>
5:13 pm - Friday April 19, 0346

የሶማሌ ክልል ተጠርጣሪዎችን አያያዝ በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው አስረዱ

የሶማሌ ክልል ተጠርጣሪዎችን አያያዝ በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው አስረዱ ታምሩ ጽጌ

‹‹በጅምላ የተቀበረ አስከሬን አውጥተን ለማስመርመር እየተነጋገርን ነው››

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን

‹‹መቃብር ሲቆፈር እኛን የሚወክል ጠበቃ ወይም እማኝ ያስፈልገናል››

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ

በጅምላ ነፍስ ግድያ፣ በከባድና ቀላል የአካል ጉዳት፣ በሃይማኖትና የንግድ ተቋማት ቃጠሎ፣ በንብረት ውድመት፣ በማፈናቀልና ሕገወጥ ቡድን በማደራጀት፣ በማስታጠቅ፣ ትዕዛዝ በመስጠትና በሌሎችም ወንጀሎች ተጠርጥረው፣ በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች፣ በማረፊያ ቤት አያያዛቸውን አስመልክቶ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው ምላሽ ሰጡ፡፡

ኃላፊው ኮማንደር ኪዳነ አየለ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው እንዳስረዱት ተጠርጣሪዎቹ አቶ አብዲ መሐመድ፣ ወ/ሮ ራሂማ መሐመድ፣ አቶ አብዱራዛቅ ሳኒና ኮሚሽነር ፈረሃት ጣሂር አያያዛቸውን በሚመለከት ለፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢና ትክክል አይደለም፡፡ ታሳሪዎቹ በአግባቡ እየተስተናገዱ መሆኑን፣ ታስረው የሚገኙት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኛ ማረፊያ ቤት መሆኑንና በየሳምንቱ ሰኞ እሳቸውን ጨምሮ ኃላፊዎች የእስረኛ ጉብኝት ሲያደርጉ ያለባቸውን ችግር እንደሚጠይቁና እስካሁን በእነሱ ላይ ምንም ችግር እንዳልሰሙና እንዳላዩ ተናግረዋል፡፡ ሕክምናን በሚመለከት ላነሱት ጥያቄ ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፣ በእስር ቤቱ የጤና መኮንኖችና ነርሶች ተመድበው ለእስረኞች የቅርብ ክትትል በማድረግ በደረጃቸው ሕክምና ይሰጣሉ፡፡ አቶ አብዲም ሆኑ ወ/ሮ ራሂማ በሪፈር ፖሊስ ሆስፒታል ሄደው ሕክምና እንደተደረገላቸው፣ በተለይ አቶ አብዲ ተክለ ሃይማኖት ሆስፒታል ተወስደው መታከማቸውን ገልጸዋል፡፡ ፀጉራቸውን እንዲስተካከሉም ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡ ኮሚሽነር ፈረሃን መድኃኒት በአግባቡ እንደማያገኙ ስላመለከቱትም፣ ተቋማቸው የቻለውን ጥረት አድርጎ እሳቸው የፈለጉትን መድኃኒት በማጣቱ ቤተሰቦቻቸው ጭምር እንዲፈልጉላቸው እስከማድረግ መድረሱንና ፍርድ ቤት የሚናገሩትና በማረፊያ ቤት ከእነሱ ጋር የሚነጋገሩት የተለያየ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የማረፊያ ቦታ ንፅህናና ጥበትን በሚመለከት ኃላፊው እንዳስረዱት፣ እንዲያውም ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩበት ክፍል ከሌሎቹ የተሻለ ነው፡፡ ማለትም እነሱ የታሰሩት ለየብቻቸው መሆኑን ሌሎች ግን ሁለት፣ ሁለት እየሆኑ የሚታሰሩበት ክፍል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች የተለየ ሳይሆን፣ የተሻለና ተቋሙ ያለው ማቆያ ቦታ በመሆኑ የተለየ ነገር አይደለም ብለዋል፡፡ አቶ አብዲ እጅግ በተሻለና ሁሉም ነገር በተሟላበት ክፍል ውስጥ መታሰራቸውንም አክለዋል፡፡ ንፅህናን በሚመለከት ራሳቸው ተጠርጣሪዎቹ እንዲያፀዱ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ በጨለማ ቤት ስለመታሰራቸው የተናገሩት ሐሰት መሆኑን፣ ጨለማ የሆነ ማረፊያ ቤት እንደሌለና በርም ተከፍቶ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡ በተለይ አቶ አብዲ በቋንቋ ችግር ቤተሰቦቻቸው ሊጠይቋቸው እንዳልቻሉ ያቀረቡት አቤቱታን በሚመለከት ችግሩ አንድ ቀን ተፈጥሮ እንደነበር አረጋግጠው፣ አሁን ችግሩ ተፈትቶ በፈለጉት ቋንቋ እየተነጋገሩና ቤተሰቦቻቸውም እየጠየቋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀርቦለት የነበረውን የተጠርጣሪዎች አቤቱታ አስመልክቶ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ቀርበው ምላሽ ከሰጡ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ ደግሞ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተሰጠው አሥር ቀናት ውስጥ የሠራውንና ይቀረኛል ያለውን የምርመራ ሒደት ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የዘጠኝ ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ በሁከቱና ብጥብጡ ምክንያት ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን በርካታ ሰዎች በሚመለከት ከጅግጅጋ ሆስፒታል የሕክምና ማስረጃ መጠየቁን፣ ተጠርጣሪዎቹ ላደራጁት ‹‹ሄጎ›› ለሚባለው ቡድን የሚውል ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በመደረጉ፣ ምን ያህል እንደሆነ ማስረጃ እንዲሰጠው መጠየቁን ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች እየተደዋወሉ ስለወንጀሉ አፈጻጸም የተነጋገሩባቸው 14 ሞባይሎችና አሥር ሲም ካርዶች፣ የተለያዩ የወንጀል ድርጊት ሲፈጽሙ የሚያሳዩ ሲዲና ሦስት ላፕቶፖችን ለመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ለምርመራ መስጠቱን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

የሚቀሩ የምርመራ ሒደቶችን በሚመለከት ያልተያዙ ግብረ አበሮችን መያዝ፣ በተጎጂዎች ላይ የደረሰውን የአካል ጉዳት መጠን የሚያስረዳ ማስረጃ ከሆስፒታል መቀበል፣ በጅምላ ተጨፍጭፈው በአንድ ጉድጓድ የተቀበሩ በርካታ ዜጎችን አስከሬን አውጥቶ ማስመርመር፣ ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ወጣ የተባለውን የገንዘብ መጠን የሚገልጽ ማስረጃ መቀበል፣ የሞባይል፣ የሲም ካርድ፣ የሲዲና የላፕቶፖች የቴክኒክ ምርመራ ውጤት መቀበል፣ የተደፈሩ ሕፃናትና ሴቶች የሕክምና ምርመራ ውጤት መቀበል፣ ቀደም ብሎ የተሰጠውን የ18 ሰዎች አስከሬን ምርመራ ውጤት መቀበል እንደሚቀረው ለችሎቱ በማስረዳት፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ ሒደትና የጠየቀውን 14 ተጨማሪ ቀናት በሚመለከት ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው አማካይነት ተቃውመዋል፡፡ ፖሊስ ላለፉት ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ‹‹ሠርቻለሁ›› የሚላቸው የምርመራ ሒደቶች ተመሳሳይና በይዘታቸውም አንድ ዓይነት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ስንት ግብረ አበሮች እንደያዘ አለመግለጹን፣ ከአሥር ቀናት በፊት በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች አስከሬን እንደሚያወጣ ቢናገርም፣ የስንት ሰው አስከሬን እንዳወጣና ስንት እንደቀረው አለመናገሩን፣ በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ የሕክምናና ሌሎች ማስረጃዎችን በሰዓታት ወይም በሁለትና ሦስት ቀናት መቀበል እየቻለ አለመቀበሉን፣ የቴክኒክ ምርመራም በተመሳሳይ ሁኔታ ከመንግሥት ተቋም የሚገኝ በመሆኑ የሰዓታት ሥራን ሆነ ብሎ ከማጓተት በስተቀር፣ መርማሪ በቡድኑ ሥራውን በአግባቡ እየሠራ አለመሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የወ/ሮ ራሂማ መሐመድ ጠበቃ አቶ ሞላልኝ መለሰ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ቀሪ የምርመራ ሥራ ለማከናወን ተጠርጣሪዎችን በማረፊያ ቤት የሚያስቆይ የምርመራ ሥራ መኖሩን መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ ሊያስረዳ ይገባል፡፡ እስካሁን ግን ደንበኛቸውን በማረፊያ ቤት ሊያስቆይ የሚችል የምርመራ ሒደት እንዳለው ባለማስረዳቱ፣ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር ሊለቀቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስ የፈለገውን ጊዜ ወስዶ ምርመራውን መቀጠል እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በአግባቡ እየሠራ መሆኑ መታየት እንዳለበት አቶ ሞላልኝ አሳስበው፣ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች እስከሚያዙ ድረስ የእሳቸው ደንበኛ (ወ/ሮ ራሂማ) በማረፊያ ቤት መቆየት እንደሌላባቸው ተናግረዋል፡፡ የፖሊስ ጥያቄ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ከማሳጣት ባለፈ የሕግ መሠረት እንደሌለውም አክለዋል፡፡ ደንበኛቸው የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ መሆናቸውን አስታውሰው፣ መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮና ከሌሎች ተቋማት በመሆኑ፣ ከእሳቸው ደንበኛ ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ ታስረው ሊቆዩ እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸው ሲሠሩ የነበረውና ፖሊስ በምርመራው እያስረዳው ያለው ነገር ስለማይገናኝ፣ የምርመራ መዝገቡ ተለይቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ በደንበኛቸው ላይ እየቀረበ ያለው የምርመራ ሒደት እሳቸው ይሠሩት ከነበረው የሥራ ድርሻ ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) መሠረት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ውድቅ ተደርጎ በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

አቶ አብዲ ደግሞ ለችሎቱ እንደተናገሩት፣ ፖሊስ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የምርመራ ውጤት እያቀረበ ነው፡፡ ሰዎች በጅምላ ተገድለው ተቀብረዋል ቢልም፣ እነማን እንደሞቱ፣ ስንት እንደሆኑ፣ የእነማን ወገኖች እንደሆኑ፣ መቼና የት እንደተቀበሩ የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤቱ አለማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ የጅምላ ቀብር ቦታ የሚያስቆፍር ከሆነም ‹‹እኛን የሚወክል ጠበቃና ሌሎች እማኞች መገኘት አለባቸው፤›› በማለት፣ ያልተሠራውን ይኼንን ያህል ተገኝቷል ተብሎ ለፍርድ ቤት እንዳይቀርብ ሥጋታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹መርማሪ ቡድኑ ሞባይሎችን ልክ እንደ ፈንጂ ሁል ጊዜ ያቀርባል፤›› ያሉት አቶ አብዲ፣ በዚህ ላይ ፍርድ ቤቱ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በተረኛ ችሎት ስለሚሠራና ዳኞች በየጊዜው ስለሚቀያየሩ፣ መርማሪ ፖሊስም በየጊዜው 50 ግብረ አበሮችና 60 ግብረ አበሮች እያለና እሱም እያቀያየረ ጊዜ እየወሰደ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር አዋሳኝ በመሆኑና ሰፊ ስለሆነ ለምርመራ አስቸጋሪና የማይመች መሆኑን ቢናገርም፣ መንግሥት ያለበትና ሰላማዊ ክልል በመሆኑ እንደ ምክንያት ሊቀርብ እንደማይገባውም አቶ አብዲ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ በእነሱ ላይ እየተደረገ ያለውን የምርመራና አያያዝ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲያውቁት እንዲደረግላቸውም አቶ አብዲ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ኦቶ ፈርሃን ጣሂርና የዳያስፖራ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አብዱራዛቅ ሳኒ መርማሪ ፖሊስ ነገሮች እንደተስተካከሉ እየተናገረ ቢሆንም፣ ላለፉት 43 ቀናት (እስከ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) ታስረው የሚገኙት በጨለማ ቤት ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽነሩ የስኳር ሕመምተኛ በመሆናቸው የሚፈልጉትን መድኃኒት ማግኘት አለመቻላቸውንም አስረድተዋል፡፡ አቶ አብዱራዛቅ ደግሞ የአስም ሕመምተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የታሰሩበት ክፍል አየር ስለማያስገባ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ ራሂማም እንደገለጹት፣ ላለባቸው ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት እየወሰዱት ያለው መድኃኒት ከመታሰራቸው በፊት ይወስዱት የነበረ ነው፡፡ ደማቸው ሲወጣና ሲወርድ መውሰድ ያለባቸው የተለያዩ መድኃኒቶች ቢሆኑም፣ ሊያገኙ ባለመቻላቸው አደጋ ውስጥ መሆናቸውንና ሰሞኑንም ጥሏቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በዶክተር ተመርምረው መድኃኒቱ ካልተለወጠላቸው፣ በማንኛውም ሰዓት አደጋ ሊያስከትልባቸው እንደሚችልም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተጠረጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና መብት በመቃወም ምክንያቱን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ቢፈቀድላቸው ምስክሮችን እንደሚያስፈራሩና እንደሚያስጠፉ፣ ሰነዶችን እንደሚያጠፉና ተሰሚነት ስላላቸው የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ስለሚችሉ ምርመራ እንደሚያደናቅፉበት ተናግሯል፡፡ ተጠርጣሪዎች የግብረ አበሮቻቸውን ማንነት እንዲገልጽ መርማሪ ቡድኑን መጠየቃቸው ተገቢ እንዳልሆነና በሚስጥር ክትትል በማድረግ ለሕግ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አቶ አብዲና ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች 41 አባላት ያሉትን የ‹‹ሄጎ›› ቡድን በመሰብሰብና በማስታጠቅ፣ ቡድኑ ደግሞ ሌሎችን የክልሉን ወጣቶች በመቀስቀስ በዘርና በሃይማኖት በመለየት ከክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል ጋር በመሆን ወንጀሉ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን በማስረዳት፣ ይኼንን ድርጊት ለመመርመር ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የታጠቁት የ‹‹ሄጎ›› ቡድን አባላት በቀላሉ የሚያዙ አለመሆናቸውንና አጠቃላይ የወንጀሉ አፈጻጸም ውስብስብና ጊዜ የሚወስድ መሆኑንም አክሏል፡፡ በጅምላ ተገድለው ተቀብረዋል የተባሉ ሰዎች አስከሬን አወጣጥን በሚመለከት፣ መርማሪ ቡድን ብቻውን የሚያወጣው ሳይሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች እማኞች ባሉበት የሚከናወን መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡ መርማሪ ፖሊስ እንዳስረዳው የምርመራ ሒደቱ ውስብስብ መሆኑን እንደተገነዘበ፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮች መኖራቸውንና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ማስፈለጉን በማመኑ፣ 11 ተጨማሪ ቀናት በመፍቀድ ለጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ሕመማቸው ከጤና መኮንንና ከነርሶች አቅም በላይ በመሆኑ ሐኪም ዘንድ ቀርበው እንዲታከሙ፣ አጠቃላይ አያያዛቸው እንዲስተካከል፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርና ቤተሰቦቻቸው እንዲጠይቋቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡

Filed in: Amharic