>
5:13 pm - Thursday April 20, 5882

ሽማግሌዎቿን፣ ጥበቦቿን፣ ታሪኮቿን፣ ቅርሶቿን የምትጥል ሐገር! (እሸቱ ብሩ ይትባረክ)

ሽማግሌዎቿን፣ ጥበቦቿን፣ ታሪኮቿን፣ ቅርሶቿን የምትጥል ሐገር!
እሸቱ ብሩ ይትባረክ
ይህቺ ድንቅ ክቡር ታሪካዊት ሐገራችን ኢትዮጵያ በቅድመ አያቶቻችን ገድል፣ ጥበብና ዕውቀት ትልቅ ከፍታ ላይ የተሠቀለች ሐገር ነበረች፡፡ ከፍታዋ በአንድ ነገር ብቻ አልነበረም፡፡ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በስነጥበብ፣ በቅርስ፣ በመንፈሳዊ ስልጣኔ፣ በፍልስፍና፣ በሙዚቃ፣ በስነቃል፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በዜማ፣ በጀግንነት፣ ወዘተ ሩቅ ተስፈንጥራ እንደነበረች ታሪክ ይመሠክራል፡፡ አባቶቻችን፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ለሐገራቸው ያልከፈሉት መስዋዕትነት የለም፡፡ ነፃነቷንና ዳርድንበሯን ከማስጠበቅ ጀምሮ ኩሩ ታሪኳን፣ ልዩ ባህሏን፣ ድንቅ ጥበቧን በራሷ ፊደል ለማስተላለፍ ታላቅ ተጋድሎአድርገዋል፡፡
 ብራና ፍቀው ታሪካቸውን፣ ጥበባቸውን፣ መንፈሳዊ ድርሳናቸውን ደርሠው፤ ከጠላት እጅ ጠብቀው፤ በዋሻና በገዳሙ ደብቀው አቆይተውልናል፡፡ ይሄም ታላቅነታቸው ዛሬ በሐገራችን የሚታየውን ድንቅ ቅርስ፣ ልዩ ባህል፣ ረቂቅ ጥበብና ዕውቀት፣መቻቻልና አንድነት፣ ፍቅርና አብሮነትን አትርፎልናል፡፡ ክብር ለነዚህ ድንቅ አባቶቻችን እና አያቶቻችን! በእነሱ መስዋዕትነት እልፍ ትሩፋት አግኝተናልና!ነገር ግን ዛሬ ዛሬ ይሄ ጥበባችን፣ ቅርሳችን፣ ታሪካችን፣ አንድነታችን፣ ተቻችሎ መኖራችን፣ መዋደዳችን፣ ፍቅራችን፣ ወንድማማችነታችን፣ ዝምድናችን ጠውልጎና ደርቆ ሊጠፋ የደረሠ ይመስላል፡፡
በመካከላችን አለመስማማት ነግሶ አንዱ በአንዱ ላይ በመነሣት የጠላትነት ስሜት ማሳየት አዲስ በሽታ ሆኖብናል፡፡ ትውልዱ በመስፋት ጥበብ ከመጠበብ ይልቅ እርስበርሱ በዘር፣ በጎጥ፣ በመንደርተኝነት ተከፋፍሎ አንሶ ጠብቧል፡፡ቅርሳችንን፣ ታሪካችንን፣ ጥበባችንን ሲጠፋ በዓይናችን እያየን እኔን አይመለከትም የእከሌ ክልል ጉዳይ ነው በሚል እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለናል፡፡ ለዚህ አንዱ ማስረጃ የሚሆነው ቅርሶቻችን ሊወድሙ ጫፍ ላይ መድረሳቸውን እያየን ዝም ማለታችን ነው፡፡
 ለምሣሌ የቅዱስ ላሊበላ ቤተመቅደሶች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ማን ይድረስላቸው?? እኛው
ነንና! ሌላ ማን አለ! ወዳጆች አንድነቱን የማያረጋግጥ ቅርሶቹን የማይጠብቅና ታሪኩን የማያከብር ትውልድ ወዴት ይሆን ጉዞው? የአባቶቹን ጥበብ ይዞ የማያቆይና የራሱን አክሎ ለመጪው ትውልድ የማያስተላልፍ የውጪውን ናፋቂ፣ የሐገሩን ናቂ ብኩን ትውልድ ታሪኩ ላይ ምን ይፃፍለት ይሆን?? በዚህ ዘመን ለዚህ ትውልድ ዘመኑን የሚዋጅ ሽማግሌ ጠፍቶ እርስበርሱ እንዳይስማማ ሆኗል፤ የሚያስታርቅ ሠው ተቸግረን አንዱ ባንዱ ላይ ብሔር ተኮር የጦርነት ነጋሪት የሚያሠማበት፣ የጥል ከበሮ የሚደልቅበት ከባድ ጊዜ ላይ ደርሠናል፡፡
ሽማግሌዎቻችንን የት ጣልናቸው? የአብሮነታችንንስ ጥበብ ወዴት አደረስነው? በጋራ ሐገራዊ አጀንዳዎቻችን ዙሪያ ተነጋግረን የማንስማማባውስ ለምንድነው? ባለውለታዎቻችንን፣ታሪክ ሠሪዎቻችንን፣ ሽማግሌዎቻችንን እያሸማቀቅንና የውሸት ታሪክ እየፈጠርን የምናሳቅቃቸውስ ምን ያህል ብንጠብ ነው? አስታራቂያችን ማን ይሆን ጎበዝ? እንጃ!
