>

ጃዋር መሃመድ - ዳግማዊ ስሁል ሚካኤል?!!! (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

ጃዋር መሃመድ-ዳግማዊ ስሁል ሚካኤል?!!!

ያሬድ ደምሴ መኮንን

በጦረኝታቸዉ የሚታወቁት ራስ ስኡል ሚካኤል በወሎና በቋራዎች መሃል የነበረዉን የስልጣን ፍትጊያ ለማስወገድ በንጉስ እዮአስ ግብዣ ከትግሬ ወደ ጎንደር መተዉ ስራቸዉን ጀመሩ፡፡ ሆኖም ግን ከጊዜ በኋላ ስሁል ሚካኤል እጅግ አደገኛ እየሆኑ ስለመጡ ነገሩ ያላማራቸዉ ንጉስ እዮአስ ስሁል ሚካኤልን ያሰናብቷቸዋል፡፡ይህ ስንብት ለትግራዩ ራስ አልተዋጠላቸዉም፡፡በዚህም የተነሳ ማንም ባልጠበቀዉ ሁኔታ አጼ እዮአስን በሻሽ አሳንቀዉ አስገድሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ያሻቸዉን እያነገሱ ያሻቸዉን ደግሞ እያወረዱ ለ40 ዓመታት ያህል ኃያል ሆነዉ ለመዝለቅ ቻሉ፡፡

ራስ ሚካኤል ለደንቡ ያህል የይስሙላ ንጉሰ ነገስት መሾማቸዉ ባይቀርም ዋናዉ የመንግስት ስልጣን ግን በሳቸዉ እጅ ነበር፡፡ተክለጻድቅ መኩሪያ እንደሚነግሩን በስሁል ሚካኤል የተሾመዉ ንጉሰ ነገስት የሚደረገዉን ነገር ወሬዉን እየሰማ ከመታዘብ በቀር ለምን ተደረገ ብሎ ለመከራከርና ለመቆጣት አቅም አልነበረዉም፡፡

ራስ ሚካኤል የእብሪትና የጭካኔ ስራ በመስራት ተወዳዳሪ አልነበራቸዉም፡፡ራስ ሚካኤል ከሸፈተዉ የቀድሞ ንጉስ ፋሲል ጋር ጦርነት ገጥሞ ከሁለቱም ወገን አስር ሺ ሰዉ ካለቀ በኋላ ፋሲል ሸሽቶ አመለጠ፡፡ከፋሲል ጦር የተማረኩትን ወታደሮች በስሁል ሚካኤል ትእዛዝ እንዲገደሉ ተደረገ፡፡እንዲያዉም አንዱ ዋጨቃ የተባለ የፋሲል ተከታይ ይምሩኛል ብሎ እጅ በመስጠቱ በጭፍሮቹ ተገሎ ቆዳዉ እንደ ከብት ተገፎ እንደ ስልቻ ተሰፍቶ ገለባ ተሞልቶ ለራስ ሚካኤል አሳይዋቸዉ ይባላል ሲሉ ተክለጻድቅ መኩሪያ ይነግሩናል፡፡

በአጭር አማርኛ ለኔ ጃዋር መሃመድ የዘመነ መሳፍንቱ ዳግማዊ ስሁል ሚካኤል ዳግም ክስተት ነዉ፡፡ የኦሮሞ አክቲቪስቱ ጃዋር መሃመድ እንደ ሚካኤል ስሁል ሁሉ የሁለት ወገን ፍጥጫን ለማርገብ ሲባል ወደደአገር ቤት የገባዉ በአብይ ግብዣ ነበር፡፡የአብይ መንግስት ከህወሃት ኢህአዴግ ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ዉስጥ በነበረበት ጊዜ አሁን እየተደረገ ያለዉን ሃገራዊ ለዉጥ ያፋጥናሉ በሚል እሳቤ ዉጭ ያሉ ተቃዋሚዎች በዶ/ር አብይ ጥሪ ወደሃገር ዉስጥ እንዲገቡ ሲደረግ ጃዋርም አብሮ መግባቱ ይታወቃል፡፡

የጃዋር መምጣት በእርሱ የሚመራዉን ቄሮ ከአብይ ጎን አሰልፎ ታላቋን ኢትዮጵያ የመገንባት ሂደቱን ያፋጥናል ተብሎ ቢታሰብም፣ ጃዋር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከዶ/ር አብይ የመደመር እሳቤ በተቃራኒዉ እየተጓዘ ለለዉጡ እንቅፋት እየሆነ መጣ፡፡የቀን ተሌት ህልሙ ታላቋ ኢትዮጵያን መገንባት ሳይሆን ማፈራረስ መሆኑን ከንግግሮቹና ከድርጊቶቹ ታወቀ፡፡እየዋለ እያደረ የጃዋር አደገኛነት በቡራዩ ላይ ታየና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለማስደንገጥና ለማስቆጣት በቃ፡፡

“ብዙ ነገር ተምሬያለሁ ብዙ ነገር ቀስሜያለሁ” ብሎ የሚያስበዉ ጃዋር በህጋዊ መንገድ ወደ ስልጣን መምጣት አይፈልግም፡፡ለርሱ የፓርቲ አባል መሆን፣ ሚኒስቴር መሆን መታሰር ነዉ፡፡ምክንያታቸዉ ይለያይ እንጂ የትግራዩ ስሁል ሚካኤልም ያደረገዉ ይሄንን ነዉ፡፡

“ያንን ልምድ ለአንድ ፓርቲ ሰጥቼ ለአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስረክቤ መቀመጥ አልፈልግም “ ይልሃል ጃዋር መሃመድ፡፡

ግን ደግሞ ዘወር ይልና ከሚበቃኝ በላይ ስልጣን አለኝ ሲል ያቅራራብሃል፡፡ስለዚህ ይህ ሰዉ እንደ ዘመነ መሳፍንቱ ሚካኤል ስሁል፣ ከጀርባ ሆኖ የፈለገዉን እየሾመ ያስጠላዉን ደግሞ እየሻረ ከንጉሱ በላይ ንጉስ ሆኖ እያዘዘ እየናዘዘ ለመኖር ማቀዱ ማይደል?

“እኔ እንደ ነጻ ፈረስ የፈለኩትን እየተናገርኩ የፈለገኝን እየሰራሁ በፓርቲ ፕሪሲፕል በምናምን ምናምን ሳልታሰር ይህችን ሃገር  መርዳት ነዉ”

እና ከዚህ በላይ ስሁል ሚካኤልን መሆን ከየት ይመጣል? ምንም ሳይሆኑ ሁሉንም መሆን ማለት ይሄዉ ነዉ!! የሚገርመዉ አይደለም የፓርቲ አባልና ሚንስትር ሳይሆኑ ቀርቶ፣ የፓርቲ አባልና ሚንስትር ሆነዉም እንኳ የፈለጉትን መናገርና የፈልጉትን መስራት እንደማይቻል በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ባገኘዉ ተቀባይነት ለሰከረዉና ልቡ ላበጠበት ጃዋር ገና ያልተገለጸለት መሆኑ ነዉ፡፡ህግ ባለበት ሃገር የፈለጉት እየተናገሩ መኖርም ሆነ የፈለጉትን እያረጉ መኖር ባይቻልም ለኦሮሚያዉ ስሁል ሚካኤል ግን ይህ ሁሉ ተፈቅዶለታል፡፡

በዘመነ መሳፍንት ዘመን ነገስታቱ ወደ ዙፋን የሚመጡት የስዉሩን ንጉስ ስሁል ሚካኤል ይሁንታ ሲያገኙ ብቻ እንደነበረዉ ሁሉ፣ ጃዋርም እነ ዶ/ር አብይ የሚመሩት የኢህአዴግ መንግስት በስልጣን መቀጠል የቻለዉ የእርሱን ቡራኬ አግኝተዉ እንደሆነ ሲነግረን ደረቱን ነፍቶ ነዉ፡፡ማንከልካይ አለዉና?

“ኢህአዴግን እኮ ሆነ ብለን ነዉ የተዉነዉ በቦታዉ!!” ይልሃል ጃዋር በድፍረት፡፡በዚህ ቢያበቃ ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ጃዋር ግን ይቀጥላል “እዚች ሃገር ላይ ሁለት መንግስት አለ፡፡ አብይ የሚመራዉ መንግስትና የቄሮ መንግስት!” ሲል በድፍረት ያዉጃል፡፡ጉድ በል አብይ!!!

እንደ ጃዋር አባባል ዶ/ር አብይ ከፊት ሆኖ ሃገሪቱን የሚመራ ይምሰለን እንጂ ይቺ ሃገር የምትመራዉ በዳግማዊዉ ስሁል ሚካኤል ጃዋር ነዉ ማለት ነዉ፡፡ ሃገሪቱን አስተዳድራለሁ የሚለዉ አካልም ለዚህ መረን የለቀቀ አባባል ግልጽና ቀጥተኛ ምላሽ ሲሰጥ እስካሁን ስላልሰማን ለጊዜዉም ቢሆን በዓለም ላይ በሁለት መንግስታት የሚተዳደር ህዝብ የሚኖርባት ብቸኛዋ ሃገር ኢትዮጵያ ሆናለች ለማለት ተገደናል፡፡

ሁሉን አወቁ (omniscient) የ”ፖለቲካል ሳይንቲስቱ” ጃዋር አሁን ያሉት መሪዎች እርሱ ባለዉ መንገድ ካልተጓዙ ይቺ ሃገር ከፍተኛ የመክሸፍ ዕድል አላት ብሎ ትንቢት ይናገራል፡፡ይቺ ሃገር እርሱ በቀየሰዉ የብሄርተኝነት መንገድ ካልሄደች ሁለተኛ ዕድልም የላትም ብሎ ያሟርታል፡፡ሁሉን ቻዩ (omnipotent) ጃዋር ቢያሻዉ ብቻዉን ኦሮሚያን ባንድ ሌሊት ገንጥሎ ሊያሳየን የሚችልበት አቅም እንዳለዉ ይታበያል፡፡ለእሱ ምን ተስኖት!!

“እኔ ኦሮሚያን መገንጠል ብፈልግ ማን ከለከለኝ? I could have done it before four months ago” ሲል ትዕቢት በተሞላበት እርግጠኛነት ይነግርሃል፡፡ለጃዋር አገር መገንጠል የዶሮ ብልት የመገንጠል ያህል እንኳ የሚከብድ ስራ አይደለም፡፡ የህወሃትን ሃሳብ የትግራይ ህዝብ ሃሳብ አድርጎ እንደሚቆጥረዉ ህወሃት ጃዋርም የርሱን ቅዠት የመላዉ የኦሮሞ ህዝብ ሃሳብ አድርጎ ሲቆጥረዉ፡፡ ጃዋር እብሪቱን ይቀጥላል……

“አሁንም ብንፈልግ  nobody can prevent us. ይሄንን መንግስት ዉስጥ ያሉ ሰዎችም ያዉቃሉ!!” ይልሃል ዳግማዊዉ ስሁል ሚካኤል፡፡ጃዋር የኦሮሚያ መገንጠል የኦሮሞን ህዝብ ወደ ማያባራ ጦርነት ዉስጥ እንደሚከተዉ በዚያች ካልኩሌተሩ ያሰላት አይመስልም፡፡የነ ጃዋር ካርታ እነማንን ሊያስቆጣ እንደሚችል ማወቅም የፈለገ አይመስልም፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ እየተባለ ያለዉ መንግስት አለን ብለን፣ሁሉን ነገር ዶ/ር አብይ ላይ ጥለን እየኖርን ባለበት ወቅት ነዉ፡፡ አሁን እየተፈጸመ ያለዉን ግድያና አፈሳ ስንመለከት ይህችን አገር እየመራት ያለዉ ከፊት ያለዉ አብይ ሳይሆን ጃዋር መሆኑን ልንጠረጥር ግድ ይለናል፡፡

እንደ ስሁል ሚካኤል ሃያል ሆኖ ከጀርባ ሆኖ ያሻዉን እያስፈጸመ ያለዉ ጃዋር የሰዎች በቆንጬራ ተጨፍጭፈዉና በድንጋይ ተወግረዉ ባሰቃቂ ሁኔታ መገደል አይዘገንነዉም፡፡ግለሰቦች በብሄራቸዉ ምክንያት ቆዳቸዉ ተገፎ ጫማ ቢሰራበት እንኳ የሚሰቀጥጠዉ ፍጡር አይደለም፡፡ ስለንጹሃን መሞት እየተወራ እርሱ ግን በሃሰት “እኔም ሰዎች ተገለዉብኛል” ሲል የእዉነት ጭፍጨፋን በሃሰት ግድያ ለማጣፋት ይሞክራል፡፡ የአብይ መንግስትም እዚች ሃገር በነጃዋር መሃመድ እተፈጸመ ያለዉን ሽብር ቤተ መንግስት ቁጭ ብሎ ከመታዘብ በቀር በሽብር አቀናባሪዎቹ ላይ ርምጃ ለመዉሰድ ሲሳነዉና የፖሊስ ሃይልም አህያዉን ፈርቶ ዳዉላዉን ሲደበድብ ለመታዘብ በቅተናል፡፡

ስለዚህ የስሁል ሚካኤልን ፈለግ እግር በግር እየተከተለ እንደልቡ የሚፈነጨዉንና ለመፈንጬት ያሰበዉን ጃዋር መሃመድ የአቢይ መንግስት ከወዲሁ ሃግ ሊለዉ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ይሄ ልቡ በእብሪት ያበጠበት ወፈፌ ይቺን ሃገር ወደለየለት ብጥብጥና እልቂት ይዟት የመንጎድ ዕድሉ ሰፊ ነዉ፡፡

ስለሆነም ዶ/ር አብይ በዚች ሃገር ላይ ሁለት መንግስት ያለመኖሩን ባስቸኳይ ድጋፉን ለቸረዉ በሚሊዮናት የሚቆጠር ህዝብ በአፋጣኝ ሊያሳይ ይገባል፡፡የአብይ መንግስት የዚችን ሃገር አንድነትና ሰላም ለማስከበር ማንንም ሳይፈራ በዚች አንድ ሃገር ላይ ሌላ መንግስት ነን በሚለዉ ቡድን ላይ የሃይል እርምጃ ለመዉሰድ ካልደፈረ ይቺ ሃገር ከዘመነ መሳፍንት ወደ ከፋዉ ሌላ ዘመነ መሳፍንት ተሸጋረች ማለት አይደለምን?!!

ቸር ያሰማን!!

Filed in: Amharic