>
5:13 pm - Tuesday April 20, 9120

ኦነግ በቅድሚያ ከአላማው ጋር ይፋታ!! (ፋሲል የኔአለም)

ኦነግ በቅድሚያ ከአላማው ጋር ይፋታ!!
ፋሲል የኔአለም
 መቼም የኦነግ 2 ሺ ሰራዊት  ስልጣን ይይዛል ብሎ እንቅልፉን አጥቶ የሚያድር የሚኖር አይመስለኝም።  እንኳን በ2 ሺ፣ በ20 ሺውም አልተሳካ። የፖለቲካ ትርፍ ባሳይገኝለትም፣ በ2 ሺ ወታደሮቹ ሰላማዊ ዜጎችን ሰላም ሊነሳቸው ይችላል። የኦነግ ሰራዊት በረገጠበት ቦታ ሁሉ ግድያ፣ መፈናቀል፣ መሸበር ወዘተ የቀን ተቀን ክስተት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ድርጊቶች ግን ኦነግን ከመንግስት ስልጣን ይበልጥ ያርቁታል እንጅ አያቀርቡትም።

ኦነግ ከአላማው ጋር አልተፋታም፤ እኛም ጠመንጃውን እንጅ አላማውን እንዲፈታ አልወተወትነውም ፤ ጠመንጃ እንድትታጠቅ ወይም እንድትፈታ የሚያደርግህ አላማህ ነው። “አላማየን በሰላም ለማካሄድ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም” ብለህ ካመንክ ትታጠቃለህ፤ “ምቹ ናቸው” ካልክ ደግሞ ታወርዳለህ።  በአጭር አነጋገር፣ ኦነግ ትጥቁን የማይፈታው ከአላማው ጋር ስላልተፋታ ነው ። ከኤርትራም የወጣው አገሪቱ “ በቃኝ” ስላለችው፣ እንዲሁም መንግስቱን የኦሮሞ ተወላጆች ተቆጣጥረውታል ብሎ ስላሰበ እንጅ ከአላማው ጋር ፍች ስለፈጸመ አይመስለኝም።  ኦነግ “ኤርትራ ቆይ” ብትለው ወይም ከኤርትራ ጋር ሰላም ባይወርድ ኖሮ  ይቆይ ነበር፤  ስልጣን በብአዴን ( አዴፓ) እጅ ቢገባ ኖሮም አይመጣም ነበር። ኦነግ ሁኔታዎች ገፋፍተውት ቢመለስም፣  አሁንም “የራስን እድል በራስ ከመወሰን” ጥያቄው ጋር አልተፋታም። አሁንም የመገንጠልና አገር የመመስረት ህልሙን ከማለም አልቦዘነም። ለጊዜው ዝምታን ቢመርጥም፣ ነገ እነ አብይ በምርጫ ቢሸነፉና የሌላ ብሄር ሰው፣ በተለይም የአማራ ተወላጅ፣ ስልጣን ቢይዝ፣ የመገንጠል ጥያቄውን መልሶ ማንሳቱ የማንሸሸው ሃቅ ነው።

የእነ አብይ ትልቁ ፈተና ኦነግን ከአላማው  ጋር አፋትቶ፣ የ 21ኛው ክፍለ ዘመን ስልጡን ፖለቲካ እንዲላመድ ማድረግ ነው። ኦነግ ከአስተሳሰቡ ጋር እስካልተፋታ ድረስ፣  ዛሬ ትጥቁን ቢፈታ እንኳን ፣ ለነገው ሰላማችን ዋስትና ሊሆን አይችልም።  በማንኛውም ጊዜ የህዝቡን ስሜት እየቀሰቀሰ ሰላም እንዲታወክ ሊያደርግ ይችላል። እነ አብይ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ እረዳለሁ ። ሰሶተኛ አማራጭ ግን ያላቸው አይመስለኝም።  አንደኛው አማራጭ አላማውን እና ትጥቁ  እንዲፈታ አግባብቶ ከሰላማዊ ፖለቲካው ጋር እንዲላመድ ማገዝ ነው። ይህን አልቀበልም ካለ ደግሞ “እድልህን ሞክር” ብሎ  ወደ መጣበት ጫካ መመለስና በጫካው ህግ ማነጋገር ነው። የአብይ መንግስት የጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል የሚችለው የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ዋና ሃላፊነት የተጣለው መንግስት ላይ መሆኑን ተቀብሎ ፈጣን እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው።

Filed in: Amharic