>
5:13 pm - Thursday April 19, 6125

አዲስአበቤ አሁንም ከኢትዮጵያዊው አብርሃም ሊንከን ጐን እንቁም!!! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

አዲስአበቤ አሁንም ከኢትዮጵያዊው አብርሃም ሊንከን ጐን እንቁም!!!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
አዲስአበቤዎች ከፊታችን የህልውና አደጋ ተጋርጦብናል። አዲስአበቤ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የጀመረው ንቅናቄ ያስፈራቸው የመንፈስ ጐልያዶች ሰይፋቸውን መዘውብናል። ተስፋ የጣልንበት ዛሬም ተስፋችን ያልተሟጠጠበት የዶክተር አቢይ መንግስት ግራ በሚያጋባ ሁኔታ የጅምላ እስሩን አይቶ እንዳላየ ሆኗል። ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኗል። ከሁኔታዎች እንደምንረዳው የለውጥ ሃይል የሆነው የዶክተር አቢይ ቡድን የሴራውን ባለቤቶች በሚገባ አውቋቸዋል። ይህም ሆኖ  ከኪሳቸው እያወጡ “ሳሪስና መርካቶ ያለ አዲስአበቤ 43 ኦሮሞ ገደለ” ብለው የሩዋንዳ መሰል እልቂትና ብጥብጥ ሲደግሱ መንግስታዊ ምላሽ ለመስጠት አልፈለገም። እናቴ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ እንደሚባለው አዲስአበቤ አጠፋ የተባለው ነብስ ከ43 ወደ 60 አድጓል። ነገ 100 አሊያም 200 የማይሆንበት አንዳችም ምክንያት የለም። ከነገ ወዲያ አንድ ሺህ ይደርሳል።
አዲስአበቤ ሆይ! አደጋ መጣሁ መጣሁ እያለህ ነው። ሁኔታዎች አደገኛ አቅጣጫ እየያዙ ነው። በዚህ ከቀጠለ ሩዋንዳን የመሰለ አደገኛ የታሪክ ክስተት በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ አያንዣብብም ማለት አይቻልም። ” መርካቶ ላይ ጉራጌ ችግር ፈጥሮብሃል” የሚል የእርምጀሰ ውሰድ መልእክት ከአክራሪው ቡድን የተላለፈው ዝም ብሎ አይደለም። የተጠና፣ የታቀደ፣ ህዝብን መሃል መርካቶ ላይ ለማፋጀትና ለማተራመስ በማሰብ የተዘጋጀ ውጥን ነው። እርግጥም አክራሪው ቡድን እሳቱን ማቀጣጠል ከመርካቶ መጀመሩ እልቂቱን ወደ ስበት ማእከሉ ለመጐተት በማሰብ ነው። እርግጥ ይሄ ለአዲስአበቤ የመረረ ጥላቻና የበታችነት ስሜት ያለው ቡድን ያልተገነዘበው ነገር አዲስ አበባ ውስጥ አንዴ እሳቱ ከተቀጣጠለ ሁላችንም ሰለባ እንሆናለን እንጂ ማንም ወገን አሸናፊ የሚሆንበት እድል የለም።
አዲስአበቤ ሆይ! የዶክተር አቢይ የለውጥ አስተሳሰብ ተሸንፎ ስልጣን በእነዚህ አደገኛ ሃይሎች ከተጠለፈ የሰነቅነው ተስፋ ወደ ጥልቅ ባህር ይወረወራል። እነዚህ አገር ለማፍረስ ቆርጠው የተነሱ አዲስ በቀል ዘረኞች ዋነኛ አላማቸው የለውጥ ሃይሉን ጉዞ መቀልበስ ነው። ይሄ ካልተሳካላቸው የለውጥ አስተሳሰቡን በማስገደድ ጠምዝዞ ማስቀየር ነው። ይህን እኩይ ተልእኮአቸውን ለማስፈፀም ከህውሓት ቆሞ ቀር ቡድን እና ለውጡ ይጐዳኛል ብለው ከሚያምኑት ጋር የሶስትዬሽ የጋራ ግንባር ፈጥረዋል። ይህ በሶስት ትናንሽ ጭንቅላት የተፈጠረው የጋራ ግንባር መዳረሻው አንድ ባይሆንም ታላቁን የለውጥ አጀንዳችንን ለመቀማት የሚችሉበት እድል ሠፊ ነው። ሰሞኑን ዶክተር አቢይ  ሽግግር እያካሄደ አይደለም፣ ብቃት የለውም፣ አገሪቷ ላይ ሰላም ማስፈን ስላልቻለ ከስልጣን ይውረድ የሚል መፈክር ይዘው ብቅ ያሉት በዚህ ምክንያት ነው።