ለዚህ ምሣሌ ይሆነን ዘንድ አንድ ወግ አለ፡፡  በጥንት ዘመን አንዲት ከሌላው ዓለም የተለየ ህግ፣ ወግና ልማድ ያላት ሐገር ነበረች፡፡ የዚች ሐገር የተለየ ህግ፣ ወግና ልማድ አንድ ሠው ሲሸመግል ሠው ወደማይደርስበት ተራራ ተወስዶ መጣል ሲሆን በዚያ ቦታ ሲጣልም የሚበላውና የሚጠጣው አጥቶ እንዲሞት ማድረግ ነው፡፡ በዚህች ሐገር ሽማግሌ መጦር የሚታሠብ አይደለም፡፡ ምን አለፋችሁ ሽማግሌ እንደሸንኮራ አገዳ ተመጥጦ የሚጣልባት ሐገር ነች፡፡ አንድ ወቅት የዚች ሐገር ከፍተኛ ባለስልጣን የሆነ ሠው የእሱ ተራ ሆነና ሽማግሌ አባቱን ተራራ ላይ የሚጥልበት ቀን ደረሠ፡፡
ነገር ግን ሚስቱ ይሄንን እንዳያደርግ ይልቁንም አባቱን ከዋሻ ደብቆት ምግቡን ዕለት ዕለት እንዲያቀርብለት መከረችው፡፡ እሱም ሚስቱ እንዳለችው ይሄንኑ በሚስጥር ማድረግ ጀመረ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ እግዚአብሔር በድንገት ለዚያች ሐገር ንጉስ ተገለጠና እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ ጠየቀው፡፡ እንቆቅልሹን መፍታትም ሆነ ማስፈታት ቢያቅተው ግን በሐገሩ ላይ ቅጣት እንደሚያወርድበት ያስጠነቅቀዋል፡፡ እንቆቅልሹም እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹ሁለት እባቦች በፊትህ አቀረብኩ፡፡ ወንዱንና ሴቱን እባብ ለይልኝ›› አለው፡፡ ይሁንና ንጉሱም ሆነ የንጉሱ ባለሟሎች እንቆቅልሹን መፍታት ተሳናቸው፡፡ ንጉሱም ቢጨንቀው፡- ‹‹ይህን እንቆቅልሽ የሚፈታልኝ በህይወት ዘመኑ የሚሻውን በሙሉ አደርግለታለሁ›› ብሎ ለሕዝቡ ቃል ገባ፡፡ ይህንን የሠማው ባለስልጣን አባቱን በዋሻ ደብቆት ስለነበረ ወደአባቱ በፍጥነት በመሄድ እንቆቅልሹን ይነግረዋል፡፡
ሽማግሌውም ጥያቄውን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ እንዲህ አለ፡- ሂድና ለንጉሱ ንገረው፡፡ ሁለቱን እባቦች በአበባ ምንጣፍህ ላይ አስቀምጣቸው፡፡ ቀድሞ ወደሌላኛው እባብ የሚንቀሳቀሰው ወንዱ እባብ ነው፡፡ ሴቷ እባብ ግን ወንዱን ትጠብቀዋለች እንጂ ወደእሱ አትሄድም›› አለው፡፡ ባለስልጣኑም የአባቱን ምክር ይዞ በችኮላ ሲገሠግስ ንጉሱ ዘንድ ይቀርብና የእንቆቅልሹን ፍቺ ይነግረዋል፡፡ ንጉሱም እግዚአብሔር ዘንድ ቀርቦ ምላሹን ተናገረ፡፡
እግዚዘብሔርም አሁንም ሌላ ጥያቄ አቀረበለት፡- ‹‹ሁለት በቀለማቸውም፣ በአቋማቸውም ፍፁም አንድ ዓይነት የሆኑ ፈረሶች አቀረብኩልህ፡፡ እነዚህ ፈረሶች እናትና ልጅ ናቸው፡፡ እናቲቱን ከልጇ ለይተህ ንገረኝ፡፡ የዚህን መልስ ካገኘህ ሐገርህ ከጥፋት ይተርፋል›› አለው፡፡ ንጉሱ አሁንም ምላሹ ጨነቀውና ባለስልጣኑን መልስ እንዲፈልግለት ጠየቀው፡፡ ባለስልጣኑም ወደሽማግሌ አባቱ ዘንድ ሄደ፡፡ አባቱም ጥያቄውን ሠምቶ እንዲህ አለው፡-
‹‹ለንጉሱ ንገረው፡፡ ሁለቱንም ፈረሶች በጋጥ ውስጥ አስገባና ጭድ አቅርብላቸው፡፡ ጭዱን በአፏ ወደልጇ የምትገፋው እናቲቱ ነች›› አለው፡፡ ባለስልጣኑም ሽማግሌ አባቱ እንደነገረው ለንጉሱ ተናገረ፡፡ ንጉሱም እግዚአብሔር ዘንድ ቀርቦ መልሱን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም አለው፡- ‹‹እነሆ ለልጆቸህና ለወጣቶችህ ያሠብካትን ሐገር እንዳላጠፋት የሽማግሌው ጥበብ ታደጋት›› አለው፡፡
ንጉሱም የዚህን ሁሉ ሚስጥር ተረዳ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ሽማግሌን በተራራ ጥሎና አስርቦ የመግደል ደንብና ሕግ እንዲሻር አዘዘ ይባላል፡፡ ወዳጆች ሽማግሌዎቻችን፣ አዛውንቶቻችን፣ ቅርሶቻችን፣ ታሪኮቻችን የያዙት ድንቅ ጥበብና ዕውቀት የትየለሌ ነው፡፡
የዛሬ አደገኛ ችግራችንን (The Present Danger) በሽማግሌዎቻችን ጥበብ ልናስወግደው ይገባል፡፡ አባቶቻችን፣ ቅድመ አያቶቻችን እንደዚህ ዓይነቱን ችግር በዕውቀታቸው አልፈውታል፡፡ አልፈውትም ቅኝ ያልተገዛች፣ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ዳርድንበሯ የተከበረ ሐገር አስረክበውናል፡፡
ዛሬም የጋሞ አባቶቻችን ድንቅ ጥበባቸውን በመጠቀም የአባቶቻቸውን ታሪክ ደግመውታል፡፡ የሽማግሌ ደሃ እንዳንሆን አንድ ምልክት ሆነውልናል፡፡ ባለፈው ሠሞን በደምፍላቱ ገስግሶ፣ በቁጣው ግንባሩ ተቋጥሮ፣ በንዴቱ ተንደርድሮ ለበቀል እጁን ሊዘረጋ የነበረውን የአርባምንጭ ወጣት፣ የአብራካቸውን ክፋይ በጥበባቸው አስክነውታል፡፡ ወደቀልቡ እንዲመለስ አረጋግተው በፍቅር ገዝተውታል፡፡ ክብር ይገባቸዋል! አባቶቻቸውን የሠሙም ወጣቶቹ ሊመሠገኑ ይገባል! ተሠሚና ሠሚ ሲግባቡ ማየት ምንኛ ደስ ይላል! የጋሞ አባቶች ከጥፋትና ከእልቂት ሐገራቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ወገናቸውን ጠብቀዋልና ታሪክ ሲያመሠግናቸው ይኖራል! ከዚህ በላይ ሽምግልና ወዴት አለ ጎበዝ?
ሐገራችን እንደነዚህ ዓይነቶችን ጥበበኛ ሽማግሌዎች አሁንም ደግማ ደጋግማ ትጣራለች፡፡ በሐገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠማው የጦርነት ነጋሪት፣ የመገዳደል ዛቻ፣ የመጠፋፋት ዝግጅት፣ የመለያየት ልፈፋ፣ የመፈነቃቀል ጅምርን ማስወገድ የሚቻለው በሽማግሌዎቻችን ጥበብ ብቻ ነው፡፡ የሽማግሌ ደሃ አንሁን! በየትኛውም አካባቢ ያሉ ሽማግሌ አባቶቻችን ሐገራችን የተደቀነባትን አደጋ በጥበባቸው ያስወግዱ ዘንድ ልቦናቸው ይነሳሳ! ለሠላምና ፍቅር ሽምግልናቸው ይትጋ! አሜን ይሁንልን!
ሽማግሌዎቿን፣ ጥበቦቿን፣ ታሪኮቿን፣ ቅርሶቿን፣ ማንነቷን የምትጥል ሐገር መጨረሻዋ መጥፋት እንጂ መልማት አይደለም! ጥሪቶቿን ትታ የምትነጉድ ሐገር ወደኋላ እንጂ ወደፊት አትራመድም፡፡ ዕድገትም ሆነ ልማት ያለሠላም፣ ያለፍቅር፣ ያለአንድነት እውን የሚሆን አይደለም፡፡ የወደቁትንና የጣልናቸውን ሽማግሌዎቻችን ሠብስበን ክብር በመስጠት እናድምጣቸው! አዛውንቶቻችንን እናክብር!
አረጋውያንን እንጡር! ጥበባቸውን እንቅሠም፣ ሊወድቁ ያሉ ቅርሶቻችንን ቀና አድርገን እንንከባከባቸው! መጥፎና ክፉ ታሪካችንን ተምረንበት ጥሩ ጥሩውን ብቻ እናስፋፋ የሚለው የዛሬው ቁምነገርና ዋና መልዕክት ነው!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
Filed in: Amharic