>
5:13 pm - Sunday April 18, 2956

የመፅሐፍ ቅኝት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ)  

የመፅሐፍ ቅኝት 

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ – ጎንደር

የመፅሃፉ ርዕስ፡ የኤርትራ ሕልምና ሌሎች የኢትኖግራፊ ወጎች

ደራሲ፡ አፈንዲ ሙተቂ                                

ገፅ፡ 225

መግቢያ

መፅሃፉ በሰባት ምዕራፎች፣ በበርካታ ንዑስ ርዕሶችና በየትየለሌ ጭብጦች (ቁምነገሮች) ላይ ያተኮረ የወግ ድርሳን ነው፡፡ ደራሲው ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር በሚያሳብቅ መልኩ ሁሉንም ምእራፎች የሚጀምረው በሙዚቃ ነበር፡፡ ሙዚቃ የመጣጥፎቹ ሁሉ መጀመሪያ ስለሆነ አርዕስቱን ስንተዋወቅ እስኪ በየትኛው ሙዚቃ ተሰናስኖ የቀረበ መሆኑን እግረ መንገዳችንን እንመልከት፡፡ ሀረርጌን የተመለከተውን የመጀመሪያ ምእራፍ በገናናው ሙዚቀኛ ማህሙድ አህመድ “የብርቱካን ጭማቂ” ዜማ ከራሱ የኦሮሞ ማንነት ጋር ከሽኖ በማስተዋወቅ አሃዱ አለ፤ ምዕራፍ ሁለትን ደግሞ በሌላኛው ዕውቅ ዜመኛ ጌታቸው ካሳ “የከረመ ፍቅር”ን እያንቆረቆረ ጂማን በተሚማ ትዝታ አስጎበኘን፤ መች በዚህ አብቅቶ ትግራይን በሶስተኛው ምዕራፍ ሲያስጎበኘንም ሙዚቃ አልነጠፈበትም፤ ይኸውም ዝነኛው የባሕታ ገብረሕይወትን ትግርኛ ሙዚቃውን ያንቆረቁርን ነበር፤ ጎንደርን ሲያወሳ ቃሉን ባላወቀበት ዕድሜ አያሌው መንበር የተባለ የልጅነት ጓዱ ሀረር ከተማ ላይ ያዜመለተን አማሮ-እንግሊዝኛ ዜማ በሚኒሊክ ወስናቸው ትዝታ አያረጅም ፈረስ ጋልቦ ያስነብበናል፤ በምዕራፍ አምስት ወደጉራጌ የወሰደን አፈንዲ የአርጋው በዳሶ “አለም ብሬ ነይ ነይ” ማጀቢያው ነበር፤ በምዕራፍ አምስት “አንቺየ ጎጃምን ያላችሁ ውረዱ እንያችሁ” በተሰኘው ዜማ አባይ በርሃ ይዞን ወርዶ ጎጃም ያሻግረናል፤ በመጨረሻው ምዕራፍ በወጣት ኤርትራውያኑ መዝሙር ጀምሮ ሀገረ ኤርትራን በሰፊው ያስጎበኘናል፡፡ እኔም እስኪ ከንባቤ ቱርፋት በየምዕራፉ የሸነጡኝን ጭብቶች በአጭሩ ላውራላችሁ፤ ለሙሉ ንባብ ለማነቃቃት ያሕል፡፡  

ምዕራፍ አንድ – የሀረርጌ ኦሮሞ ነኝ – እኔ ማንም ነኝ፤ ግለሰብ ነኝ፤ ሀረርጌ ነኝ፤ አሮሞ ያውም የሃረርጌ፣ የምስራቅ ሰው፣ ኢትዮጵያዊ በማለት ዘርፈ ብዙ ማንነቱን የሚያወሳው ደራሲው በሙዚቃዊ ጅማሮው ወጥኖ፣ በቋንቋው ሰድሮ፤ በምግብ መጠጡ፣ በአልባስ በጌጡ ሞሽሮ፤ በጨዋታ፣ ፌዝ፣ ቁምነገሩ አስወቦ፤ በግብርና በሰርግ በጎሳ ስርዓቱ ክቦ የማንነቱን ትውውቅ ሲያጠናቅቅ አንዲህ ብላችሁ ጥሩኝ ይላል፤ አፈንዲ ሙተቂ፤ ወልደ ገለምሶ፤ ዘምድረ ሐረርጌ፤ ወነገደ ኢቱ፤ ወዘብሔረ ኦሮሞ፤  ወ-ሀገረ ኢትዮጵያ አከተመ፤ መጠሪያው ነው ተዋወቁት፡፡ ከዚህ የማንነት መጠሪያና በርካታ ዕሴቶች መኖር ማማ ላይ ለመውጣት ግን ፈርጀ ብዙ የማንነቱ አለባውያን፣ የኑሮ ብሂሎቹ ይጠቀሳሉ፤ ከመሰረታውያኑ ምግብና መጠጥ፣ አልባሳት፣ መጠለያ ጀምሮ እስከ ጎሳ ስርዓቱ ድረስ ይወሳሉ፡፡ ምግብና መጠጥ፡ ወተት “ከሲልላ” (እንገር) እስከ “ወሌምቦ” (አይብ) ድረስ በቂጣ አጣጥሞ ጠጥቶ፣ “ጉድ መጣ ጉድ መጣ ገንፎ ዛፍ ላይ ወጣ” ሲባል በመላ ሃገሪቱ በእንቆቅልሽ የሚወደውን ሙዙን በተለይም የአዋሬ ሙዝ በአይነት ገምጦ፣ ሸንኮራውን መጥጦ፣ ፍራፍሬውን ተመግቦ ያደገ ሲሆን፤ በጨዋታ መዝሙሮቹ ደግሞ ከሸጎየ፣ ረገዳ፣ ሂቦ፣ ኩኩ መለኮቴ፣ እንቆቅልሹ፣ ተዩን ተይ (እንቆቅልሽ መሰል ጨዋታ)፣ ዶጋ ነስሪ (ተረት)፣ ከብት እገዳና ወፍ ጥበቃውን ከውኖ፣ ከማሽላ ልዩ ፍቅር ሰፍሮ ያደገ፤ ከግብርናው (ዘር፣ አረም፣ ጉልጓሎ) ተሳትፎ፣ የሰርግ ስርዓቱን “ከቃድማ” (ከእጮኝነት) እስከ “ጫብሳ” (በሽምግልና አቋራጭ ጋብቻ) ከውኖ፣ በጎሳ ስርዓቱ (ኢቱ ነገድ፣ ቃሉ ጎሳ) ሱታፌ የተሰራ ማንነት ነው፡፡

በዚህ ሁሉ መሰራት ውስጥ ያሉ አስተምህሮቶች መዘርዘር ከባድ ቢሆንም ቅሉ በጥቂቱ፤ የምግብና መጠጥ ስሪቱ፣ የከብቶቹ ስያሜ፣ ውዳሴያቸው፣ የማሽላው ዝርያ፣ የሕብረት ስራ ማህበራቱ ጉዛ ይለዋል ደራሲው (ደበያት- በጎንደር፣ ወንፈል (ልፍንቲ) ትግራይ፣ ጅጌ – ኦሮሚያ ወዘተ የሚሰኙ አንደሆኑ የሚታወቁትን ካሕሣይ ገ/እግዚአብሄር የተሰኙ የዘርፉ ተመራማሪ ይጠቅሳሉ)፣ የማሽላ ጉድጓድ ስራ፣ ህብረ ዝማሬ፣ የማሽላ እንጀራ ዝግጅቱ፣ የሰርግ ዘፈኖቹ (የወጣቶች፣ ደቺሳና ረገዳ፣ የኮረዶች ሄሌ)፣ የጎሳና ነገድ ባህላዊ ስርዓት (የጎሳ አደረጃጀት፣ የጎሳ ሃላፊነቶች፣ ዋቄ ፈናን የኦሮሞ ጥንታዊ ዕምነት፣ የቃሉ ጎሳ የተቀባነት፣ የቃሉ መንፈሳዊ መሪነትና የዓለም ስልጣን ጥዩፍነት፣ የቃሉ የቡራኬ መገለጫዎች (ከለቻ-በግንባር የሚደረግ ጌጥ፣ ከርቤ-ቅንድብ መቀንደቢያ፣ ጮኾ – አንካሴ መሳይ አነስተኛ ጦር፣ ቱፍታ – የምራቅ ፍንጣቂ – ይኸም ከራያ ጋር ምስስሎሽ ያለው ለመሆኑ አቶ በአካል ንጉሴ ያጠኑት የራያ ቆቦ ሸነቻ ጥናት ላይ ቱፉታ ክዋኔው ሲሆን ሸነቻ ቃል ግጥም አንደሆነ የሰነዱት ጥናታቸው ዋቢ ነው፤ በሁለቱ ህዝብ መሃል ምስስሎሹ ሊጠና የሚገባው ሆኖ ሌላኛው ተመሳስሎ ራያን የሚያወሳው የስነፅሁፍ ዘርፋቸው “ሚሪግዱ” የተሰኜው የግጥምና ዜማ ስርዓት ነው፤ በመፅሃፉ ከተካተተው ሚሪግዱ የሚከተሉትን ሩብአያት ልውሰድ ለራያ መጠቀስ አብነት ይሆነኝ ዘንድ፤  

አኒያ ጸሎተኛ ነው፣ ማጣት የለበትም፤

ከረዩ ጀግና ነው፣ ፈሪ የለበትም፤

የወሎ ውበትማ ጉድለት የለበትም፤

ራያ ወገኔን ይላል፣ ተንኮል የለበትም፡፡  

ከዚህ ባሻገር ከዘመናዊው መንግስት መዋቅር ጋር የሚመሳሰል የጊቤ መንግስታት ከኦሮሞው አባ ገዳ ስርዓት ጋር በማዋቀር አቋቋመው ይጠቀሙበት የነበረውን ቢሮክራሲ መዋቅር በምስል እንመልከት፤     

ምስል 1፡ የጊቤ መንግስታት ከኦሮሞው አባገዳ ስርዓት ጋር አዋቅረው ያቋቋሙት የቢሮክራሲ መዋቅር

ምዕራፍ ሁለት – ጅማና ተሚማ – የከረመ ፍቅር (ትዝታ) ያንገላወዳቸው ደራሲውና የደራሲው የመንፈስ ፈረስ ደንገላሳ እየጋለቡ ጅማ ይዘውን ነጎዱ እናም “ሰላማካ ያገኔ ሰላማካ” እያሉ በጥቅሉ ለጅማ ጉብላሊቶች በሕሊናቸው የምስጢር ጓዳ ትውስታቸውን በጥላሁን ገሰሰ “ሰላማካ”፣ በሃጫሉ ሁንዴሳ “ሰኚ ሞቲ”፣ በአብደላ ሙሃመድ “አሸም አሸማ”፣ በሲቲና አብደላ “ብርቱካኒ” እና በንዋይ ደበበ “ከጊቤ ባሻገር” ሙዚቃዎች አጅበው አስጎበኙን፡፡ ደራሲው ጅማን ከዘፈኖቿ ባሻገር ባሉ መገለጫዎቿ በትንታኔ ያቀረበልን ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ቀልብን ሰቅዘው ከሚዙት መካከል፤  “ሂዳ ዳርቡ” (ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩትም ቅሉ ሎሚ ውርወራ መሰል የጂማ ልጃገረዶች ለወንዶች ፍቅራቸውን መግለጫ ክዋኔ)፣ “ሂን ሙስሂና” (እንጨት አትሁን) የሚል ትርጓሜ የተሰጠው እንግዶችን የማጫዎቻ ዘይቤ፣ የታሪክ ሃብታም ሲል የሚዘረዝራቸው የጅማ ቀደምት ታሪክ (የትራፊክ መብራቷ፣ የከተማ አውቶብስ፣ የአባ ጅፋር ሙዝየም፣ የመንግስት ምስረታዎች፣ መላ ኢትዮጵያን (ኤርትራና ጅቡቲን ጨምሮ) ተደራሽ ያደረጉ የንግድ መስመሮች፣ አሁን ድረስ ሙስሊም ሁሉ ነጋዴ የሚል ትርክት መነሻ ታሪክ አንዲሁም ኦሮሞን ሁሉ የጥንቱ የዋቄ ፈና ዕምነት ተከታይ አድርጎ ከማሰብ ተለምዷዊ አስተሳሰብ ጋር ተዛምዶ የቀረበበት ትንታኔ፣ የአባጅፋር የመድረሰተል ኮሌጅ ጅማሮ ወዘተ) ይገኙበታል፡፡ በመጨረሻም ደራሲው ይህን አጭር ኢትኖግራፊክ ወግ ከአሁን ቀደም “ሰተቴ” በተሰኘ ምርጥ ታሪክ ቀመስ ልብወለዳቸው በውብ ቋንቋና ስነፅሁፍ ችሎታቸው የጅማን ታሪክ ላስቃኙን የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ መታሰቢያ ሲያደርግ በከድር ሰተቴ ላይ የፃፍኳትን አጭር ቅኝት ዞር ብየ ተመልክቼ፤ ይገባቸዋል አልኩኝ! ባያንሳቸው!

ምዕራፍ ሶስት – ትግራይ የትንግርቶች እናት – የሙዚቃ ስልቶቿን፣ ከያኒዎቿን እየጠቃቀሰ በትግራይ መደመሙን ቀጥሎ የጥንታውያኑን የዳማትና የአክሱማውያን መንግስታት ገናናነት፣ ቀዳማዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑትን ከተሞች (አክሱም፣ የሃ፣ ውቅሮና ጎሎ መኸዳ) ጠቃቅሶ ጥንተ ታሪካቸውን ያትታል፤  የዳማትና የአክሱምን መተካካት፣ የግዕዝ ቋንቋ ሕያውነትና አሁን የደረሰበት ሁኔታ ከፊደል ገበታ ታሪክ ጋር አሰናስሎ ይተርክልናል፣ ውዳሴ አክሱም (ክርስትና አቡነ ሰላማ ያስገቡባት፣ መፅሃፍ ቅዱስ ወደ ግዕዝ የተተረጎመባት ጥንታዊት ስልጣኔ) ሲል ያቀርብላታል፣ ምስጋና ዘንጉሰ አልነጃሽ (እስልምናን በደግ ልቦና የተቀበለ፣ የቁረይሽ መሪዎችና የነብዩ መሐመድ (ሱ.ዐ.ወ) በችሎት መሰል አከራክሮ ርትዕ ፍርድ ያስቀመጠ፣ ለነብዩ መልዕክተኞች የሰጠው ምስክርነትም “ዛሬ የሰማሁት ሁሉ ሙሴና ኢየሱስ ካስተማሩት ትምህርት ተመሳሳይ ነው፡፡” የሚል እንደነበር፤ በመጨረሻም በነፃነት ይኖሩ ዘንድ ንጉሱ ፈቃዱ አንደሆነ በውብ የታሪክ ፍሰት ይተርክልናል፡፡     

ምዕራፍ አራት – ጎንደር እንዴት ነሽ? – የበርካ ነገስታት ምድር ጎንደርን በበዛ ውዳሴና ታሪካዊ ሁነቶች ብሎም የጎንደር ፍሬዎች ዝርዝር አጅቦ የሚያቀርብልን ደራሲው፤ የጎንደር የጥበብ ሰዎች አዝማሪዎቿን ጨምሮ ከደንበኛ ቤትና ቅኔያዊ ግጥሞቻቸው ጋር ኳኩሎ፣ አምባገነኑን መላኩ ተፈራ ከነመወድሱ፣ ዕውቁ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከስራዎቹ ጋር ይጠቃቅስና፣ ሊቁ አባ ገብረሃናን ብሎም አስገራሚውን ንጉስ አፄ ባካፋን ከቅኔ መምህራቸው ተዋነይ ጋር ከሚወሱበት ቅኔያቸው ጋር ያቀረበልን ሲሆን ደራሲው በአማርኛ ያቀረበው ቅኔ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር በአንድ ወቅት ካሳተማት ርዕሷን ከዘነጋሁት አጭር መፅሃፍ እንዳነበብኩት ግዕዙ ይበልጥ ገላጭ ነውና እንዲህ የሚል ነበር፤

ኢትርስዓ ባካፋ ዘተዋነይነ ክልኤነ

እስመ ከመ አቡሁ ለአብርሃም አንተ ወብዕሲቱ አነ፡፡

በማስከተልም አፄ በጉልበቱን የቋራው ካሳ ሃይሉ ከግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ተውኔት የመጀመሪያ ገቢር ስንኞችን ተውሶ ታሪኩን ባጭሩ አስነብቦን የጎንደር ጉብኝቱን ያከትማል፡፡    

ምዕራፍ አምስት – ሽርሽር በጉራጌ ምድር  – የጉራጌን ሕዝብ በላቡ በወዙ ሰርቶ አደር፣ የፋይናንስ ሳይንስ ምድር፣ የጥንካሬ ተምሳሌት ሕዝብ ሲል ይገልፀዋል፡፡ ጉራጌን “የኢትዮጵያ ጃፓን” ይለዋል፡፡ የጉራጌን  ቋንቋ፣ የምግብ (እንሰት)፣ የጎሳ፣ የስም አወጣጥ፣ የሰባት ቤት ጉራጌ መስተጋብር ከአጎራባች ማህበረሰቡ ጋር፣ “የጀካ” የተሰኘው የሸንጎ ስርዓታቸው፣ “ሴራ” የህግ ስርዓታቸው፣ አለንጋ የተባለ የመሬት ስሪት፣ እድሮች አስተዳደር፣ የቤት አሰራሩ (“ጎዮ” ትልቅ ቤት፣ “ኸራር” መካከለኛና “ዘገር” አነስተኛ ቤቶች)፣  “ጃፈር” የሚባል የመንደር ስርዓት፣ እንሰትና ተረፈ ምርቱ … በዝርዝር ቀርበው ይነበባሉ፡፡

ምዕራፍ ስድስት – ዝክረ ጎጃም –  የጎጃምን መሬት በጀግኖቿ (በላይ ዘለቀ፣ ተድላ ጓሉ፣ ራስ አዳል፣ …)፣ በባለቅኔና ዜመኞቿ (ሙሉጌታ ሉሌ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አበበ መለሰ፣ ዮፍታሄ ንጉሴ)፣ በስነፅሁፍ ሰዎቿ (ሃዲስ አለማየሁ፣ አቤ ጉበኛ፣  አፈወርቅ ገብረየሱስ …)፣ በሊቃውንቶቿ (አራት አይናው ጎሹ፣ ቆምጨ አምባው፣…)፣ በከተሞቿ (ፍኖተ ሰላም፣ ባህርዳር፣ ጎዛምን፣ ሞጣ፣ ዱር ቤቴ፣ ዳንግላ፣ …) አባይን በጭልፋ እንዲሉ ለአብነት እያነሳሳ ያስጎበኘናል፡፡ በተጨማሪም ጎጃም የሃይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የሰዋሰው (የቋንቋ)፣ የስነቃሎች፣ የጥንታዊ ባህላዊ ጥበባትና ዕውቀት መፍለቂያ፣ የግጥም ወቅኔያት (ከልጅ የስም አወጣጥ ጀምሮ – እነ ፍቅር ይልቃል፣ እያደር አዲስ፣ ምናላቸው ስማቸው…) ዋቢ በመጠቃቀስ እጅግ ሰፊ ትረካዎችን አካፍሎን፤ ከጀግናዎቹ ሰራተኞቿ መሃል ቆምጨ አምባውን ከአስቂኝና አስተማሪ ትርክቱ ጋር ብሎም አባ ኮስትር በላይ ዘለቀን የሚዘክረው የኢትኖግራፊ ወግ ጋብ አድርጎ ሌላ ቀጠሮ ይዞ ወደ ኤርትራ ይዘልቃል፡፡   

ምዕራፍ ሰባት – የኤርትራ ሕልም  

የኢትዮጵያና የኤርትራ መቀራረብ ሕልሙ እንደነበር በ2004 የከተበበት መጣጥፉን እያስበበን እስከ ሐምሌ 2010 የዘለቀው የአፈንዲ ድርሳን ሕልሙ ዕውን የሆነበትን ቀን ከታደምን ይኸው ሶስት ወራት ተቆጠሩ፤ እናም ከዚያ በኋላ የሚያስነብበን የስለቱን ውጤት የነበረውን ቀድሞ የከተበው መጣጥፍ እንደሆነና መፅሃፉም የዳቦ ስሙን ያገኘበትን ምክኒያት ገላጭ ነው፤ የመፅሃፉ የሽፋን ስዕል ግን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያልጠፋ (በግድግዳው ሰቅሎት) የነበረና ያለ የቤኒ ዐመር ወጣት ምሰል ሲሆን ይህም ለተደራሲያኑ ሕልም መሳካት ማሳያ የሚሆን ሰነድ ነው፡፡ ከትውስታችን መገለጫዎች መካከል የወጣቱ ምስል፣ የእያንዳንዳችን የልጅነት የስዕል መለማመጃ ኤርትራ ፅፎ የሰው ገፅ መሳል፣ ሙዚቃዎች፣ እንቆቅልሽ ሃገር ስጠኝ አስመራን ሰጥቼሃለሁ የሚለው ምላሻችን፣ አስመራን አወዳሽ የሕፃንናት መዝሙሮቻችን … አንድ ባንድ በትውስታ መነፅር ተሰድረው ቀርበዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ስለኤርትራ ጀግና መፍለቂያነት (አብርሃም ደቦጭ፣ ሞገስ አስገዶም፣ ዘርዓይ ደረስ፣…)፣ ጥበበኞች መፈልፈያነት፣ የአስመራ ስያሜ የትመጣ፣ የጣልያኑና የእንግሊዛውያኑ አገዛዝ ልዩነት በሃገሪቱ ያሰፈናቸው ደግና መጥፎ ገፅታዎች፣ የጣሊያኑ ቅሪቶቹ የአስመራ ድምቀት ሕንፃዎቿና መንገዶቿ (የዩኔስኮ የአለም ቅርስ ምዝጉብ ከተማነት አስተዋፅኦቸው)፣ እንግሊዛውያኑ ያደረሱት ውድመትና ተንኮል፣ የእግር ኳስ ፈርጦቿ (ኢታሎ ቫስሎ፣ ሉቺያኖ ቫስሎ፣ አማኑኤል እያሱ፣ ነጋሽ ተክሊት …) ወዘተ በማውሳት በትረካ ይዞን ይነጉዳል፡፡

በመቀጠልም ኤርትራን ለአራት ከፍሎ በምዕራብ ኤርትራ – ጋሽና ሰቲት ይባል የነበረውን የሃገሪቱ ክፍል በርካታ ነገሮች ማለትም ህዝቦቹን (ሕዳራብ፣ ናራ፣ ኩናማ፣ ቢኒ አመር፣ ብሄረ ትግረ)፣ እስልምናና ትግረን ወዘተ ጠቃቅሶ ይተርክልናል፡፡ በሰሜን ኤርትራ ደግሞ ታወቂው የኤርትራ ገዳም ደብረ ሲና መገኛ የሆነው ዞባ አሰንባን፣ የቢለንና ሌሎች ህዝቦችን፣ ከረንና ዙሪያዋን፣ የኤርትራውያኑ የፅናት ምልክት የሚሰኘውና የገንዘባቸው መጠሪያ የሆነውን የናቅፋ ከተማ ወዘተ ያስጎበኘናል፡፡ በምስራቅ ኤርትራ – የቀይ ባህር ምድር ውስጥ ዕድሜ ጠገቧን ምፅዋ ታሪኳንና ዙሪያ ገባዋን ያስቀኘናል፤ ደሴቶቿንም እንደ ዳህላክ፣ ዞላና አዶሊስ፣ ትልቁ ተራራ እምባሶይራን አሁን ባሉበትና ጥንተ ፋይዳቸውን እያነፃፀረ ይገልፃቸዋል፡፡ ወደ ማዕከላዊ ኤርትራ በመጓዝ የታላቁ ኦርቶዶክስ ገዳም ደብረ ቢዘን መገኛና የታላቁ “ብሔረ ትግርኛ” የተሰኘው ሕዝብ መቀመጫነቱንና ታሪኩን እያጠየቀ ያስረዳናል፡፡ በመጨረሻም ከማዕከላዊው ዞን ለኤርትራ ነፃነት አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎችን ዘርዝሮ ውዳሴ እንካችሁ የሚላቸው በርካቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ የአሁኑ የኤርትራ ፕረዜደንት ኢሳያስ አፈወርቂም ተጠቃሽ አንደነበርና ከውጥኑ ጀምሮ እስከመጨረሻው የትግልና የሕይወት ጎዳናቸውን ተከትሎ ያስተዋውቀናል፡፡

በማሰረጊያም የአንድ ኤርትራዊ ከሁለት አረቦች ባገኘው የስጦታ ገንዘብ በኤርትራና በሐረር ከተማ የአይነስውራንና አረጋውያን መርጃ ማዕከል በማቋቋም በፍቅርና በአንድነት ዕገዛ ያደርግ የነበረ አብርሃ ባሃታ ስለተሰኘ ግለሰብ ሰብዓዊ ታሪክ ጀባ ብሎ ፍቅር ይስጠን የሚል መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

አጭር መልዕክትና አስተያየት

ዘይገርም!  ደራሲው ሁሉንም ስፍራዎች በተለይ የኤርትራ ቦታዎችን በጥሩ ሁኔታ ይተነትናቸዋል፤  እውነትም የመንፈስ ፈረሱ ሽምጥ እየጋለበ በመንፈስ እዚያው ደርሶ ነው የሚያስነብበን እንጂ በመሃል ደጋግሞ እንደሚገልፀው በተለይ ኤርትራን አንድ ቀን ሄጀ እጎበኛት ይሆናል በሚል ዕቅድ ላይ ያለ ሩቅ ነዋሪ አይመስልም፤ ናቅፋን ሲገልፅማ “የድሮዋ ናቅፋ በአፅሟ ነው የቀረችው … ከ1983 ወዲህ ያለችው ናቅፋ በአዲስ መልክ ነው የተሰራችው … የጥንቷ አይደለችም” ሲል ከበዓሉ ግርማ እግረኛዋ ብሎ የቀይ ኮከብ ዘመቻን አብሮ የዘመተ ነው የሚመስለው፤ … ምኞትህ እውን ይሁን አልኩ! አኔም ተመኘሁ እንዲህ በምናብ ልኮ እንዳስጎበኘኝ ግዘፍ ነስቼ ባየኋቸው አልኩ፤ አቦ አንተም የልብህ ይሙላ! እኔም መሻቴ ይሁን!

የግል አስተያየት ይህን መፅሃፍ ቢያነቡት አንዳቺ ፋይዳ ያገኛሉ፤ ስል ሊያነቡት የሚገባው እነማን አንደሆኑና ከድርሳኑ ለአብነት ያህል (ጥቆማዎችን) አስተምህሮቶችን  በመጥቀስ እጋብዛለሁ፡፡

1ኛ. የቋንቋና ስነፅሁፍ፣ የስነ-ልሳን፣ የፎክሎር፣ የአንትቶፖሎጂ ተማሪዎችና ባለሙያዎች – በርካታ ቋንቋዎች (ኦሮምኛ፣ ጉራጊኛ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ትግረ (ኤርትራውያ በብዛት የሚናገሩት)፣ ግዕዝ፣ ሶማሊያኛ፣ አረብኛ፣ ዳሃሊክ፣ ሳሆትዋሊ)፤ ስነቃሎች (ለምሳሌ የትግረ አዳል፣ የጎጃም ስም አወጣጥ)፣ ስነፅሁፎች፣ የሙዚቃ፣ የመዝሙር ግጥሞች፣ የኤርትራው ኪና ፈርዳ እና የኦሮሞው እሬቻ ባህል ምስስሎሽ፣ የነፃነት ትግል ምስረታ ሂደት፣ ማህበረሰባዊ ግጭት መፍቻ መንገዶች ወዘተ በመፅሃፉ ውስጥ ጥቆማ የተደረገባቸው ጥናት ትኩረቶች ናቸው፡፡

2ኛ. የስነጥበባት (ሙዚቃና ስነግጥም፣ ሥዕል፣ ስነሕንፃ ወዘተ) ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች – የሃረርጌ፣ የጅማ ኦሮምኛ፣ የጉራጌ ዜማዎች፣ የጎንደር አዝማሪዎች ቅኔያትና ግጥሞች፣ የትግርኛ ሙዚቃ ሰልቶች፣ የኤርትራ፣ የአዲስአበባ፣ የድሬድዋ፣ የጎንደር … የማህበረሰብ ዘፈኖች፣ የአስመራ ሕንፃዎች፣ ወደቦች፣ የአክሱም ሰልጣኔ ወዘተ፡፡  

3ኛ. የስርዓተ መንግስት፣ ሥርዓተ ፆታ፣ የስነ ትምህርት፣ ስነ-መለኮት ባለሙያዎች – የጊቤ መንግስታት ስርዓት፣ የኩናማው ዲሰንት ስርዓት (እናታዊነት)፣ የመድረሰተል ኮሌጅ ተሞክሮ፣ የክርስትና እስልምና ዋቄፈናን .. ወዘተ ጉልሕ ፋይዳ ያላቸው የጥናት ጥቆማዎች ተካትተውበታል፡፡    

መልካም ንባብ

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ – ጎንደር  

Solomon Dawud Arragie,
MA in English Literature & BA in
Sociology
Lecturer at CSSH, Department ELL
Program Coordinator of Save the children
Project at
CMHS Community Based Rehabilitation
Program
UoG – Gondar City, Ethiopia   

Email : solomon123@yahoo.com         

Filed in: Amharic