>

በሰው ሕይወትና ደህንነት ላይ ምን ዓይነት  ፖለቲካዊ ቁማር ነው የተጀመረው !?! (አሰፋ ሀይሉ)

በሰው ሕይወትና ደህንነት ላይ ምን ዓይነት  ፖለቲካዊ ቁማር ነው የተጀመረው !?!
አሰፋ ሀይሉ
 
* የአንድ ህግ ያለበት – እና በሌላ ሀገር ጦር ያልተወረረ መንግሥት – ዋናው ተግባሩ – እንደ ዩኤን – ይሄንን ያህል ሰው ተፈናቀለ እያለ ማውራት ነው?? ወይስ ሄዶ እንዳይፈናቀል ማስቆም??? የመንግሥት ዋነኛ ሚናና አስፈላጊነትስ ምንድነው?? 
ፈጽሞ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር ነው ይሄ፡- «ከዚህ አካባቢ ይሄን ያህል ሰው ተፈናቀለ!» የሚል መግለጫና ዜና እኮ ነው…???!!! በዓለም ላይ… የመንግሥት አስተዳደር፣ ጦር ሠራዊት፣ የፀጥታ ኃይል፣ ወዘተ ባለበት በየትኛውም ሉዓላዊ ሀገር፡-
۝ የእርስ በእርስ ጦርነት (Internal Armed Conflict) (እንደ ሶርያ፣ የመን ወይም እንደ ኮንጎዎቹ የኖርድ-ኪቩ ጦርነት) በሌለበት፣
۝ የተፈጥሮ መቅሠፍት (Natural Disaster) (እንደ ህንዶቹ የኬራላ ጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ወይ እሣተ ገሞራ፣ ወይ ሱናሚ፣ ወዘተ) ባልተከሰተበት ፣
۝ የታጠቀ የውጭ ወራሪ ኃይል (External Aggression) (እንደ ሊቢያና ኢራቅ) ባልመጣበት፣
۝ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ሆነ ብሎ ዜጎችን በማፈናቀል ተግባር (Forced Displacement) (እንደ ማያንማር ሮሂንጊያ ሙስሊሞች) ባልተሠማራበት፣
۝ ከፀጥታ አካላት ሙከራና ቁጥጥር ውጭ የሆነ ታላቅ ሕዝባዊ አመፅ (ማዕበል) (Explosive Massive Riot) (ሳውዝ አፍሪካና ሣዑዲ የውጭ ዜጎችን በዜጎቻቸው የቁጣ አመፅ እንዳፈናቀሉት) ባልተቀሰቀሰበት፣
በምንም መልኩ . . . አይደለም በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን «ተፈናቀሉ!» እየተባለ በሀገርቤት ዜና ልክ ድንገተኛ የመኪና አደጋ እንደደረሰ ሊነገርና ሊሰማ ይቅርና፤ አንድም ዜጋ እንኳ በሕገ-ወጦች «ተፈናቀለ!» ብሎ ማውራት፣ መናገር፣ እና እውነትም ዜናውን አምኖ – ልክ የጎርፉ መጥለቅለቁ እስኪያልፍ እንደሚጠበቀው – አፈናቃዮቹ ስሜታቸው እስኪያልፍላቸው ተፈናቃዮቹን እያጓጓዙና እያስጠለሉ – ያን ዜና «ይህን ያህል ሰው ከዚህ ሥፍራ ዛሬ ተፈናቀለ፣ ከዚህ ሥፍራ ትናንት ይሄን ያህል ሰው ተፈናቀለ!…» እያሉ ማወጁ፣ ዜና ማሠራጨቱ፤ እና የጎርፍ መጥለቅለቁ እስኪያልፍ እዝጌርን እየተለማመኑ ቁጭ ማለቱ ….. በእውነት… በእውነት ነው የምለው…. በየትኛውም ዓለም መንግሥት ቢሆን «ፍፁም እንቆቅልሽ» ፣ ፍፁም ግራ አጋቢ፣ እና እጅግ አሣፋሪም ነው!!
የማንኛውም በዓለም ላይ ያለ አንድ ሉዓላዊ መንግሥት – የትኛውም ህግና መንግሥት ያለበት… ሉዐላዊ ሀገር ዋነኛ መገለጫ ምንድነው?? መንግሥት ባለበት ሀገር – ዋነኛው የመንግሥት ተግባር – በግዛቱ ወሰን ውስጥ ያሉትን ‹‹ዜጎች፣ ዜጎችን ብቻ ሣይሆን ማናቸውንም በግዛቱ የሚገኙ ሰዎች፣ በግዛቱ የሚገኙትን ንብረቶች፣ እና በግዛቱ የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን ‹መ ቆ ጣ ጠ ር› ነው፡፡ (A state’s sovereignty implies that it has assumed control over the persons, properties and conditions residing within its territory!)፡፡
ይሄ ነገር በዓለም ላይ የታወቀ ነው፡፡ ከማንም ጤነኛ አስተሳሰብ ካለው ሰውም የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በፊትም በብዙዎች ተደጋግሞ የተነገረ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ በውል ባላስታውስም እኔም አሁን እደግመዋለሁ፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ይህን ያህል ዜጎች ተፈናቀሉ ብሎ ሰብዓዊ ሪፖርት ማውጣት አይደለም፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ይህን ያህል ሰዎች ሞቱ ብሎ ሰብዓዊ ሪፖርት ማቅረብ አይደለም፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር በሌሎች ዜጎች የተፈናቀሉ የሀገሪቱን ዜጎች ድንኳንና ካምፕ እየቀለሱ ማስጠለል አይደለም፡፡
የመንግሥት ዋነኛ ተግባር እንዲህ አይነት ህገወጥ ድርጊት – በአንድም ሰው ላይ ቢሆን – ዜጋም ይሁን የውጭ ዜጋ – በአንድም ሰው ላይ እንዳይፈጸም ነቅቶ መጠበቅ ነው፡፡ በአንድም ሰው ላይ ደግሞ ሲፈጸም – በግዛቱ ባለ ሰው ህይወትና ደህንነት ዋና ኃላፊነቱ የዜጋው ሳይሆን የመንግሥት ነውና – ወዲያው በሥፍራው ደርሶ ህገወጦቹን በቁጥጥር ሥር አውሎ – በስም ለይቶ – ለፍርድ የማቅረብ – ሀገራዊም፣ ዓለማቀፋዊም ግዴታ አለበት መንግሥት፡፡
የውጭ ጠላት ባልመጣበት – የእርስ በእርስ ጦርነት ባልተቀሰቀሰበት ሠላማዊ ሀገር ውስጥ – ጥቂት ህገወጦች – በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቀሉ እያለ – እጁን አጣጥፎ እየተቁለጨለጨ የሚያወራ የየትኛውም ዓለም መንግሥት – በዓለም ፊት ይዋረዳል፡፡ በዓለም ፊት የሁሉም መንግሥታት መሣቂያ ነው የሚሆነው??!!!
የዓለም ሀገራትና ዓለማቀፍ ተቋማት እንኳ – ሌላ ቀርቶ – መንግሥት ዓልባ ሆነዋል በሚባሉ ሀገራት (በወቅቱ) – የሆነን አካባቢ ወይም ግዛት አስመልክቶ – ግንኙነት ለመፍጠር ሲፈልጉ – መጀመሪያ የሚጠይቁት የታወቀና የተለመደ ጥያቄ፡- «ለመሆኑ ያንን አካባቢ የሚቆጣጠረው ኃይል ማን ነው? ወይም የትኛው ኃይል ነው በግዛቱ ላይ ሥልጣን ያለው?» የሚል ነው፡፡
እና እንግዲህ… መንግሥት ከነሙሉ ሠራዊቱና ከነሙሉ ኃይሉ … ከነሙሉ የአስተዳደር መዋቅሩ በሚሠራበት ሀገር ላይ… ህግና ፍርድ ቤት ባለበት ሀገር ላይ…. መንግሥት ሥራው አስፋልት ለአስፋልት የሚንገላወዱ ወጣቶችን ከመዲናው እየያዘ ማፈስ ነው?? ወይስ… የሰውን ነፍስ የሚቀጥፉትን…. አንድን ሰው ቢሆንም፣ አንድን ቤተሰብ ቢሆንም ከህግ በላይ ሆነው ከቤትህ ለቀህ ውጣ ብለው የሚጨፈጭፉ፣ የሚያፈናቅሉ ሰዎችን በሥፍራው ተገኝቶ ማስቆም ነው????
የአንድ ህግ ያለበት – እና በሌላ ሀገር ጦር ያልተወረረ መንግሥት – ዋናው ተግባሩ – እንደ ዩኤን – ይሄንን ያህል ሰው ተፈናቀለ እያለ ማውራት ነው?? ወይስ ሄዶ እንዳይፈናቀል ማስቆም??? የመንግሥት ዋነኛ ሚናና አስፈላጊነትስ ምንድነው??
ያለበለዚያማ – መንግሥት የሰውን ደህንነት የማይጠብቅና ከዳር ሆኖ እንዲህ ሆነ፣ እንዲህ ተደረገ እያለ የሚዘግብ የሩቅ ተመልካች ከሆነ – ታዲያ ለምን እኛን ዜጎቹን አስታጥቆ – ራሳችሁን በራሳችሁ ጠብቁ፣ ራሳችሁን ተከላከሉ፣ ሥራችሁ ያውጣችሁ ብሎ አንድያውን ለምን አይነግረንም???!!!
ምን ዓይነት መንግሥታዊ ቀልድ፣ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ቁማር ነው የተጀመረው – በሰው ሕይወትና ደህንነት ላይ?????!!!! ስንቴስ ነው በየሀገሩ በሚሆነው ላንቃችን እስኪሰነጠቅ የምንጮኸው… እና የምንመክረው… እና የቁራ ጩኸታችንን ለማይሰማ ጆሮ የምንጮኸው – እና ምንስ ነው ማድረግ ያለብን ከዚህ በላይ….????  እና አሁንም እንጮኻለን ለሕዝቡ የቆመ ሰሚ መንግሥት ካለ፣ አሁንም እጮኻለሁ ለዜጎቹ ደህንነት የሚቆረቆር ሰሚ አካል ካለ፡-
۝ መንግሥት ሆይ፡- ስንት ሰው ከየት ቦታ ሲፈናቀሉ እንደታዘብክ አትንገረን!
۝ ሊያፈናቅሉ ሲሉ አስቆምኳቸው በለን!
۝ ገና አስር ሰው ያፈናቀሉትን ወደሌላ ቤት ሳይሸጋገሩ ይዤ ለህግ አቀረብኳቸው በለን!
۝ የሆነን የግዛቴን ክፍል ከተቆጣጠሩት ኃይሎች አስለቅቄ ነፃ አወጣሁ ብለህ ንገረን!
۝ ለዚህ ዓይነቶቹ መቅሰፍታዊ ህገወጥ ሰዎች/ቡድኖች ይሄን መከላከያ መፍትሄ ለደህንነታችሁ አዘጋጅቼላችኋለሁ በለን!
۝ አንተም እንደ ቀይ መስቀልና እንደ አምነስቲ ከዳር ቆመህ የተፈናቀለ ሰው መቁጠርህ አሳፈረን እኮ መንግሥት ሆይ!
۝ እኛን ዜጎችህን ለወራዳ ህገወጦች አሳልፈህ በሠጠኸን ቁጥር አንተ ተዋርደህ እኛን ዜጎችህንም በዓለም ፊት አዋረድከን እኮ መንግሥታችን ሆይ!
۝ ከመኖራችን፣ ከደህንነታችን በላይ ቅድሚያ ምን አለ?? እና እባክህ መንግሥታችን ሆይ፡- ዜጎችህን አክብር! ለዜጎችህ ደህንነት ተጨነቅ!
۝ የአንድ ቤተሰብ ቤት ቀልድ አይደለም! የአንድ ሰው ኑሮና ህይወት ቀልድ አይደለም! ስለዚሕ ቀልድህን አቁምልንና ትክክለኛ የመንግሥትን ከለላ ለእኛ ላልታጠቅነው እና ከአምላክ በቀር ራሳችንን የምንከላከልበት ሌላ አዳኝ ለሌለን ዜጎችህ ቁምነገር ተግባር ፈጽም!!»
I ask my government and the current Ethiopian authorities, to stop watching this forced internal displacement of thousands of people under their nose, right in front of the government’s eyes; to act responsibly and appropriately to protect the lives, livelihoods, peace and general well-being of us all, we the Ethiopian civilian citizens in the country at large!!!!!
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ የአምላክ ጥበቃና ቸርነት አይለየን፡፡ ለመንግሥታችን ሥደታችንንና መፈናቀላችንን የሚያስብ አዛኝ ልቦና፣ ለደህንነታችን ዘብ የሚያስቆም ቅን ልቦና ይስጥልን፡፡ መንግሥታችንን የሚያሸብረውን፣ ወገናችንን የሚያፈናቅለውን፣ ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ የሚገዳደረውን፣ ክፉ ‹‹ኃይል›› – አንድዬ (- ከይቅርታ ጋር! -) እግሩን ቄጠማ፣ ዕድሉን ጠማማ ያድርግልን!! አበቃሁ፡፡
According to the Guiding Principles of the United Nations, the definition of Internal Displacement is:
“persons or groups of persons who have been forced or obliged to flee or to leave their homes or places of habitual residence, in particular as a result of or in order to avoid the effects of ARMED CONFLICT, SITUATIONS OF GENERALIZED VIOLENCE, VIOLATIONS OF HUMAN RIGHTS or NATURAL OR HUMAN-MADE DISASTERS, and who have not crossed an internationally recognized State border.” (- caps, mine)
Filed in: Amharic