>
5:13 pm - Thursday April 20, 7256

የጸጥታ አስከባሪውም ሆነ አገዛዙ ምንም የማለት የሞራል ብቃትና መብት የላቸውም!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

የጸጥታ አስከባሪውም ሆነ አገዛዙ ምንም የማለት የሞራል ብቃትና መብት የላቸውም!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
* አገዛዙ በግልጽ በይፋ ሐሰተኛ መረጃ እየለቀቁ፣ ጠባብና የዜጎችን መብት የሚፃረር ጠንቀኛ ቅስቀሳ እያደረጉ የጎሳ ግጭት የሚቀሰቅሱ እንደ እነ ጃዋር ያሉ አሸባሪዎችን እንደፈለጉ እንዲሆኑ ነፃ የለቀቀ ሆኖ እያለ፡፡
* የአሸባሪነትና የውንብድና ተግባራቸውን ሲፈጽሙ የሚያሳይ ፎቶ እና ቪዲዮ (ምሥለ አካልና ትዕይንተ ሁነት) በየ ፌስ ቡክ አካውንታቸው (መጽሐፈ ገጽ መዝገባቸው) የሚለጥፉ ነፍነበላ አሸባሪ ወንበዴዎች ያለምንም ሥጋት በነጻነት እንደውም በወታደራዊ አጀብ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ፡፡
* የቡራዩ፣ የአሸዋ ሜዳ፣ የአዲስ አበባ ዙሪያ አካበቢዎች ሕዝብ በኋላ ላይ የደረሰውን የአሸባሪና የውንብድና ተግባር ያደረሱት አሸባሪዎች ጥቃቱን ሊያደርሱ እንደሆነ ጥቃቱ በስፋት መፈጸም ከመጀመሩ ሁለት ሦስት ቀናት በፊት ሕዝቡ በመረጃ የተደገፈ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ የጥቃት እርምጃዎች መረጃዎችን አቅርቦ “እባካቹህ ድረሱልን አድኑን!” እያለ አቤቱታ አቅርቦ በነበረበት ሁኔታ የጸጥታ አካሉ ይሄንን የድረሱልን ጥሪ ሆን ብሎ “ጆሮዳባ ልበስ!” ብሎ በሕዝብ ላይ እልቂት እንዲፈጸም ያደረገ ሆኖ እያለና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ እንዲሁም ከወንበዴ አሸባሪዎች ጋር ተባብረው ይህ ግፍ በሕዝብ ላይ እንዲፈጸም ያደረጉ ወንበዴ የጸጥታ አካላት በሥራ ላይ ባሉበት ሁኔታ፡፡ ለነገሩ ሲጀመር ጥቃቱን ማን እንዲፈጸም አደረገውና???
* ግዙፍ ግዙፍ ወንጀል ውንብድና ዝርፊያ የፈጸሙ ሌባ፣ ነፍሰበላ፣ አሸባሪ፣ ወንበዴ የአገዛዙ ባለሥልጣናት ምናቸውም ሳይነካ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና እንዲኖሩ አድርጎ ባለበት ሁኔታ፡፡
የሕግ አካሉ ወይም አገዛዙ በሰልፍ ላይ የተሳተፈውንም ያልተሳተፈውንም የአዲስ አበባ ወጣት የዜጎችን መብት በጣሰና ሕገወጥ በሆነ መንገድ “ያልተፈቀደ ሰልፍ ተሳትፋቹሃል!” ምንትስ በሚል ንጹሐን ዜጎችን ሊያስር፣ ሊያሰቃይ፣ ሊቀጣ፣ ሊያርም የሚችልበት ምንም ዓይነት የሞራልም (የቅስምም) ሆነ የሕግ ብቃትና መብት የለውም!!! እራሳቸው የአገዛዙ አካላት በሙሉ ተሰብስቦ በየወንጀሉ እየተፈረደበት ወኅኒ መወርወር ነው ያለበት!!!
ሲጀመር ማስፈቀድ የሚባል ሕጋዊ አሠራር የለም የአፈና አሠራር እንጅ!!! የዚህ አፈሳ ምክንያትና ዓላማ ከአራት ወራት በኋላ የሚደረገውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤትና ከንቲባ ምርጫ ላይ ለተቃዋሚዎች በንቃት ሊቀሰቅሱና ሊያስተባብሩ የሚችሉ ወጣቶችን አስሮ በመያዝ ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር በማድረግ ለማሸነፍ በማሰብ የሚደረግ አፈሳ ነው ሌላ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ነገሮች ወደየት አቅጣጫ እየሔዱ እንደሆነና የተጃጃልክበት የነዐቢይ ድራማም (ትውንተ ሁነትም) ማጃጃያና ጊዜ መግዣነት ጥርት ብሎ እየታየ እንደሆነ በዐይንህ ዓይተሃል በጆሮህ ሰምተሃል፡፡ በግልጽ አነጋገር እነ ዐቢይ የቱንም ያህል አንድነት፣ ኢትዮጵያ ምንንትስ እያሉ የቱንም ያህል ለማጃጃል ቢጥሩም በተጨባጭ ግን በወያኔ የሚደገፍ ጠባብ የኦሮሞ አገዛዝ ተጭኖብሃል፡፡ ኦሮሞን ለይቶ ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ እየተፈጸሙ ያሉ ሕግን ያልተከተሉ ሹመቶች፣ መመሪያዎች፣ ትዕዛዞችና አሠራሮች የሚያረጋግጡት ይሄንን ነው፡፡
ከዚህ በኋላም በነዐቢይ የሚጃጃል ካለ ማሰብ የተሳነው ዘገምተኛ መሆኑን ለራሱ እርግጠኛ ይሁን፡፡ ነገሮች ከመወሳሰባቸውና ለመፍትሔ ከማስቸገራቸው በፊት እንደምንም ጠንክረህ መፍትሔ እንድታበጅለት ሁኔታው ግድ ይልሃልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ወገብህን አስረህ ፈጥነህ ተነሥ!!! ዋ በኋላ ዝም ያልክ ጊዜ!!! ብትነሣ ነው የሚሻልህ ተነሥ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic