>

የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤና የህወሓት አማራጮች (ያሬድ ጥበቡ)

የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤና የህወሓት አማራጮች
ያሬድ ጥበቡ
የህወሓት 13ኛ ጉባኤ መዝጊያ ላይ አምባሳደር ስዩም መስፍን ያደረጉትን ንግግር በጥሞና አዳመጥኩ ። ህወሓት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነቱ ፈቀቅ እንደማይል ነው የተናገሩት ። በአንድ በኩል ኢህአዴግ መቀጠሉና አለመሰባበሩ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ፣ ውስጣዊ አንድነቱን ካልጠበቀ ግን ቀጣይነቱን ችግር ላይ ይጥለዋል ። አባል ድርጅቶቹን ስለማያስማማ አብዪታዊ ዴሞክራሲ አቃፊ ርእዮት መሆን የሚችል አይመስለኝም ። ሆኖም የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ፖለቲካ አሽቀንጥሮ ኢኮኖሚውን አጥብቆ መያዝ አደራዳሪ ሃሳብ ይመስለኛል ። መለስ ከበረሃ ቀናት ጀምሮ በ”ነፃ ብሄራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ” ጀምሮት የነበረውን እሳቤ አሳድጎ በሥልጣን ዘመኑ ወደ “ልማታዊ መንግስት” አስተሳሰብ አስመንድጎ፣ ታሪክ ሰርቶ አልፏል ። ህወሓት ይህን ተአምር የፈጠረ እሳቤ ዝም ብዬ አልወረውርም ነው የሚለው ። ተገቢ ክርክር ነው ። ኢህአዴግስ ቢሆን የአብዪታዊ ዴሞክራሲን የልማታዊ መንግስት እሳቤ አሽቀንጥሮ በምን ሊተካው ነው? በገበያ ኢኮኖሚ? አይመስለኝም ።
በአንፃሩ የአብዪታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካ አፋኝ፣ ገዳይና ጥፍር ነቃይ ፣ ጠርሙስ ዉሃ ብልት ላይ አንጠልጣይ መሆኑ ተጋልጧል ። በአቢይ የመደመር ትህትና የስደትና የእስርቤት በሮች ተከፍተው ስደተኞችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነፃ ወጥተዋል ፣ በዚህም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካ ተቀብሯል ። ህወሓት የተቀበረን ነገር መሻት የለበትም ። ስለሆነም፣ የአብዪታዊ ዴሞክራሲን ኢኮኖሚ ክርክሩን ጠበቅ አድርጎ ይዞ ፣ ጥፋት ያደረሰውን የፖለቲካ ገፅታውን በመተው ከቀሩት የኢህአዴግ ድርጅቶች ጋር በመተማመንና በአንድነት መቀጠል የሚችልበትን ሁኔታ ቢያመቻች ተገቢ መስሎ ይሰማኛል ። የህወሓት መሪዎች ለሁኔታው የሚመጥን ሰጥቶ መቀበል ለማድረግ ሃሞት / መኣንጣ ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።
በተጨማሪም፣ ህወሓት በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ የሚኖሩትን ተጋሩ ፍላጎት ብቻ የሚወክል ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ ያሉትንም ባለሃብቶች ጥቅም የሚወክል በመሆኑ፣ በአሁኑ ሰአት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅቶች ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ ያደረሰውን አለመረጋጋት መፍትሄ ለማስገኘት፣ ከዚህ በፊት በህወሓት አቀንቃኝነት በአዲስ አበባ ላይ የተጣለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልክ የማስያዝና የከተማዋ ነዋሪዎች ሉአላዊ ባለቤቶቿ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ትግል እንድታደርጉ አደራ ማለት እወዳለሁ ። የሞራል ግዴታም አለባችሁ ። የህወሓትን የፖለቲካ ሥልጣን ለማስጠበቅ ይጠቅማል ብላችሁ በማሰብ የኢትዮጵያንና የኦሮሞ ብሄርተኝነቶችን በማጋጨት ያሰላሰላችሁት ስልት ያደረሰው ጥፋት በመሆኑ፣ አሁን የበደላችሁትን ለመካስ እድሉ ስላላችሁና ፣ ይህን ብታደርጉ በአዲስ አበባ ውስጥ ያላችሁንም ስም ለማደስ ሊጠቅማችሁ ስለሚችልና፣ በዚህ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ድጋፍም እንደምታገኙ እርግጠኛ በመሆኔ፣ ለአመታት የቆየውን የመጠላለፍ ፓለቲካ አስወግዳችሁ፣ በግልፅና  በመድረክ በሚካሄድ የፖለቲካ ትግል እንድትተኩት አደራ ማለት እወዳለሁ። ፈጣሪ ቀናውን እንዲያሳያችሁ ፀሎቴ ነው ።
Filed in: Amharic