>

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና፤ ለኢትዮጵያውያን ፋይዳው ምንድን ነው? (ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ)

የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና፤ ለኢትዮጵያውያን ፋይዳው ምንድን ነው?
በፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ
መግቢያ
ኢትዮጵያኒዝምን ለማወቅ፤ ማን እንደፈጠረው? መቼ እንደተጀመረና? ማንን ጠቀመ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ጠቃሚ ነው። ቀጥሎም እኛ ኢትዮጵያውያን ለምን ስለ ኢትዮጵያኒዝም እስካሁን ሳናውቅ እንደቀረንና፤ ወደፊትም ለምን የኢትዮጵያኒዝምን ፋይዳ፤የማወቅ ፍላጎትና ጉጉት ሊያድርብን እንደሚገባ ቀደምት የነፃነት ታሪክ ትግሎችንና የወደፊቱንም በማንሳት ሃሳብ እንለዋወጣለን።
የኢትዮጵያኒዝም አፈጣጠር
1/ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና የተፈጠረው፤ በሃይማኖትና በፖለቲካ የጭቆና ቀንበር ውስጥ ወድቀው፤ እንዴት ነፃነታቸውን ለመቀዳጀት እንደሚችሉ ሲያስቡና ሲያሰላስሉ በነበሩ፤ ከአፍሪካ በባርነት የተጋዙ ጥቁር-አሜሪካውያን ነው። የፍልስፍናው ንድፈ- ሃሳብ፤ መንፈሳዊነትን ከሰው ልጆች ነፃነት ጋር ያጣመረ፣ ያቀናጀና ያስተሳሰረ ነው።
 የኢትዮጵያኒዝም ጅማሬ
2/ ኢትዮጵያኒዝም የተጀመረው በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ቢሆንም፤ ከ1776 የአሜሪካ የነፃነት ትግልን ተከትሎ እያየለና እየተስፋፋ መጣ። እ.አ.አ በ1808 ዓ.ም የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያንም በአሜሪካ ተቋቋመ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያኒዝም በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ እስከ
20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ተጠናክሮ ዘልቆአል። በመንፈሳዊ ዓለም የተሰማሩ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ቄሶችም ፍልስፍናው እንዲስፋፋ ብዙ ጥረት አድርገዋል። የነፃነት አፍቃሪዎችም አፍሪካ ለአፍሪካውያን ትገባለች! የሚለውን የፓን- አፍሪካን መሪ መፈክር ያስተጋቡት፤የኢትዮጵያኒዝም የነጻነት መንፈስ አደፋፍሮአቸው ነው።
ኢትዮጵያኒዝምና ዘረኝነት
3/ ኢትዮጵያኒዝምና የዘረኝነትን ደዌ ፍቱን መዳህኒት ነው። ዘረኝነት ጥቁሮችን ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ማግለሉ ብቻ ሳይሆን፤በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥም ከባድ ጫና ነበረው።
ለምሳሌ በሃይማኖት ጥቁርነትን እንደ ሰይጣን፤ ነጭነትን ደግሞ እንደ መላዕክት ማየት የተለመደ የነጭ ቄሶች እምነትና ተግባር ነበር። በዚህም መሰረት እውነተኛ መንፈሳዊ ነፃነት የሚፈልጉ የጥቁር ቄሶች፤ይህን የቀለም ግለላ በራሳቸው በጥቁሮች ላይ ሆን ብሎ የተደረገ መንፈሳዊ ኩነናን መሆኑን በመገንዘባቸው፤ ሕሊናቸውን ጎረበጣቸው። ከቶውንም ሊቀበሉት አልቻሉም።
ከዚህም አልፎ በገጠጠ የዘረኝነት መንፈስ፤የነጭ ቄሶች ሲሰብኩ የጥቁር ቄሶች ቀና ብለው ወደ ላይ አምላክን ከመማፀን ይልቅ፤ ወደታች አንገታቸዉን ደፍተው ቁልቁል እንዲያዩ የሚያደረጉባቸው ግዳጅና ማስፈራራት ጥቁሮችን አንገሸገሻቸው። በተጨማሪም የነጭ ቤተክርስቲያን ቄሶች፤ የጥቁር ቄሶች ምንም ያመራር ተግባር እንዳያገኙ መንገዱን ሁሉ ከረቸሙባቸው።
ይሁን እንጂ ጥቁሮች፤ እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ በራሱ ፍጡራን ልዩነት እንዲደረግ አይፈቅደም በሚል ደግነትና ቻይነት፤ በነጭ ቤተ ክርስቲያን ቤት የተንሰራፋው ዘረኝነት እንዲቀር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም። በዚህ ምክንያት እንደምዕመናን ወደ እግዚአብሔር ካላንዳች ዘረኝነትና አድሎ የሚያገናኝ አዲስ ቤተ ክርስትያን ለመመስረት ወሰኑ ።
 በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ ስሙዋ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ በተለይም፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የሚለው ተማጽእኖ፤ መድሎና ዘረኝነትን አስቀርቶ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መንፈሳዊ ጎዳና ሆኖ ስላገኙት፤ቤተክርስቲያናቸውን በኢትዮጵያኒዚም ፍልስፍና መሰረት ላይ አቆሙት። ከዚህ በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያ እንደ ብቸኛ ነጻ የጥቁር ሀገር ሁና ራስዋን ማስተዳደር በመብቃትዋ፤ ኢትዮጵያኒዝምን ለማስፋፋት ታላቅ ተምሳሌትነቱዋ ከመንፈሳዊ መሰረትነቱ አልፎ ዓለማዊ ጭቆናዎችን ለመቋቋም እና ነፃነት ለመቀዳጀት የማስቻል ጠቀሜታዋ የጎላ ሆነ።
የኢትዮጵያኒዚም ባሕሪያት
4/ ኢትዮጵያኒዚም፤መንፈሳዊ ነፃነት፣ በራስ መተማመን ፣ለራስ ክብር መስጠት ፣እራስን መቻል ፣የዉጭ ጭቆናን መቋቋም ፣ዓለማዊ ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወት ማነጽን፣ የተጨቆኑ ሰዎች በጋራ እንዲተባበሩ፣ የሰብአዊ መረዳዳትና እርስበርስ መተሳሰብን ያጨቀ አስተምሮት ነው።
ኢትዮጵያኒዚም የፈጠረው የነጻነት መንፈስና መነቃቃትም፤ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር አላቆ ልጆችዋ በነጻነትና በእድገት ጎዳና እንዲገስግሱ የሚያልመውን ፓናአፍሪካኒዝምን ፍልስፍና ወለደ።  የኢትዮጵያኒዚምና የፓንአፍሪካን ቅደመ ተከተልና ትሥሥርን ለአሁኑና ለመጪው ትውልዶች ለማስተላለፍ ሲባል ዛሬ በአዲስ አበባ ፤በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ የታላቁ ፓን አፍሪካኒስት ዶክትር ኩዋሜ ንክሩማህ ሀውልት ስር፤ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ተማጽእኖ ተቀርጾ ይገኛል ። የዚህን መልእክት ታሪካዊ አመጣጥ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለራሱም ሆነ ለልጆቹ ማስተማር አለበት።
የዛሬው ትውልድ እጅግ በጣም ሊያጤነው የሚገባው ጉዳይ አለ። ይኼም በአለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካ ገና እውነተኛ ነጻነትዋን አለመቀዳጀትዋን ነው። ይህንንም በማገናዘብ ነው፤ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦይ ኢምቤኪ፤እንደ ቅድመ 21ኛው ክፍለ ዘመን ትግሎች ሁሉ፤ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አፍሪካን ከዘረኝነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ፤ ኢትዮጵያኒዝምን በግድ መሰረት ማድረግ አለብን ሲሉ የሚያስተምሩት። እንደሚታወቀው እስከዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በደቡብ አፍሪካ በአሜሪካና በካሪቢያን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጎን ላልተጠናቀቀው የነጻነት ትግል ትልቅ ግልጋሎት ላይ በመስጠት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያኒዚም ያስመዘገባቸው ለውጦችና የገጠሙት ሳንኮች
5/ ኢትዮጵያኒዝም በዓለም መድረክ ያስገኛቸው ለውጦች ብዙ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ፤ የአፍሪካን ናሽናል ኮንግሬስ ያቋቋሙት በኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና ጥልቅ እውቀት የገበዩ የደቡብ አፍሪካ ቄሶች ናቸው። ለምሳሌ የመጀመሪያው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ጆን ላንጋቢሌሌ ዱቤ፤ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናቸውና አቁዋማቸው ታስረው ከተፈቱ በሁዋላ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ ፕሬዝዳንት ሁነዋል ።  የስማቸው ቅፅል ስምም፤ ‘ግልፅ ኢትዮጵያዊ’ ማለትም ሁልጊዜ ለአደጋ የተጋለጠ ይባል ነበር።
6/ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ብዙ መስዋትነት ተከፍሎበት የተገነባ ነው። እ.አ.አ በ1896 ፤በታላቁ ዳግማዊ ምንይልክ አመራር፤ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት በተስፋፊ ኢታሊያ ላይ የተቀዳጀቺው ድል ፤በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ይማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ተስፋን ያጎናፀፈ ነበር።
ይህንን ድል ተከትሎ የደቡቡ አፍሪካ ዘረኛ ነጮች በ1906 የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና እንደ አደገኛ የኢትዮጵያ ፕሮፖጋንዳ አድርገው ስለቆጠሩት፣ ሕግ አውጥተውና ፍልስፍናውን አንቋሽሸው ኢትዮጵያኒስቶችን ማሰርና አልፎ አልፎም መግደል ጀመሩ ። ቀጥለውም የኢትዮጵያኒዝምን እንቅስቃሴ እንደ አደጋና እንደ ሽብር አሰፍፊ ቆጥረው የወታደር ሀይላቸውን አጠናከሩ። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃቸው፤ በ1906 የዙሉ እንቅስቃሴን ቀጥሎም የባንባታና በኒያሳላንድና በሌሎችም አካባቢዎች የፀረ- አፓርታይድን ተቃውሞን ሊገታው አልቻለም።
ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፤ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ፤ እንደ ናይጀሪያ እና ጋና፤ በፈረንሳይ ስር የነበሩ እንደ ካሜሮን ያሉ ሀገሮች የኢትዮጵያኒዝምን ፍልስፍና በመጠቀም ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር አገናኝተው ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ኢትዮጵያኒዝም ሁነኛ ስልት ሆኖአቸዋል። በኬንያ እነ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ ሳይቀሩ አፍሪካ ለአፍሪካዊያን፤የሚለውን የፓን አፍሪካ ፅንሰ ሀሳብ ተከትለው እሰከ 1960 ዓ.ም ድረስ ተጠቅመውበታል። የራስ ተፈሪያኒዝም በካሪቢያን ሀገሮች የመነጨውና የተስፋፋውም ከዚሁ ከኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ጋር ተያይዞ ነው።
ባጠቃላይ ሲታይ፤ ኢትዮጵያኒዝም በተለያየ መንገድ ቢገለፅምና የተለያዩ ሰዎችና ሀገሮች ቢጠቀሙበትም፤ አላማው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛትና ከዘረኝነት ለማውጣት እንደ ችቦ መብራት ሆኖ እንዳገለገለና ግልጋሎቱን እንደቀጠለ ምንም ጥርጥር የለውም።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያኒዝም
7/ በኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና የጎላ መሆኑን በእሳካሁኑ ዳሰሳችን ለማሳየት ሞክረናል። አፅንኦት ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ግን ፤ ኢትዮጵያ የዓለም የመንፈሳዊ ምግብ ምንጭና ተምሳሌት መሆኗ ምንም የሚያሻማ ነገር እንደሌለው ነው። ኢትዮጵያን ሊጎዱዋትና ሊገድሉዋት የሚያሴሩ ሀገሮች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ማወቅ የሚገባቸው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በሰው ልጆች የነጻነት ትግል ውስጥ ያበረከተቺው ድርሻ ሕያው ሆኖ የሚኖርና ሊፋቅ የማይችል መሆኑን ነው።
