>
5:13 pm - Friday April 18, 4504

የዶክተር አብይ መንግስት በዚህ ጉዳይ ምን ይላል?  (ደረጀ ሀብተወልድ)

የዶክተር አብይ መንግስት በዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
ደረጀ ሀብተወልድ
ከአክቲቪስቶች ታማኝ በዬነ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች አርበኞች ግንቦት ሰባት -የዶክተር አብይን የሰላም ጥሪ ከልብ በመቀበል ወደ ሀገር ገብተው በፍጹም መታመን ላበረከቱት ለውጡን የማገዝ ተግባር አድናቆቴን እቸራቸዋለሁ።
አርበኞች ግንቦት ሰባት በተለያዩ ከተሞች ካደረጋቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች የተገነዘብኩት ሀቅ ፣የንቅናቄው መሪዎች የሃሳብ የበላይነት አሸናፊ ሆኖ ለሚወጣበት ስልጡን ፖለቲካና ዲሞክራሲያዊ ስርአት አብዝተው መናፈቃቸውን ነው።
ባደረጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ ህዝቡ ለለውጡ ኃይል ድጋፍ እንዲሰጥ ያለማሳለስ መወትወታቸውን በዐይኔ ተመልክቻለሁ።በጆሮዬ ሰምቻለሁ። ከዶክተር አብይ ጋር በገቡት የእምነት ቃል ኪዳን መሰረት ከነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረጋቸው ህያው ምስክር ነኝ።
አያድርገውና ለወጡ በሰበብና በምክንያት ቢጠለፍ ፣ ወይም በፀረ ለውጥ ኃይሎች ቢቀለበስ ፣እነሱ ባለዕዳ አይደሉም። ” ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጩን” የሚያሰኛቸው አንዳችም ነገር የለም።
ምክንያቱም፣በአንዳንድ ጉዳዮች በደጋፊዎቻቸው እየተወቀሱ ጭምር ለውጡን ለማሳካት ሲሉ ታግሰው የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋልና።
በአንዳንድ አካባቢዎች ሆነ ብሎ የተፈጠሩባቸውን እንቅፋትና ችግሮች በመታገስና በማሳለፍ – ለውጡን ለማገዝ እስከ ጥግ ድረስ ሄደዋልና።
የአክቲቪስ ታማኝም ሆነ የንቅናቄው ስብሰባዎች በሙሉ ያለ ምንም ኮሽታ በሰላም መጠናቀቃቸውም ሌላው እነሱንም ሆነ ደጋፊዎቻቸውን ምስጋና የሚያስቸር ነው።
ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ለውጡን ከልብ እያገዙ ያሉት እነዚህ ኃይሎች ከሌሎች ደጋፊዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በሚል በተለያዩ ከተሞች ሊያደርጓቸው የሚይዟቸው የስብሰባ ፕሮግራሞች በመስተዳድር አካላት በተደጋጋሚ ሆነ ብለው እንዲሰረዙ የሚደረጉበት ምስጢር ሊገባኝ አልቻለም።
ተቃዋሚዎች በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያደረገው የዶክተር አብይ መንግስት ምን ይላል?
Filed in: Amharic