>
5:13 pm - Tuesday April 18, 3443

አገራችንን የሰጡን...! (ውብሸት ታዬ)

አገራችንን የሰጡን…!
ውብሸት ታዬ
* ግንኮ ሳይቸግር፤ ሳያስፈልግ አንዳችን ሌላችንን አስለቅሰናል። ገድለናል፤ ቢያንስ ልብ ሰብረናል። የእኛ ስላልሆኑ ብቻ የሌላውን አባት፣ የሌላውን እናት፣ እህት፣ ልጅ፣ ወዘተ ገድለናል፣ አሳደናል፣ አዋርደናል፤  አሸማቀናል። ብድሩ ዞሮ እኛምጋ መጥቷል። 
 
  እንደዚህ አስቤበት አላውቅም ነበር። አሁን ግን በእንባዬ አሻግሬ ከመራር እውነት ጋር እየታገልኩ ነው። እጠይቃለሁ፤ እጨነቃለሁ። ለካ ከህያዋን ብቻ ሳይሆን ከሙታን መንደርም ትልቅ እውቀት፤ ትልቅ ምስጢር አለ!
   ቆሜ ያልቀበርኳቸው አባቴ ረፍተ አካል ተቆፍሮ ወጣ። ዘመኔን ወቅሰው ሊመለሱ ያወጧቸው መስሎኝ ሁሉ ፈራሁ፤ እኒህ ሰው በአባታቸው (ሰላሌ) የሰጎ ካራው የበዳሳ(Badhaasaa) ጉዳ፤ በእናታቸው የመርሃቤቴዋ የሸዋርካብሽ ግምቱ ልጅ ናቸው። አጽማቸው የወጣው የዘመናት አጋራቸው እናቴ አብራቸው ልታርፍ ስለመጣች ነበር። በጣም እወዳት ስለነበር ለዘላለም የምትኖርልኝ ይመስለኝ ነበር።
   እናቴስ ማን ናት? አባቷ የያያ ጉለሌው ባላምባራስ ገለታ በዳኔ(Badhaanee) እናቷ መንዜዋ ብርሃኔ ሃብቴ ነበሩ። አባቴ በእስሬ ጦስ ሊያዩኝ እየናፈቁ አለፉ። እማ (Haarmee koo!) ለአጭር ጊዜም ቢሆን አገኘችኝ። በሕይወቴ እንደዛሬ የከፋኝ፤ ያዘንኩበት ቀን የለም፤ ታዲያ ለምንድነው እያነባሁ ይህን ሁሉ የምነግራችሁ?
   ከሰጎ ካራ እስከ መርሃቤቴ፣ ከያያ ጉለሌ እስከመንዝ የወሰደን መስመር ምን ነበር? እያልኩ ሁሌ እጠይቅ ስለነበር ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ከቶ ነገር ቀመራችን ምንድነው? እንዴት ነን? እኒህ የብዙ ትውልዶችን መስመር በንጹህ ፍቅራቸውና በደማቸው አጣምረው በአንድ መቃብር ውስጥ ለዘላለሙ የተቃቀፉ አጋሮች ምን ያስተምሩናል? በእውኑ የእኔ አባትና እናት ብቻ ናቸው? ልብ ካልነው እኮ እንዴትም፤ እንደምንም ቢሆን ይህችን አገራችንን የሰጡን እነሱ ናቸው።
   ለዚህ ነው መጨነቅ፤ መጠበብ። እኛስ ለልጆቻችን ምን አይነት አገር ይሆን የምንሰጠው? ምን እየነገርናቸው ይሆን የምናሳድጋቸው? እኔ የደረሰብኝ አይነቱ ይህ የዛሬው እንባ ከእግዚአብሔር የመጣ ብንፈልግም የማናስቀረው የተፈጥሮ እውነት ነው።
  ግንኮ ሳይቸግር፤ ሳያስፈልግ አንዳችን ሌላችንን አስለቅሰናል። ገድለናል፤ ቢያንስ ልብ ሰብረናል። የእኛ ስላልሆኑ ብቻ የሌላውን አባት፣ የሌላውን እናት፣ እህት፣ ልጅ፣ ወዘተ አሳደናል። አዋርደናል፤ አሸማቀናል። ብድሩ ዞሮ እኛምጋ መጥቷል።
   እና እስከመቼ እንዲህ እየሆነ ይቀጥል? እስከመቼ ወላጆቻችን መቃብር ላይ ቆመን እንኳ የአገራችን መጻኢ እጣ ፈንታ ምን ይሆን እያልን እንቃት? እንዴት እኛው ያውተፈተፍነው ቋጠሮ ውሉ እኛኑ ቸግሮ አፋቺ እንፈልግ? ስለሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት በሰበክንበት በዚያው ዕለት ጀምበር ወደ ጸብና መለያየት ማን መራን?
   መቋጫዬ በፍቅራችን ፀሐይ አይግባበት የሚል ነው። ውዶቻችንን በውድ አገራችን ጦረን የምንቀብር፣ ትውልድ ሲያልፍ ጸንታ የምትኖረዋን አገራችንን እንጠብቃት የሚል ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic