>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9864

ዘር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ በህግ ይገደብ (አበበ ገላው)

ዘር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ በህግ ይገደብ

አበበ ገላው

ዛሬ አገራችን የገጠማት ቀውስ ድንገት የመጣ አይደለም። ላለፉት 27 አመታት ህዝብን ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመዝረፍ ሲባል የተረጨው የዘር መርዝ ውጤት ነው። ለበርካታ አመታት የዘር ፖለቲካ ንግድ የመጨረሻ ትርፉ ማለቂያ የሌለው ