>

ለውጥ እና ለቀድሞ ባለስልጣን የይቅርታና የፍትህ ጥያቄ !!! (ሞሀመድ ኤ እንድሪስ)

ለውጥ እና ለቀድሞ ባለስልጣን የይቅርታና የፍትህ ጥያቄ !!!
ሞሀመድ ኤ እንድሪስ
ከአንድ ስርአት ወደሌላ ስርአት፣ ከአንድ መንግስት ወደ ሌላ መንግስት ወይንም በአንድ መንግስት ውስጥ ስር ነቀል ሊባል የሚችል ለውጥ ሲካሄድ የአዲሱን ጉዞ የሚጎትቱ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ አንዱ በቀደመው ግዜ ሹማምንት የነበሩ እና ህዝብ ከፍተኛ ብሶት የሚያሰማባቸው አልያም በቀጥታ በወንጀል የተሳተፉ ባለስልጣናት ጉዳይ ነው፡፡  ይህ በሁሉም ሀገራት ከአንባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር ወቅት የሚያጋጥም እና ሀገራዊ መፍትሄ የሚሻ ነው፡፡ ሀገራዊ ስንል በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር፣ መንግስት በሚመራው ህጋዊ እና ማህበረሰባዊ አካሄድ ውስጥ በሚያልፍ በውል በሚታወቅ ሂደት የሚተገበር ለማለት ነው፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ሽግግሩን ውጤታማ ለማድረግ መንግስታት እርቅ እና ሰላም የማውረድ (Reconciliation) ወይንም የሽግግር ግዜ ፍትህን ማስፈፀም (Transitional Justice) እንአማራጭ ይጠቀማሉ፡፡ የዶክተር አብ መንግስት ሁለቱንም መርሀቸውን ጠብቆ አልተገበራቸውም፡፡ ሀገራዊ ይቅርታ እና መደመር ስሌትም ወደታች ሲወርድ በምን አተገባበር ፍትሀዊ ሆኖ እደሚቀጥል ማሳያ የለውም፡፡ በዚህም ምክንያት ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በተናጠል ያላቸው አቅም አሁንም ጠንካራ መሆኑ ግለሰብ ባለስልጣንትን በተናጠል የመዳኘት እድሉ በቀላሉ የማይታሰብ ነው የሚሆነው፡፡
የዶክተር አብይ መንግስት ወደስልጣን ከመጣ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ህዝብ የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናትን በራሱ የመዳኘት ዝንባሌ ያሳየባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡ በተለይ በኛ ሀገር ህዝብን በወል የሚበድሉ እንዳሉ ሁሉ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ብቻውን በደል አድርሶብኛል ብሎ የሚይዛቸው አመራሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ባለስልጣን በህግ እና በህግ ብቻ ስለማይመራ ኢ-ፍትሀዊነቱ ከቦታ ቦታ፣ ከባለስልጣን ባለስልጣን እንዲሁም ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል፡፡ ይህ ሁኔታ የህዝብ ብሶት የሚነሳባቸው ብዙዎቹ ባለስልጣናት የስርአቱ አስፈፃሚዎች ከመሆናቸው ውጭ የጋራ ወጥ የሆነ መለኪያ ሊቀመጥላቸው አይችልም፡፡ በመሆኑም ሁሉም ጉዳዮችን ከህግ እና ሀገር አንፃር ከመሆኑ ይልቅ ከብሶቱ እና ከርሱ ተጨባጭ በመነሳት ተገቢ ነው የሚለውን አቋም ይወስዳል፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የአቶ በረከት መኪና ተብሎ በተገመተ ተሸከርካሪ ላይ የተወሰደው እርምጃ አንዱ የቅርብ ግዜ ማሳያ ነው፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ  በአቶ ጌታቸው አሰፋ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ መመረጥ እና በሀዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ ተሳታፊ የመሆን አጋጣሚ አለ በሚል መነሻ የዶክተር አብይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ ዋና ዋና የሚባሉ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሳይቀር ሲጠይቁ ይታያል፡ በዚሁ ሰሞን በአቶ ጁኔዲን ሳዶ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በተለየ መልኩ አደባባይ ወጥተው ይቅርታ ይጠይቁ የሚል ጥያቄ ሲደመጥ ነበር፡፡ ሁሉንም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው በመንግስት አቅጣጫ ውስጥ የማይፈሱ፣ ሀገራዊ ወጥነት የሌላቸው፣ ለህጋዊ እና ፍትሀዊነታቸው የጋራ ስምምነት የሌላቸው መሆኑ እና ብዙ መሰዋእትነት ለተከፈለበት ለውጥ ያላቸው አሉታዊ እና አዎንታዊ ጠቀሜታ ያልተሰላ መሆናቸው ነው፡፡
ስለ Reconciliation እና Transitional Justice ምንነትና አተገባበር ወደፊት በሰፊው መወያየታችን አይቀርም፡፡ ይህ ፅሁፍ ከሰሞኑ ከተነሱ የአንድ ማህበረሰብ ክፍሎች (የተወሰኑ ሙስሊም ፌስቡከሮች) ከነበረ ብሶት በመነሳት በራሳቸው ባስቀመጡት መስፈርት ለቀድሞው ሚኒስር አቶ ጁኔዲን ያቀረቡትን የይፋ ይቅርታ ይጠይቅ ጥየቄ መነሻ በማድረግ በተለያዩ ገፆች ላይ በነበሩ ውይይቶች የሰጠኋቸውን አስተያየቶች በሶስት ምክንያቶች ሰብሰብ አድርጌ ላመጣቸው ወደድኩ፡፡ አንድ ይህ ጉዳይ ሀገራዊ መፍትሄ እስካልተሰጠው ድረስ ነገ በሌሎች ባለስልጣናትም በተናጠል የመነሳት እድሉ ሰፊ ስለሆነ፡፡ ሁለት አስተያየቶቹን በገፄ ላይ ሰፍረው እንዲቆዩ ለማድረግና በሶስተኛ ደረጃ ለቀጣይ ውይይት መስፈንጠሪያ እንዲሆኑ፡፡
ከመርህ ጋር በተያዘ
ከባለስልጣናት ይቅርታ ጋር በተያያዘ የመርህ ጥያቄ የሚሆነው መንግስት ስርአቱን እና ባለስልጣናቱን በሙሉ ወክሎ ይቅርታ ሲጠይቅ “ይቅርታው እነ እከሌን ሊያካትት አይገባውም” የሚል ጥያቄ ቢቀርብ፣ ከዚህ በፊት በየመድረኩ መንግስትንም ሆነ የበደሉንን ይቅር ብለናል ሲባል “እነ እከሌ አይመለከታቸውም ቢባል ” እና መሰል ጥያቄዎች ናቸው የመርህ ሊባሉ የሚችሉት። ከዚያ ውጭ ያለው መንግስት በይፋ ይቅርታ ጠይቆበት ህዝብ ቅሬታ ያላቀረበበት አጀንዳን የማስፈፀም ሂደት ነው ብዬ የማስበው
ይቅርታ እና ፍትህ
በባለስጣናቱ ላይ እየተነሳ ያለው እያንዳንዱ የፖለቲካ አመራር ባጠፋው ጥፋት ልክ ለተለያየ የህብረተሰብ ክፍል እየወጣ ይቅርታ ይበል የሚል የፍትህ ይሁን የፖለቲካ ጥያቄ መለየት የማይቻል ነው።
ከጌታቸው አሰፋ ጋር ተያይዞ ለተነሳው እኔ የሚታየኝ ጉዳዩን የአብይ መንግስት ከትራንዚሽናል ጀስቲስ አንፃር የሚያየው ከሆነ በጥፋታቸው መጠየቅ ያለባቸው በተዋረድ መጠየቅ አለባቸው። ይሄ ብዙ የሚያወያይ አይደለም። የአብይ መንግስት በይቅርታ ፍሬምዎርክ ለመዳኘት ከወሰነ እና ህዝቡ ይቅርታው ሊያካትታቸው አይገባም ብሎ ተቃውሞ የሚያደርግ ከሆነ ያ የመርህ ጥያቄ ነው ለለውጡ ያስኬዳል ከተባለ ከሀይማኖትና ከብሔር ምልከታ በመውጣት ኦብጀክቲቭሊ ማየት ይፈልጋል። ከዚያ ውጭ ኢህአዴግ እነሽፈራውንም እነበረከትንም ጨምሮ ነባር ኢህአዴጎችን “በክብር” እያሰናበተ ለሌሎች የምናስቀምጠው የመለያ መስፈርቱ ለግዜው ሰብጀክቲቭ መሆኑ አይቀርም። ዋናው ነጥቤ ወይ ለሁሉም የሚሰራ መርህ እንያዝ ወይንም መንግስቱ የመረጠውቨን መርህ ስሜት ሳይጫነን እንቀበል ነው
የተናጠል ይቅርታን በተመለከተ
የአቶ ጁኔዲንን ይቅርታ የመጠየቅ ጉዳይ ለመረዳት እና ለማስረዳት በዚህ ርቀት የመጓዝን አካሄድ አልደግፍም። ስርአቱ ላጠፋው ጥፋት በተወካያቸው በዶክተር አብይ እና በአራቱ ፓርቲዎች በኩል በይፋና በተደጋጋሚ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ ከነሰሩት ጥፋት በስልጣን ላይ ላሉትም፣ ለተባረረቱም፣ ለሞቱትም ባለስልጣናት መንግስት ሀላፊነቱን ወስዶ የጠየቀው ይቅርታ ነው። ፖለቲካዊ አግባብነትም ያለው ይሄው ነው።
ከዚያ ውጭ በአንድ በተበላሸ ስርአት ውስጥ ያሉ እያንዳንዱ አስፈፃሚዎች ለተለያየ የህብረተሰብ ክፍል በተናጠል ይቅርታ ይጠይቁ ማለት አንድም እራስን እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ የተጠየቀው ይቅርታ የማይመለከተኝ ገለልተኛ አካል ነኝ ከማለት አልያም ፖለቲከኞችን በኛ በራሳችን ህግ እንዳኝ የሚል የተሳሳተ አመለካከት የወለደው ተደርጎ ነው የሚወሰደው። መንግስት ስህተት መስራቱን በግልፅ ሙስሊሙን በመጥቀስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ገልፁዋል። አንዳንዱ ባለስልጣን ሀይማኖተኞች ላይ ለደረሰው በደል የበለጠ እጁ አለበት ከተባለ፣ ሌላው የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመበደል ብዙ ሚና ነበረው ከተባለ፣ መንግስት የወሰደው ሀላፊነት ቀርቶ ሁሉም በተናጠል በመንግስት ተገዶ እጁን ላስገባበት ጉዳይ ሁሉ ይቅርታ ይጠይቅ የሚለው አስተሳሰብ በየመንግስት መዋቅሩ እየወረደ የትጋ ሊቆም ነው።
የዘገየ ይቅርታን በተመለከተ
ሀ) ሁሉም ባለስልጣናት ለውጥ አይቀሬ መሆኑን እስኪያምኑና አደጋው አፍንጫቸው ስር እስኪመጣ ሲሻቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሲፈልጉ እድገቱ የወለደው ችግር ነው እያሉ እራሳቸውን ንፁህ ሲያደርጉ ነበር። እስከማውቀውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደመንግስት ከጠየቁት ይቅርታ ውጭ የተጠየቀ የተናጠል ይቅርታ የለም። አቶ ጁነዲን አንድም በግሉ ሳይሆን ጥፋት የሰራው እንደስርአቱ አካል በመሆኑ በግሉ መጠየቅ ላይኖርበት ይችላል አልያም አስገዳጅ ሁኔታ እስኪገጥመው አዘግይቶ ሊሆን ይችላል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ወደ ፖለቲካ እየተንደረደር ላለ ሰው መረዳት አይከብድም፡፡ ሌላው አቶ ጁነዲን በኢህአዴግ ውስጥ ወክሎ የገባው “የመረጠውን አካባቢ” እንደመሆኑ ይቅርታ መጠየቅ ካለበት “ለመራጩ ህዝብ” ነው። ይህም ፖለቲካሊ ምን ማለት እንደሆነ አጥርተን ካልሄድን እያኮበኮቡ ያሉ አማተር ፖለቲከኞቻችን እጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው የሚሆነው፡፡
Filed in: Amharic