8/ የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ ውስጣዊ ችግሮቹን ለመፍታት እውነተኛ ነጻነትን ማፍቀር አለበት። ከዚህም ባሻገር በጠባብ ክልሎች ሳይወሰን፤ አድማሰ ሰፊ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል።
ትውልዱ ለምን ኢትዮጵያ ለሌላው ዓለም ተምሳሌት ልትሆን በቃች የሚለውን ጥያቄ አንስቶና መልሱን አግኝቶ፤ ከሊሎች አፍሪካውያንና ነጻነት አፍቃሪዎች ጋር በማበር፤ እውነተኛ ነጻነት ለመቀዳጀት ሁነኛ የሆነውን ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ማስፋፍትና ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት።
 ይህን ወደ ጎን ትቶ፤ በዚያ እጅግ በጨለመ ዘመን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለነጻነታቸው የከፈሉትን መስዋትነት ከማክበር ውጪ፤ባልገባውና ባልተረዳው ታሪክ፤ በተንኮለኞች ፕሮፖጋንዳና በማያውቀው ጉዳይ፤ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ስልጣኔ መናቅና ማንቋሸሽ ትልቅ ስህተት መሆኑን በጥዋቱ ሊረዳው ይገባል። ኢትዮጵያ ታሪካዊ ሀገር ናት! ኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጭ ናት! ለተጨቆኑ ህዝቦች የሰጠችው የመንፈስ ጥንካሬ፤ ዛሬ ላገኙት ነፃነት እና እድገት ሕያው ምስክር ነው።
9/ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ለዓለም እንደጠቀመ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያንም ፍልስፍናውን እንደ ሌሎች ሀገሮች ተጠቅመን ለገጠሙን ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት እንችላለን ። ኢትዮጵያኒዝም የተመሰረተው በክርስትና ሃይማኖት ላይ የነጭ ቄሶች ዘረኝነትን በማስፋፋት ያደርሱ የነበረውን በደል እምቢ! ከማለት የተነሳ እንደነበር አይተናል። የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮችንም ታሪክ በኢትዮጵያኒዝም አመለካከት ስናየው፤ የእምነት ተቃውሞ በተነሳበቸው ጊዜና ምዕመናኑ ስደት ባጋጠማቸው ወቅት ኢትዮጵያ ያደረገችላቸው ድጋፍ ትልቅ ልዩነት እንዳመጣ እንማራለን።
ነብዩ መሐመድ ከመካ መዲና ወደ ኢትዮጵያ ምዕመናቸውን ከላኩ በሁዋላ በወቅቱ የነበሩ የአረብ ገዥዎች ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱትን ምዕመናን ለንጉስ ኢዛና ሙስሊሞችን እንዲገሉ ወይም ሀገር እንዲያስለቅቋቸው ወርቅና የተለያዩ የእጅ መንሻ እንስጥህ ቢሏቸውም፤ ለመልእክተኞች ሙስሊሞች የእኛ እህትና ወንድሞች ናቸው በማለት መልእክተኞችን አሳፍረው እንደመለሱ ታሪክ ያስተምረናል።
ነብዩ መሐመድ ኢትዮጵያ የፍትህ ሀገር ናት ብለው መስክረዋል ። እውነታቸውን ነው። ይኸም ፤ ኢትዮጵያ በወቅቱ ለሙስሊሞች ያደረገችው ድጋፍ፤ በ19ኛው መቶ ክፍል ዘመን ደግሞ በክርስትና እምነታቸው ላይ ተፅእኖ ለደረሰባችው ሀገሮች የነጻነት ተስፋና መመኪያ ሆና ከመገኝትዋ ጋር የሚመሳከርና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥም መመኪያነቱዋ ልዩ ስፍራ የሚያሰጣት ነው። የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በሁለቱም ሃይማኖቶች ላይ በተለያየ ዘመን ለደረሰባችው ተመሳሳይ ችግር መፍትሄ ያመጣ ፍልስፍና ስለሆነ፤ የሁለቱን ሃይማኖት ተከታዮች በመንፈስ የሚያስተሳስር ጉንጉን ስንሰለት ነው። ኢትዮጵያኒዝም ሁለቱም ሀይማኖቶች ለወደፊት በጋራ አብረው ተከባብረው ተባብረው በመስራት ኢትዮጵያን ለማሳደግ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።
ከኢትዮጵያውያን ምን ይጠበቃል ?
10/ በመጀመሪያ የኢትዮጵያኒዝምን ታሪክና ፍልስፍና በጥንቃቄ ማጥናትና ማወቅ ይገባናል ። ለምን የጭቆናን ቀንበር ለመስበር ሊሎች አግሮች ኢትዮጵያኒዝምን ፈልስፈው ተጠቀሙበት? ለምን ዛሬ የፖለቲካ ነጻነታቸውን የተቀዳጁ አገሮችሽ ኢትዮጵያኒዝምን ዛሬም አፍሪካን ከእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ለማላቀቅ ሁነኛ ፍልስፍና ነው ብለው ይመክራሉ? ለእኛ ኢትዮጵያውያንስ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ አገርና እንደ እውነተኛ የነጻነት ተምሳሌት የመታየቱዋ ፍይዳዎቹስ ምንድን ናቸው? የሚሉትንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳትና መልሶችን ማግኘት አለብን።
11/ እርግጥ ነው፤ ለመማር ትግስት፣ጊዜና ፍላጎት አስፈላጊዎች ናቸው። በተቃራኔው ሳይማሩ በድፍረት፣በጥራ ነጠቅነትና በኩረጃ ታሪካቸውን የሚያንቁዋሽሹ ዜጎች በየዘመኑ እንደሚከሰቱ ከታሪክ እንማራለን። በጨቅላነት እድሜ፣በአጉል ድፍረትና በጭቆና ስም ኢትዮጵያ ሀገራችን በሰው ልጆች የነጻነት ተጋድሎ የሰራችውን ልዩ ታሪክ ማወላገድና የእውነተኛ የፍልስፍና ምንጭ መሆንዋን ማንቋሸሽ ራስን ማዋረድና የአጥፊዎቻችን ተባባሪ ከመሆን አይዘልም። ዛሬ በኢትዮጵያ የተወሳሰቡና መፍትሄ ሊያገኙ የሚገባቸው ችግሮች አሉብን። ችግሮቻችንን በመንጫጫትና ጥላቻ በመርጨት ሳይሆን፤ በመደማመጥና በፍቅር፤ የመለያይ ምልክቶችን በማጉላትና በማጋነን ሳይሆን፤ በማቀራረብና በማስተሳሰር እየተወያየን፤ ልንፈታቸው እንችላለን። ኢትዮጵያኒዝምን ከራሳችን ማንነት ጋር አዋህደን ፤በስልጣኔና በእድገትን ጎዳናዎች እየገስገስን ታላቋን በስልጣኔ ቀደምት የሆነችውን ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላልን።
መደምደሚያ
12/ የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና በዓለም ተሰራጭቶ ብዙ ሕዝቦችና አገሮችን ከባርነት ቀንበር ነጻ እንዳወጣ ሁሉ፤ በኢትዮጵያም ተስፋፍቶና ዳብሮ አገራችንንም ሆነ መላው አፍሪካን ከድሕነት፣ከዘረኝነትና ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እንዲያለቅቅ ሊጠናና ሊጎለብት ይገባል።
ስለሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በሰለጠነ መነገድ መወያየትና ለውጥ ለማምጣት መትጋት ይኖርብናል። በእርቅና ሰላም የዳበረና የጎለበተ አዲስ አስተሳሰብ ለማምጣት ሀገራዊ የመግባቢያ ውይይት ያስፈልጋል።
ባለፉት ዓርባ አመታት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የዉይይት መድረክ ለመፍጠር ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢካሄዱም፤ እስካሁን ግን አልተሳካልንም። ያለንበት ተጨባጪ ሁኔታ የብሄራዊ መድረክ
መፈጠርን የግድ የሚል ነው።
ኢትዮጵያ የት ነው ያለችው? ወዴየት እየሄደች ነው? ዛሬ ያለችበትስ ጎዳና ትክክል ነው? ወይስ አይደለም? 
በጋራ በመወያየትና በመግባባት አሁን ሀገራችን ካለችበት የተወሳሰበ ችግር ውስጥ መንጠቀን ልናወጣት ይገባል ።ብሔራዊ አንድነትንም ለመፍጠር የኢትዮጵያኒዝም፤ ቅንነት፣ መተሳሰብ፣ መግባባት፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ምህረትንና፣ መንፈሳዊነት ለኢትዮጵያውያን እጀግ ጠቃሚ ነው። ባሕላዊ ልዩነቶቻችን ፀጋዎቻችን እንጂ መለያያችን ሊሆኑ ከቶውንም አይገባም። ራሳችንን ጠንቅቀን ሳናውቅ፤በጥራዝ-ነጠቅና በሀሰት በተለወሱ እውቀቶች፣በጥላቻና ጽንፈኝነት ስሜት በጨለማ የምንዳክር ከሆነ የኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ ትውልድ ተስፍዎች ልንሆን አንችልም። እንደውም ለዛሬው የአፍሪካ ትውልድ የፍቅር ፀር ከመሆናችን  ባሻገር፤ ተተኪውንም ትውልድ ለባርነት ዳርገነው የምናልፍና፤ የታሪክ ስፍራችንም የስግብግቦችና የሁዋላ ቀሮች ጎራ ሆኖ ነው የሚቀረው።
ኢትዮጵያዊነትን እናስቀድም! ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነትን እንደ ጀመረቺው ሁሉ፤ ወደፊትም የመላው አፍሪካን አንድነት መገንባቷ ጥርጥር የለውም! የኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍና ለ21ኛው ክፍል ዘመን ታላቅ ለውጥ አምጪና አማራጭ የለሽ ፍልስፍና ነው።
ራእያችን ታላቁዋን አፍሪካዊት ኢትዮጵያን ማየት ነውና እግዜአብሄር ይርዳን። አሜን።
Filed in: Amharic