>

በነ በቀለ የተነሳ ሙሉ ኦሮሞን ባለመውቀስ እሳቱ ላይ ውሃ እናፍስስበት!!! (አበበ ቶላ ፈይሳ)

በነ በቀለ የተነሳ ሙሉ ኦሮሞን ባለመውቀስ እሳቱ ላይ ውሃ እናፍስስበት!!!
አበበ ቶላ ፈይሳ
የኦሮሞ ፖለቲከኞችን በጅምላ ወደማጥላላት ፈጽሞ መሄድ ተገቢ አይደለም። ልብ አድርጉ እነ ዶክተር አብይ እና አቶ ለማ መገርሳም ኦሮሞዎች ናቸው!!!
 
በነ አቶ በቀለ ገርባ መግለጫ ላይ ሁለት ጎልተው የታዩኝ ጉዳዮች አደኛው ጠላት ፍለጋ መባዘን ሁለተኛው ደግሞ ሁሉን የኔ ይሁን ባይይ የስግብግብ ፖለቲካ ነው!
እንደኔ እምነት ስለ ኦሮሞ ወይም ስለ ቄሮ በጅምላው እየተነገሩ ያሉ ኔጌቲቭ አተያዮች እና የጥርጣሬ አስተያየቶች ባለማወቅ የሚመጡ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ውይይት በማድረግ እንዲሁም በስራ የሚቀየሩ እሳቤዎች ናቸው እንጂ በጠላትነት የሚያፈራርጁ አይደሉም።
አቶ በቀለ ገርባ ባነበበው የአምስቱ ኦሮሞ ድርጅቶች መግለጫ ላይ ኢሳት ቴሌቬዥንን እንደ ጠላት ማየቱ ነውር ነው። ኢሳት አያጠፋም አልልም… አጠፋ እና ተሳሳተ ማለት ግን ለኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው ማለት አይደለም። ይሄ አይነቱ መግለጫ እና ሁሉን እንደ ጠላት የሚያይ ፖለቲካ መነሻው ደጋፊዎችን በጠላት እንደተከበቡ በመንገር ስጋት ውስጥ ማስገባት ከዛ ብቸኛ መዳኛ እኛ ነን በሚል ፖለቲካዊ ጥቅማ ጥቅም ፍለጋ የሚደረግ ሴራ ነው።
ሌላው ድርጅቶቹ የሚታገሉት የኦሮሞን ህዝብ የሃገር ባለቤት ለማድረግ እንደሆነ እና አዲሳባም ለኦሮሞ ባለቤትነት ከሚጠይቋት ከተማ እንደሆነች ነግረውናል። ኦሮሞ የሃገሩ ባለቤት ነው ማለት እና አዲሳባ የኦሮሞ ናት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እነርሱ ይወቁት። እኔ የሚታየኝ ግን በአዕምሯቸው ውስጥ ያለው ስግብግብነት ነው።
እንደኔ እምነት ኦሮሞው ማህበረሰብ ሁሉን ነገር የኔ ነው ባለቤቱ እኔ ነኝ… የሚል ስግብግብነት የለበትም። እኛ የምንረዳው እና የምናምነው ኦሮሞው ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ላይ እኩል ባለቤት እንደሆነ ነው። እኛ የምንመኘው ኦሮሞው እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉንም የሃገሪቱ ክፍሎችን በእኩል ባለቤትነት በእኩል መብት በእኩል ተጠቃሚነት እንዲኖሩበት እና እንዲያጎለብቱት ነው። ኦሮሚያ የኦሮሞው ብቻ ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናት። አዲሳባም እንደዛው።
እነ ዶክተ አብይ እና አቶ ለማ መገርሳ በዘመናዊ ፖለቲካ እና በፍቅር አስተሳሰብ ከኦሮሚያ ክልል አልፈው ምስራቅ አፍሪካ ላይ ሲነግሱ የነ በቀለ ገርባ አዲሳባን ኬኛ ብሎ በውስን ቦታ ላይ ሙጥኝ ማለት… ለኦሮሞ ህዝብ የሚመጥን ፖለቲካ አይመስለኝም!
በፍቅር እና በአንድነት ለሁላችንም የምትበቃ ሰፊ ሃገር መስራት ስንችል ህዝቡን በተወሰነ ክልል አጥሮ የዚች ሃገር ባለቤት አንተ ነህ… ጠላቶችህ ብዙ ናቸው… እያሉ ከተቀረው ህዝብ ጋር ማቃቃር ለህዝቡም አይጠቅመውም፤ በፈጣሪም ዘንድ ያስጠይቃል!
እነ በቀለ ይሄ አይነቱን መግለጫ ያወጡት በነርሱ የተነሳ ኦሮሞው ህብረተሰብ እና ሌላው ኢትዮጵያዊ በማናቆር ውስጥ የምትገኘዋን ድጋፍ ለመሰብሰብ ሊሆን ይችላል ብዬ እጠረጥራለሁ ብልህ የሆነ ቢኖር በዚህ የተነሳ ከመናቆር ይውጣ። የኦሮሞ ፖለቲከኞችን በጅምላ ወደማጥላላት ፈጽሞ መሄድ ተገቢ አይደለም። ልብ አድርጉ እነ ዶክተር አብይ እና አቶ ለማ መገርሳም ኦሮሞዎች ናቸው። ሌሎችም በርካታ ኦሮሞዎች ለሁሉም የምትበቃ ሁላችንም ባለቤት የሆንባት ትልቅ ሃገር እንድትኖረን ይመኛሉ ይሰራሉም። በነ በቀለ የተነሳ ሙሉ ኦሮሞን ባለመውቀስ እሳቱ መግለጫቸው ላይ ውሃ እናፍስስበት!
ሰላም ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic