>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7578

ዘፀአት ለኢትዮጵያ!!! (አያሌው ሥነጊዮርጊስ)

ዘፀአት ለኢትዮጵያ!!!
አያሌው ሥነጊዮርጊስ ከስዊዘርላንድ
(ዘፀአት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ ባሕሩን የሚያሻግር አንድ ሙሴን ይዞ)
 
ፋብሪካዎቿ ሁሉ ተነቃቅለው፣ በተወሰዱባት ዝነኛው እድሜ ጠገቡ ምድር ባቡር ኩባንያን ባጣችው ድሬዳዋ ተገኝተን የወጣቱን ብሶት እሪታና ዋይታ አድምጠናል። አርባ አርባ ሀያ ስለሚባለውም ግፍ ሰምተናል
 
   ይህ ድምጽ በበረሃው ውስጥ ሲጮህ የነበረውን የነቢዩ ዮሃንስን ድምጽ ይመስላል።በጨለማ በምንዳክርበት በዚያ ክፉ ዘመን እግዚአብሄር አምላክ ያቀበለውን የሰበከን የብላቴናው የቴዲ ድምጽ፤
  ለእግዚአብሄር አምላክ ምስጋና ይድረሰውና ከፈርኦን ቤት የወጣው ሙሴ ከረዳነው ከተባበርነው ባህሩን ሊያሻግረን በትላንትናው እለት ሙሉ  በሚባል ድምጽ እነሆ ተከስቷል።ወንበሩን ተቆናጧል።
  ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስጽፍ በአውሮፓውያን ሰአት አቆጣጠር ከጠዋቱ 5.30 ነው።ከእንቅልፌ ስባንን አንዳች የተስፋ ስሜት ውስጤን ሞላው።የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ተልእኮ አንግቤ በአገሬ ኢትዮጵያ በተስፋይቱ ምድር ያደረኩትን የስራ ጉዞ አጠናቅቄ ከተመለስኩ ሀያ አራት ሰአት አልሞላኝም።
 ትላንት ለውጥን የሚናፍቅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ምጥ ላይ ነበር.የኢትዮጵያን ክፉ የሚመኙትን  ጨምሮ።ይህን ስል በእርግጠኝነት ያየሁትን የታዘብኩትን ነው።ዶክተር አቢይ የተሸረበበትን ሴራ ሁሉ በጣጥሶ ያልፋል ወይስ እነ አጅሬ—–
የብዙዎች ጭንቀት ነበር።ለእግዚአብሄር አምላክ ምስጋና ይግባውና ቀንበሩ ተሰባብሮ አድሯል።የኢትዮጵያ ክፉ አሳቢዎች በጋራ የገመዱት ገመድ ተበጣጥሷል።
 በዘር፣ በሓይማኖት ፣በብሄር፣ በጎሳ
እንዳንባላ አምላክ በጥበብ የመረጠልን አማራውን፣ኦሮሞውን እስላም፣ክርስትያኑን ያካተተ ቀሪውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ሊያፀናው በውስጡ ራእይ የሰነቀ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ መሪ ሲሰጠን እንባችን ጽዋው ሞልቶ ወደ አርያም ደርሶ ሊታበስ መቅረቡን ማስተዋል የእኛ ፈንታ የመስለኛል።
   በኢትዮጵያ የስራ ጉዞየ እንባ ካራጨን የአዲስ አበባ ሕዝብ አቀባበል ጀምሮ በፌስ ቡክ ሲሰራጭ ከነበረው የእንዳትደርሱ ማስጠንቀቂያ የሚናፈስበት የአማራ ክልል ጎንደር፣ ባህርዳር ፣ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ወልዲያ፣እንዲሁም ፀረ ኢትዮጵያዊነት በእጅጉ የሚሰበክበትን ድራዳዋ ሐረርን አይቻለሁ።በደረስኩበት ቦታ ሁሉ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተገናኝቼያለሁ ተወያይቻለሁ።በስቴዲዮም በአዳራሽ ውስጥ በነበሩ ውይይቶች ተካፍያለሁ።ህፃን፣ ወጣት፣ጎልማሳ አዛውንት፣አሮጊት፣ሽማግሌ ሁሉ ላይ የተስፋ ስሜት ይነበባል።የሰው ፊት ሁሉ እንደ ጠዋት ፀሃይ ያበራል። አንዳች ክፉ መንፈስ ይህችን ፀሃይ ሊያጨልም ቢውተረተርም የጨለማው መንፈስ ዳግም እንደማያንሰራራ ሁሉም በውስጡ እምነት እንዳለው ሳይፈራ በእምነት ይናገራል።እግዚአብሄር አምላክ ከፈቀደ ማንስ ሊያግደው ሊያቆመው ይቻለዋል።
  አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ ለምን 
 ይሆን የራበው ሆዴ(ብላቴናው ቴዲ)
   በተስፋይቱ ምድር በተዘዋወርኩበት ቦታ ሁሉ በውስጤ የብላቴናውን ዘፈን እያቀነቀንኩ ነበር።
አረንጓዴ የለበሰ የልተሰራበት ቦዶ ሜዳ ድንግል መሬት፤
ባሕር ዳር የምድር ገነት የመሰለች ውብ ምድር፣ጎንደር የጥንት ውበቷን እንደያዘች አስታዋሽ ያጣች የተረሳች በጥንታዊ የታሪክ ቅርጾች የተሞላች የጀግኖች ከተማ ፤ደሴ፣ሐይቅ፣ውጫሌ ውርጌሳ፣ወልዲያ አፍሪካን ሊቀልብ የሚችል ያልተነካ ድንግል መሬት። በተፈጥሮ ውበት የታደለች በተቀጣጣይ ተራራዎች የተሞላች ውብ የውቦች ምድር፣መሀል አንባ፣ህብሩ ወረዳ፣ ወይን ጥንቅሽ፣ከውጫሌ ወደ ውርጌሳ ያለው ከላይ ሆኖ ጥምዝምዙ አራተኛውና አምስተኛው መንገድ ከታች የሚታይበት የሚማርክ ተፈጥሮ፣በእነዛ ጠመዝማዛ ተራሮች ላይ በጀርባቸው የውሃ ጀሪካን አዝለው ተራራውን እያማጡ የሚወጡ ውብ ልጃገረዶች ኮረዳዎች፣ህፃናት፣በሰንበሌጥ መሶብ ሙዳይ ሰፌድ የሚሰፉ ጥግ ጥግ የተቀመጡ ጉብል ሴቶች፣በአህያ በግመል ጭነታቸውን ጭነው የሚኳትኑ የዚያች የተስፋይቱ ምድር ወጣቶች
ሁሉም እኛን ሲያዩ ተስፋ የሰነቀ ፊታቸው ቢያበራም አንዳች ኃይል ከዚህ የመከራ ኑሮ ሊገላግላቸው እንደቀረበ ቢሰማቸውም ለእኛ ግን ሕመም ነበር።
 በእውነት ያማል።ይህ ሕመም ቁጭትን የፈጥራል።እዳም አሸክሞናል።ስለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የምናስብና የምንጨነቅ ከሆነ ይህንን አስቀያሚ ሰው ሰራሽ ድህነት ለመቅረፍ የጎን ለጎን ልፍያችንን ዛሬውኑ ማቆም ግድ ይለናል።ወገኖቻችንን ለመታደግ መረባረብ ወቅቱ ዛሬ ነው።
   በድህነት በድንቁርና በኃላቀርነት የምትሳለው ኢትዮጵያ የእኛ አለመተባበር ልፍያ፣ ፍትጊያ፣መጓተት ውጤት እንጂ የምትባለውን እንዳልሆነች በምስራቅ፣በምእራብ፣ በሰሜን፣በደቡብ ተዘዋውረንበት ሁሉ በዐይናችን ታዝበናል።በውሃ ሀብት ከዐለም ሰባተኛ የሆነች አገር፣በአመት ሶስት ጊዜ ዝናብ የምታገኝ ምድር ዜጎቿ በውሃ ጥም ሲቃጠሉ የእለት ጉርስ አጥተው ሲቆዝሙ ማየት በእውነት ከበሽታ ሁለ የከፋ በሽታ ነው ።ያማል።
  በጉዟችን ብዙ ግንዛቤ አግኝተናል  የፋሲል ግንብ ጉብኝት ቁጭትን ፈጥሮብናል። ወጣቶቿ በሚያነቡባት፣ ሕዝቦች ዋይ ዋይ በሚሉባት፣ የታቀደ ግፍ በተሰራባት፣ፋብሪካዎቿ ሁሉ ተነቃቅለው፣ በተወሰዱባት ዝነኛው እድሜ ጠገቡ ምድር ባቡር ኩባንያን ባጣችባት ድሬዳዋ ተገኝተን የወጣቱን ብሶት እሪታ ዋይታ አድምጠናል።አርባ አርባ ሀያ ስለሚባለውም ግፍ ሰምተናል።ይህ ማለት አንድ ከዩኑበርስቲ የተመረቀ ወይንም ስራ የፈለገ  ሰው ስራ ለማግኘት አርባ ፐርሰንት ከተመረጠው ብሄር ሌላ አርባ ፐርሰንት አሁንም ከምርጡ ብሄር ሀያ ፐርሰንት ከተጣለው ብሄር ማለት ነው።ብሄሮቹን መዘርዘር አልፈልግም። ድሬዳዋ ውስጥ የሚኖሩትን ሕዝቦች በማየት እናንተው ለራሳችሁ ዘርዝሯቸው።ይህ ግን በግልፅ ድሬዳዋ ውስጥ በመመርያ ሲሰራበት የኖረ ያለ መሆኑን የድሬዳዋ ወጣቶች በአዳራሽ ውስጥ በነበረን ውይይት በቁጭት ነግረውናል።
በአንዲት እድሜ ጠገብ እናት በወሮ አስካለ የተመሰረተውን የአረጋውያን ማቆያ ጣቢያንም ጎብኝተናል።እኝህ እናት በመሰረቱት የአረጋውያን ጣቢያ 120 እድሜ ጠገቦች ይስተናገዳሉ።በማቆያው የአንድ ሰው የወር ውጪ 500 የኢትዮጵያ ብር ወይንም 20 ዶላር ወይም ዩሮ ያልሞላ ነው።እኛ ፍትጊያውን ትተን በዚህ መሰል የእርዳታ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ምን ያሕል ሕዝብ ልንታደግ እንደምንችል አስበነወል?እኛ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በቦታው  የተቻለንንም እረድተናል በቀጣይም እያንዳንዳችን ልንረዳ የምንችለውን በቅንጅት ለማድረግ መክረናል።
   ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ በፀጥታ ምክንያት ፍቃድ ባላገኘንበትም ሐረር የከተማዋ ወጣቶች ያረፍንበት ድረስ በመምጣት ብሶታቸውን አውግተውናል።ከእኛ ጋር ተቀላቅሎ ለመስራትም ፍላጎታቸውን ገልፀውልን አስፈላጊውን ሁሉ አድርገናል።በየቦታው ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስተውለናል።ግን በእርግጠኝነት ያመንነውና የተረዳነው እኛ ከተባበርን ችግሮችን ከስሩ ገንድሶ ለመጣል ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕዝቦች መነሳሳት እንዳለ እርግጠኞች ሆነናል።
 ብዙ ማለት ይቻል ነበር ።ወረቀትም አይበቃውም።
  በመጨረሻም ዛሬ በዘር በጎሳ በብሄር የሚያምኑ የተደራጁ በድሬዳዋ የነገሱ፣ በሐረር ዘውድ የጫኑ ፣በአማራው ፊታውራሪ የሆኑ የመሰላቸው ሁሉ የሕብረተሰቡን አመለካከት በቅርበት እንደተረዳሁት እንደጉም እንደሚመለከታቸው ስነግራቸው በእውነት ስለእውነት ነው።ጉሙ ሲጠፋ ኢትዮጵያዊነት እንደ ፀሃይ በርቶና ደምቆ እንደሚታይ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።የሚበጀን የሚያዋጣን በዜግነት መብት ላይ የተመሰረተች ማንም በዘሩ በብሄሩ በሐይማኖቱ የማይበደልባት ለሁሉ እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገውን ትንቅንቅ በአንድነት ከልብ መርዳትና ማገዝ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው በማለት ፅሁፌን እቋጫላሁ።
   ይህ ፅሁፍ ማንንም የማይወክል የግል እይታየ መሆኑ የታወቅልኝ ።
Filed in: Amharic