና የትክክለኛነት መለኪያ ወይም ዳኛ አድርጎ ያያል። በነዳጅ ላይ እሳት እንዲሉ በዚህ ስሜታዊነት ላይ ደግሞ አክራሪ የጎጠኝነት ስሜት ሲታከልበት ነገራችን ሁሉ ጸብ ያለሽ በዳቦ ይሆናል። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ማህበረሰብ በጽሞና መወያየትም ሆነ ተወያይቶም መተማመን አይችልም። እንዲህ ያሉት ባህሪያት እየጎሉ እና በሰፊው መስተዋላቸው ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ እርስ በእርስ መተማመንን (Confidence) እንዳይኖር ያደርጋል።
Dominique Moîsi የተባለ ጸሃፊ The Geopolitics of Emotion, How cultures of Fear, Humiliation and Hope are reshaping the world በሚለው ድንቅ መጽሐፉ ውስጥ ስለ ማህበረሰብ ስሜት የጻፈውን ቁምነገር ልጥቀስ፤ “… three primary emotions: fear, hope and humiliation … are closely linked with the the notion of confidence which is the defining factor in how nations and people address the challenges they face as well as how they relate to one another.” ዶሚኒኪው 159 ገጽ በያዘው በዚህ መጽሐፉ አንድ ማህበረሰብ እርስ በራሱ የሚፈራራ ከሆነ፣ አንዱ ሌላውን የሚያጥላላ እና የሚያዋርድ ከሆነ እንዲሁም ሁሉም የጋራ ብሩህ ተስፋ ተጋሪዎች የማይሆኑ ከሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ መተማመን ይጠፋል ወይም አንዱ በሌላው ላይ እምነት ያጣል ይላል።
ይህ አይነቱ አደጋ የተጋረጠበት ማህበረሰብ ልክ እንደ ኢትዮጵያ በጎሣ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት እና በሌሎች ባህላዊ እሴቶች እጅግ የተሰባጠረ ሲሆን ደግሞ እርስ በርስ መፈራራቱ፣ አንዱ ሌላውን ማጠልሸቱ እና አለመተማመኑ ለግጭቶች መንስዔ ይሆናል። የሚፈራራ ማህበረሰብ አንዱ በሌላው ላይ መተማመኛ ያጣል። የተስፋ መሰረቱ ነገ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል የሚል የመተማመኛ መንፈስ ወይም ስሜት በአዕምሮዋችን ውስጥ መኖር ነው። አንዱ ጎሳ በሌላው ላይ ወይም የአንዱ ኃይማኖት ተከታይ በሌላው አማኝ ላይ አብሮ የመኖርና ብሩህ ተስፋ የሚሰንቀው እርስ በራሱ መተማመን ሲችል ብቻ ነው። ከዚያ አልፎ አንዱ ሌላውን ወንጃይ፣ አግላይ፣ አዋራጅ፣ አጠልሺ እና አንኳሳሽ ሲሆነ መተማመን ይጠፋል። ከዚያም በጠላትነት መፈራረጅም ሆነ አንዱ ሌላውን ስጋት አድርጎ መቁጠር ቀላል ይሆናል። በጠላትነት መፈራረጅም ሆነ ጠአትን መጠነቋቆል የጀመረ ማህበረሰብ ወደ አካላዊ ግጭት ለማምራት በቋፍ ነው። ሲጋጭም ጸቡ የሞኝ በትር አይነት ነው። የበርካታ ዘር ተኮር ግጭቶች መንስዔም ይሄው ነው። በሚተማመን፣ በሚከባበር እና የጋራ ተስፋ በሰነቀ ማህበረሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ግጭቶች ከሃሳብ ልዩነት አይዘሉም። ችግሮቻቸውን በንግግር ስለሚፈቱም ወደ አካላዊ ግጭት አይዘሉም።
