>

በቶን የሚለካ የታሪክ ማስረጃ ይዞ በፈጠራ ወሬ ተንበርካኪው አዴፓ !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

በቶን የሚለካ የታሪክ ማስረጃ ይዞ በፈጠራ ወሬ ተንበርካኪው አዴፓ !!!
አቻምየለህ ታምሩ
የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞች ወልቃይትንና ራያን በሚመለከት ምኒልክ ከትግራይ የወሰዷቸው ናቸው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ጎንደርና ወሎ ያካተቱት ነው፤ ወዘተ እያሉ ትግራይን ለማስፋፋት የሚደርቱት ትርክት  የፈጠራ ታሪክ ነው!!!
አዴፓ ያወጣውን መግለጫ አዳመጥሁት።  የዛሬው  የአዴፓ መግለጫ ከዚህ በፊት ብአዴን ያወጣቸው  ከነበሩት መግለጫዎች የተሻለ ሊባል የሚችል  መግለጫ  ነው። በመግለጫው የወጣትነት ጊዜያችንን ሰውተን ላለፉት ዓመታት የታገልንላቸውና ለሞት የቆረጡ የአማራ ልጆች የተዋደቁላቸውን  የተወሰኑ አላማዎች ለማካተት ተሞክሯል። በርግጥ ዋናው ነገር መግለጫ ማውጣቱ አይደለም። ትልቁ ነገር መግለጫውን ተግባር ላይ ማዋሉ ነው። መግለጫው ተግባር ላይ እስካልዋለ ድረስ ትርጉም የለውም።  ለምሳሌ የአማራ ወጣቶች «ድርጅታችን አዴፓ ከወሰንና ከማንነት ጋር በተያያዘ የሕዝብ ጥያቄዎች ታሪካዊ ዳራቸውን ጠብቀው እንዲፈቱ ያደርጋል» በሚል የቀረበው  የመግለጫው ክፍል ሳይውል ሳያድር ወደ መሬት እንዲወርድ ይፈልጋሉ።
የኢትዮጵያ ታሪክ በጽሑፍ መስፈር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ተከዜንና አሸንጌን ተሻግራ አታውቅም።  የወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኞች ወልቃይትንና ራያን በሚመለከት ምኒልክ ከትግራይ የወሰዷቸው ናቸው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ጎንደርና ወሎ ያካተቱት ነው፤ ወዘተ እያሉ ትግራይን ለማስፋፋት የሚደርቱት ትርክት  የፈጠራ ታሪክ ነው። ኒዮርክ ከሚያስተምረው ከገላውዲዎስ አርአያ ጀምሮ  ከወያኔ ፕሮግራም አቀንቃኝ  ብሔርተኞች ሁሉ ጋር ባለፉት ሶስት ዓመታት  ባደረግነው  ክርክር  አንድም ሰው  እኔ ያቀረብኋቸውን የታሪክ  ማስረጃዎች የሚረታ፤ ዳግማዊ  ምኒልክና  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  ወስደውብናል  የሚለውን ትርክታቸውን የሚያሳይ  ብጣሽ  የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም።
ስለዚህ ወልቃይት  በግፍ ወደ ትግራይ የተካተተ፤ እስከ አሸንጌ ያለው የራያ ክፍልም  ለም መሬት ፍለጋ ባላገሩን እያፈናቀሉ በወረራ የተያዙ  የጎንደር/ ስሜን ጠቅላይ ግዛትና የወሎ አካል እንጂ የትግራይ ኖረው አያውቁምና  ወደ ነበሩበት ይዞታቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም የአዴፓ አባላት  ወልቃይትና እስከ አሸንጌ  ድረስ ያለውን  የራያ መሬት የጎንደርና  የወሎ ክፍሎች መሆናቸውን  የሚያሳይ በቶን የሚለካ ማስረጃ እንዳለን አውቀው፤  መሬቶቹን በወረራ ለመውሰድ ወያኔ የፈበረከውን ትርክት የሚደግፍ አንዳች ነገር እንዴለሌ በመገንዘብ  ለትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታ ሲባል  በወረራ የተወሰዱትን  የጎንደርና የወሎ መሬቶች  ባስቸኳይ ለማስመለስ ያለርሕራሔ መግፋት አለባቸው።
አዴፓ ያወጣው መግለጫ በአማራ ላይ ስለተካሄደው የዘር ማጥፋት አንዳች ያለው ነገር የለም። አዲሶቹ የአዴፓ አባላትም ይህንን አያውቁ ይሆን?  በፋሽስት ወያኔ የአገዛዝ ዘመን በአማራ ላይ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት እውቅና እንዲሰጠውና የዘር ማጥፋት ለተፈጸመባቸው አማሮች የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው መታገል የእውነተኛ የሕዝብ ልጆች አላማ መሆን ይገባዋል!