አዲስአበቤ ሆይ! ይህንን እና የመሳሰለውን ሁኔታ ሁላችሁም በያላችሁበት የታዘባችሁት ይመስለኛል። አሁን ያለው ጥያቄ እያንዳንዳችን ምን ልናደርግ እንችላለን የሚለው ነው። በተለይ ከሶስት ሚሊዬን የሚበልጠው አዲስአበቤ ወጣት መዲናውን አልፎ ሄዶም አገሩን እንዲያድን ምን አይነት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እናቀጣጥል የሚለው “በጊዜ የለንም” እሳቤ ምላሽ ማግኘት አለበት። ለጊዜው የማላስታውሰው ታዋቂ ፈላስፋ ” አለምን አሸንፈህ ለመያዝ ከፈለክ ፣መጀመሪያ ራስህን አሸንፍ” ይላል። If you want to conqure the world, conquer yourself first!
እናም ራሳችንን እናሸንፍ። ከተስፋ መቁረጥና ጨለምተኝነት እንውጣ። የተጀመረውን መነቃቃት ተቋማዊ ይዘት እንስጠው። የማንም ባለጊዜ እፉኝት ዘረኛ በበታችነት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደ መንገድ ጭቃ እንዳይረግጠን ንቅናቄያችንን እናቀጣጥል። የአዲስአበቤ የተባበረ ሃይልና አቋም ዘረኞቹን ከመድፈቅ ተሻግሮ የኢትዮጵያዊነት የድል ምልክት ነው። በአገር ደረጃ የተነዛውን ሽብር፣ እልቂትና የአገር ጥፋት ልንከላከል እንችላለን። የእኛ የኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት የታፈረና የተከበረ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ክቡርነቱን እናስጠብቅ።
የአዲስ አበቤ ወጣቶች! እኛ መንቀሳቀስ ከጀመርን በስልጣን ላይ ያለውና ታላቅ ራዕይ ያነገበው የዶክተር አቢይ ቡድን ከጐናችን ይቆማል።  ያለምንም ጥርጥር ይረዳናል።  እዚህ ላይ እንድትገነዘቡት የምፈልገው ቁምነገር ሶስት የጋራ ግምባር የፈጠሩት የዘረኛ ስብስቦች ፍላጐታቸው እኛን የለውጥ አራማጅ ከሆነው ዶክተር አቢይ ጋር ማጣላት ነው።
 በእኔ እምነት ዶክተር አቢይ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ሊጫወት የሚፈልገው ሚና የአሜሪካ ተወዳጅ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን የተጫወተውን ይመስለኛል። በለውጥ አመራር ውስጥ 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን ” የወደፊት መውደቅ” ተምሳሌት ተደርጐ ይወሰዳል። ወደፊት የሚወድቅ ሰው ብርቱ ፍላጐት፣ የመለወጥ ጽናት፣ የኃላፊነት ስሜት፣ ለራስ የሚሰጥ ክብር፣ ከመቀበል ይልቅ ለመስጠት ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። አብርሃም ሊንከን እንደዚህ አይነት ስብእና እንዳለው ይነገራል። ከሁሉም በላይ ግን አብርሃም ሊንከን የተገኘው የአሜሪካ ጥቁሮች ጭንቀት እጅግ በከበደበትና የአሜሪካ አንድነት በተናጋበት ዘመን ነበር። ኢትዮጵያዊው አብርሃም ሊንከንም ከባህሪም ሆነ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተመሳሳይ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic