>

መንግስት በወታደር ዘንድ የሚከበር እንጂ የሚደፈር መሆን የለበትም!  (ያሬድ ጥበቡ)

መንግስት በወታደር ዘንድ የሚከበር እንጂ የሚደፈር መሆን የለበትም! 
ያሬድ ጥበቡ
ከተውሸለሸለ የፋና መግለጫ በግልፅ መተንተን አንደሚቻለው፣
1ኛ) ሠራዊቱ ውስጥ ለቀናት ወይም ሳምንታት የተካሄደ ውይይት እንደነበረ
2ኛ) ከእነዚህ ውይይቶች ወታደራዊ የደርግ አባላት መመረጣቸውን
3ኛ) የተመረጡት የደርግ አባላት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ወደ ቤተመንግስት መሄዳቸውን
4ኛ) ይህ ሁሉ ሲሆን የዶክተር አቢይ አስተዳደር በቂ መረጃ እንዳልነበረው
5ኛ) የደርጉ አባላት ቤተ-መንግስት ከደረሱ በሁዋላ በእቅድ ያልተያዘ ውይይት ከመንግስት ቁንጮ አመራሮች ጋር እንዲደረግ ማስገደዳቸውን ነው።
ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ወታደሮቹ ይህን ለማድረግስ እንዴት ደፈሩ? ከአሁንስ በሁዋላ በፈለጋቸው ሰአት እየመጡ ተመሳሳይ ትእይንት እንደማያደርጉ ምን መተማመኛ አለ? ከየካቲት አብዮት ጅማሮና፣ የወታደሩ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እያደጉ መስከረም ሁለት ቀን ሥልጣን ወደ መያዝ ከተሸጋገሩበት ታሪክ ጋር ምን መመሳሰልና ልዩነት አለው?
ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። በየካቲት 1966 በተመሳሳይ መንገድ የወታደሮቹን ጥያቄዎች ይዘው ሲመጡ፣ በመለሳለስ ለማስታገስ የጠየቁትን የደሞዝ ጭማሪ ወዘተ በማድረግ ለመፍታት ተሞክሮ ነበር ። ሆኖም ደረጃ በደረጃ ጥያቄያቸው እየጠነከረ፣ ትእግስታቸውም እየተሟጠጠ፣ ከአራት ወራት በሁዋላ ሰኔ 21 ቀን 1966 ደርጉን መስርተው ተቀናቃኝ ሥልጣን አራተኛ ክፍለጦር ላይ መሠረቱ ። ከዚያም ልጅ እንዳልካቸውም ለስላሳና ደካማ፣ አልጋውም ባለቤት አልባ ባዶ መሆኑን ሲያዩ፣ መስከረም ሁለት ቀን 67 ንጉሱን ገልብጠው ወታደራዊ አገዛዝ ሃገራችን ላይ ጫኑ። ለ17 ዓመታትም ቀጠቀጡን ። ከዚህ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን መማር ያስፈልጋል ።
ሁሌም መንግስት ጠንካራ እንጂ ለስላሳ ሆኖ መታየት የለበትም ። ከሚወደድ መንግስት የሚፈራ ይሻላል ይላሉ አንዳንድ ፈላስፋዎች ። በእኛ ልዩ ሁኔታ ተወዳጅም ተፈሪም መንግስት ሊኖረን ይችላል፣ ይገባልም ። በቡራዩ የተደረገውን፣ የኦነግ ታጣቂዎች በወለጋና አካባቢው የሚያደርጉት ሳያንስ፣ መሪው ወጥተው ትጥቅ አናወርድም ማለታቸው ወዘተ መንግስትን መሃሪና የሚፈቀር ሳይሆን የሚናቅ እያደረገው የሄደ ይመስለኛል። የተናቀ መንግስት ደግሞ በሥርአት ማስተዳደር እያቃተው ይሄዳል ። ከዚህ የዛሬው የወታደሮች “አመፅ” የዶክተር አቢይ አስተዳደር ትልቅ ትምህርት ሊወስድ ይገባዋል። መንግስት ሊፈራና ሊከበር እንደሚገባው  መስመሩን ማስመር አለበት ። አምባገነን ይሁን እያልኩ አይደለም።
ወታደሮች ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። መስመራቸውን ይዘው፣ ባሉበት መጠየቅ ይችላሉ። ምንም ይሁን ምን ግን፣ ወኪል መርጠው፣ ቤተመንግስት “ሰብረው” ገብተው ጥያቄ ማቅረብ ሊፈቀድላቸው አይገባም። የዶክተር አቢይ አመራርም፣ ሁኔታዎች እንዴት እዚህ ደረጃ እስኪደርስ መድረክ መክፈትም ሆነ መፍትሄ መሻት እንዳልቻለ ራሱን መፈተሽ ይገባዋል።  የዛሬው የወታደሮች ደርግ ትዕይንት በፑሽአፕ የፎቶ ምስሎች የሚደበቅ ተራ ነገር ሳይሆን፣ ኢትዮጵያችን በየቀኑ እየተላመደች የመጣችው ሥርአተ አልበኝነትና መፈናቀል አንድ አካል ነው። የዶክተር አቢይ አስተዳደር ከድግሱና ሆያሆዬው ቀነስ አድርጎ፣ የሃገሪቱ መፃኢ እድል ላይ ማተኮር ይኖርበታል። የጎላውን ሃገራዊ ችግር በፑሽአፕ ፎቶ መደበቅ አይቻልም። በደቂቅ ደረጃ የሚደረግ ማኒፑሌሽን፣ በዘላቂ ርእይ ሃገር መምራትን መተካት አይቸልም።  የወታደሮቹንም ጥያቄዎች ማወቅ መብታችን ይመስለኛል።  ሚዲያዎቹስ የት አሉ?
Filed in: Amharic