ሌላው በመግለጫው የተካተተው  ላመታት ከፍ አድርገን ስንሟገትለት የነበረው  ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ የ ያ ትውልድ  የታሪክ ትርክትንም ለማስተካከል እንደሚሰራ መጠቀሱ አበረታች ነው። ሆኖም ግን አሁንም አዴፓ ከድሮው ትርክት አልተላቀቀም። እንደ ብአዴን  ምክትልነትን እንጂ ዋናውን የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን እንደማይመኝ በሚያሳብቅ መልኩ  ሕዝብን እመራለሁ እንደሚል ፓርቲ  ኢትዮጵያ የመምራቱ  ድርሻ ይገባኛል የሚል ሀሳብ  በመግለጫው ሽታው የለም።
አዴፓ ማዕከላዊውን ሥልጣን በሚመለከት አንዳች ነገር  ትንፍሽ  እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያ የገዛ አማራ ነው የሚለውን የፈጠራ ትርክት ስለተቀበለ  ይመስላል።  እውነታው ግን ባለፉት መቶ አመታት አማራ የሆነ የኢትዮጵያ መሪ ኖሮ አያውቅም። የመጨረሻው አማራ የኢትዮጵያ መሪ ልጅ እያሱ ናቸው። ኦነግ ልጅ እያሱ ያልነገሱት ኦሮሞ ስለሆኑ ነው ይላል። ይህ ግን የሚመረምር ስለሌላ የኦነግን ፕሮግራም ለመሸጥ የፈጥሩት እንጂ  እንጂ ልጅ እያሱ በእናትም በአባትም አማራ ናቸው። ልጅ እያሱ ራሳቸው  ከስብስቴ ነጋሲ ጀምረው በመቁጠር «የዘጠኝ አማራ ንጉሥ ልጅ» እያሉ ተሰማ እሼቴን ያስገጠሙት ግጥም አለ። ከመኢሶን ጦርነት በኋላ በአውሳ አድርገው በደሴ በኩል መቅደላ መሽገው ተፈሪን ለመውጋት በመዘጋጀት ላይ ሳሉ፤
መቅደላ አፋፉ ላይ ያስካካል ፈረሱ፣
የአማራው ተወላጅ የዘጠኝ ንጉሥ ልጅ ዐስረኛው እሱ፣
እንኳን ሴቶቹና ወንዶቹም ቢነግሱ፣
አልጋውን አይለቅም አባ ጤና እያሱ፤
በማለት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ብቻ ሳይሆን ተፈሪም ቢነግሡ  አልጋቸውን እንደማይለቁ  ወታደሮቻቸው እንዲያቅራሩ አድርገዋል።
ልጅ እያሱ ባባታቸው በንጉሥ ሚካኤል በኩልም  የዘር ሐረጋቸውን  እስከ ዐፄ ፋሲል ድረስ የመዘዙበት ዝርዝር በእጃችን ይገኛል።
መመዘኛው «ዘር» ከሆነ  ባለፉት መቶ አመታት ውስጥ  ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ  እስከ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ድረስ ኢትዮጵያን  የገዙት ኦሮሞዎች ናቸው። ማንም  የማይመረምር ኦነጋዊ እየተነሳ  ኦነግ «ኦሮምያ» የምትባል አገር ለመመስረት  የፈጠረውን  ትርክት እያነሳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴናን ሻለቃ መንግሥቱን ሁለቱም ኦሮሞ ነን እያሉ አማራ ሊያደርጋቸው ቢፈልግ እውነታውን ሊለውጠው አይችልም። ስለዚህ አዴፓ  ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገል ፓርቲ እስከሆነ ድረስ  ለምክትልነት ብቻ ሳይሆን ላለፉት መቶ አመታት  ከልጅ እያሱ ዘመን ወዲህ  በኢትዮጵያ የመሪነት ቦታ ያልነበረውን  አማራ ለማዕከላዊ ሥልጣን ተሻሚነት ብሎም  ለዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት እንዲበቃል መታገል ይኖርበታል። የአማራ ትግል  በውሸት ትክርት ላይ ተመስርቶ ምክትልነትን ነባር ይዞታው ካደረገው የብአዴን አስተሳሰብ ተላቆ ለፖለቲካ ሥልጣን እንደሚታገል ፓርቲ  ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለመግባት በዋናነት ማማተር ይኖርበታል።
Filed in: Amharic