ወደ አገራችን ፖለቲካ የተመለስን እንደሆነ በማህበረሰቡ መካከል ያሉት ልዩነትን መሰረት ያደረጉት ውጥረቶች እየከረሩ እና እየሰፉ ሲመጡ እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም። ምንም እንኳን የአገዛዝ ሥርዓቱ በሂደት እየተለወጠ ቢሆንም በማህበረሰቡ መካከል ያለው ክፍተት ግን እጅግ እየሰፋ የመጣ ይመስላል። ዛሬ በብሔሮች መካከል ውጥረት አለ፤ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ውጥረት አለ፤ በመንግስት እና በተፎካካሪዎች መካከል ውጥረት አለ፤ በጎሳና በዜግነት ፖለቲካ አራማጆች መካከል ውጥረት አለ፤ በጎሳ ፖለቲካ አራማጆች መካከል ውጥረት አለ፤ በምሁራን መካከል ውጥረት አለ፤ በመገናኛ ብዙሃን እና በጋዜጠኞች መካከል ውጥረት አለ፤ በታሪክ አረዳዳችን ላይ ውጥረት አለ፤ በኃይማኖት ተቋማት መካከል ውጥረት አለ፤ በድህረ ገጽ አምደኞች መካከል ውጥረት አለ፤ በለውጥ አቀንቃኞች መካከል ውጥረት አለ። እነዚህ ውጥረቶች በፈጠሩት ስሜታዊነትም ውይይቶቻችን ሁሉ ወደ መወንጃጀል፣ ስድድብ፣ አሉታዊ ነገሮችን ማጦዝ፣ ግድፈቶችን ማግነን፣ ሃሳቦችን በሃሳብ ከመፈተሽ ይልቅ በዘር መመንዘር፣ ባጭሩ ነገራችን ሁሉ የፍለጠው ቁረጠው እየሆነ ነው።
ዛሬም ሕዝብ በመንግስት ላይ፣ እንደ ግለሰብም እርስ በራሳችን፣ አንዱ ጎሳ በሌላው ላይ፣ አንዱ ኃይማኖት በሌላው እምነት ላይ፣ አንዱ ማህበራዊ ተቋም በሌላው ተቋም ላይ እምነት እንደሌለው የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላላ። ይህ አይነቱ ሁኔታ ደግሞ አገራዊ መተማመን (National Confidence) እንዲጠፋ አድርጓል። ዛሬም ከለውጥ ማግስት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቲም ለማ ላይ ተስፋ ቢያደርግም በመንግስት ላይ ግን እንደ ተቋም እምነት አላሳደረም። ይህ ለውጥ በራሱ በመንግስት አካላት ይደናቀፋል የሚለው ስጋት ዛሬም በሕዝብ ዘንድ እንዳለ ነው። በተለይም የቅርቡ የወታደሮች ከነሙሉ ትጥቃቸው እየተግተለተሉ ወደ ቤተ መንግስት ጎራ ማለታቸው የሕዝብን ጭንቀት ይበልጥ ከፍ አድርጎታል። በቅርቡ በሱማሊያ ክልል፣ በቡራዩ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ የተከሰቱት ዘግናኝ የጎሳ ጥቃቶች የጎንዮሽ ውጥረቱ ይበልጥ አጉልተውታል።
ስሜት የሚሾፍረው ፖለቲካችን ሁላችንንም ሆደ ባሻ እና ግልፍተኛ ያደረገን መሆኑን ለማሳየት በቅርቡ እንኳን በLTV ላይ የተላለፈን አንድ ቃላ ምልልስ መነሻ በማድረግ ሰዎች በጎሳ፣ በፖለቲካ ምልከታ፣ በጽኦታ እና በሙያ ውግንና ጫፍና ጫፍ ቆመው ሲዘላለፉ እና እርባን የሌለው ሙግት ለቀናት ሲያደርጉ ታዝበናል። በራሴ ላይ የገጠመኝን አንድ ጥሩ ምሳሌ ብጠቅስ የስሜታዊነታችንን ልክ ያሳይ ይሆናል። ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ባለበት ጉዳይ ላይ ነገሩ አግባብ አይደለም፤ በአንድ አገር ሁለት ታጣቂ ኃይል ሊኖሮ አይችል፤ በሚል ኦነግ ትጥቁን እንዲፈታ በመሞገቴ አንድ አፍቃሪ ኦነግ ‘አንተ አብን የሚባለው የአማራ ድርጅት ደጋፊ ነህ‘ ብሎ ወቀሰኝ። በማግስቱ የLTV አዘጋጅ የሆነችው ጋዜጠኛ ላይ የደረሰባትን ዝልፊያ እና ተቃውሞ በማውገዝ ነገሩ የጋዜጠኝነት ነጻነት የሚጋፋ ነው እና ሊቆም ይገባል በማለት በመሞገቴ አንዱ የአማራ ብሔረተኛ ነኝ ባይ ‘አንተ የኦነግ አባል ስለሆንክ ነው’ ብሎ ወቀሰኝ። እንግዲህ ለእነዚህ ሁለት ሰዎች ወይም እንደ እነሱ አይነት ተመሳሳይ ምልከታ ላላቸው ብዙዎች ሰኞ አማራ ነኝ፤ ማክሰኞ ደሞ ኦሮሞ። ከእነዚህ አይነት ሰዎች ጋር መወያየት አይቻልም።
የብሄር ድርጅቶች ኢትዮጵያ ሲባል የሚደነግጡ እና የሚረበሹ ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊነትን አቀንቃኝ የሆነው ክፍል የብሔር ጉዳይ ሲነሳ ደሙ የሚንተከተክ ከሆነ፤ ስለ ክርስትና ሲወራ ሙስሊሙ የሚያንቀጠቅጠው ከሆነ፤ ስለ እስልምና ሲወራ ክርስቲያኑ እኔ ተረሳሁ የሚል ከሆነ እንዴት አገራዊ መተማመን ሊፈጠር ይችላል? አማራው ሲሾም ኦሮሞ ካነባ፣ ኦሮሞ ሲሾም አማራው ተገፋው ካለ፣ ትግሬው ሲገፋ ሃዲያው እሰየው ካለ፣ ጉራጌው ሲጠቃ ወላይታው ምን አግብቶችን ካለ፣ አፋሩ ሲገለል ሃረሪው ዝም ካለ እንዴት ሆኖ አገራዊ መተማመን ሊፈጠር ይችላል? አገራዊ ወይም ብሔራዊ መተማመን ባልተፈጠረበት እና እንደውም ክፍተቱ እየሰፋ በመጣበት ሁኔታ ውስጥ የአገር እና መንግስት ግንባታው ሂደት ምን ያህል የተሳካ ሊሆን ይችላል? ለዚህም አንዱ ጥሩ ምሳሌ የኦነግ ባለሥልጣናት ሰሞኑን ከመንግስት ጋር ይቅደረጉት የትጥቅ ‘ፍታ፤ አልፈታም’ ውዝግብ አንዱ የአለመተማመን ጉድለት ማሳያ ነው።
ለማጠቃለል ያህል መንግስት አገራዊ መተማመን (National Confidence) ሊፈጠር በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ቀድሞ ሊሰራ ይገባል። ይህ ካልሆነ በየቦታው እየፈነዳዱ ያሉት የጎንዮሽ ግጭቶች እየሰፉ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጡ ይችላሉ። ይህን አደጋ ለማስቀረት መንግስት፤
– ብሄራዊ የመግባቢያ ጉባዔ ቢያካሂድ እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ቢያደርግ። ጉባዔውም አንድ አገራዊ የመግባቢያ ሰነድ አጽድቆ ቢወጣ።
– በማህበረሰቡ ውስጥ ለግጭት መንስዔ የሆኑ ማናቸውም ጉዳዮች በግልጽ እና በመገናና ብዙሃን ውይይት እንዲደረግባቸው እና ምሁራኖች በጥናት ላይ የተመሰረተ የማስታረቂያ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ቢደረግ።
– በክልሎች መካከል አሁንም ድረስ እየታዩ ያሉ ውጥረቶች እና ፉክክሮች እረገብ እንዲሉ እና ወደ ጤናማ መስመር እንዲመጡ ቢደረግ፤
– መንግስት በብዙ ጉዳዮች ላይ እያሳየ ያለው የድብብቆሽ እና ነገሮችን የመሸፋፈን አዝማሚያ ማህበረሰቡ እርስ በራሱ እንዲጠራጠር እና መንግስት ላይም እምነት እንዲያጣ ምክንያት እየሆነ ስለሆነ ግልጽነት ከወዲሁ ባህል ቢያደርግ።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic