>

አዴፓ ግቡን ራቅ አድርጎ ማለምን ከኦዴፓ ይማር!! (ሚኪ አምሀራ)

አዴፓ ግቡን ራቅ አድርጎ ማለምን ከኦዴፓ ይማር!!
ሚኪ አምሀራ
ኦህዴድ/ኦዴፓ በድንገት አይደለም ወደ መሪነት የመጣዉ፡፡ ለባለፉት 10 አመታት ሲሰራበት ቆይቶ ነዉ፡፡ አባሎችን ሲመለምል፤ ሲያስተምር፤ በዉጭ ሀገራት አካባቢ ባሉ ኤምባሲዎች ሲመድብ ሲመክር ኖሮ ነዉ፡፡ አሁን ላይ ያሉት ዋና ዋና የኦህዴድ ሰወች ባብዛኛዉ በባለፉት 10 አመታት ፖለቲካል ሳይንስ፤ ፖሊሲ፤ ሊደርሽፕ እና አድሚኒስትሬሽን እና በመሳሰሉት ሙያዎቸ ሲሰለጥኑ እና የሀገሪቱን የማህል አገር ፖለቲካ በንቃት ሲከታተሉ የቆዩ ናቸዉ፡፡ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዉጭ ተጽእኖ በቅርቡ ነጻ አይሆንም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እነ አሜሪካ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በተለይም የአመራር ምርጫ፤ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ እና የአካባቢዉ ጂኦ ፖለቲክስ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖዉ ይቀጥላል፡፡ ህወሃት 27 አመት ሲመራ ይሄን በማወቁ ከሀገር ዉስጥ ፖለቲካዉ ይለቅ የዉጭ ጉዳይ ላይ አተኩሮ ነበር፡፡ መለስ ዜናዊ ጠቅላይ ሚኒስቴር ነበር ከማለት ይልቅ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ዌስተርኖች ከህወሃት ዉጭ ለረዥም ጊዜ ሰዉ አልታያቸዉ ብሎ ነበር፡፡ ህወሃት አማራን እንደ ደርግ ኦሮሞን እንደ ገንጣይ ለዉጭዉ አለም በመሳል በጥርጣሬ እንዲታዩ ተደርጎ ቆይቷል፡፡ ህወሃት ከዚህም አልፋ የራሷን ሰወች በአለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ እንዲገቡ እድሉን ተጠቅማበታለች፡፡ ኦህዴድ እንደመጣ አካባቢ በአሜሪካ አለመታመኑ እነ ለማ መገርሳን ሁሉ አበሳጭቶ ነበር፡፡ እነ ወርቅነህ ገበየሁን በተደጋጋሚ ዋሽንግተን ዲሲ በመላክ እንዲሁም ግርማ ብሩን (በወቅቱ በአሜሪካ አምባሳደር) በመጠቀም የኦህዴድን ፍላጎት በማስረዳት ከጊዜ በኋላ አሜሪካኖችን መማረክ ችለዋል፡፡ ይሄን ባንድ ወቅት ሊያናግሩን ፈቃደኛ ያልነበሩ አገሮች ሁሉ አሁን ጉልበታችን እየሳሙ ነዉ ሲል አቶ ለማ ገልጻል፡፡
ኢህአዴግ በህይወት ከቀጠለ እንዲሁም ምርጫወችን የሚያሸንፉ ከሆነ አዴፓ ቀጣይ የመሪነት አድል አለዉ፡፡ ይሄም የሚቀጥሉት 5 እና 6 አመታት አዴፓ እቅድ አዉጥቶ እራሱን እና አባሎችን በትምህርት፤ በፖለቲካ  እና በመሪነት ጥበብ እያዘጋጀ መጠበቅ አለበት፡፡ በባህርዳር ፖለቲካ ቢዚ መሆን የለበትም፡፡ የመሃል አገር ፖለቲካ እና የዉጭ ግንኙነት አካባቢ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማሳየት አለበት፡፡ ዝም ብሎ ተደብቆ ኑሮ በኋላ መሪ አድርጉኝ ቢል የሚሰማዉ የለም፡፡ምክትል እየሆኑ መኖርም አያዋጣም፡፡ ለምሳሌ እነ ዶ/ር አምባቸዉን ወይም ሌሎች የተሻሉትን ፈልጎ ወደ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካባቢ እንዲሄዱ ማድረግ ነዉ፡፡ አዴፓ ሰወችን ለአምባሳደርነት ሲመድብም እራሱን የሚጎዱ ሰወች መሆን የለበትም ይልቁን ድርጅቱን የሚያኮሩ እና አቅም ያላቸዉ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ለማንኛዉም ራቅ አድርገን ማለም አለብን፡፡
Filed in: Amharic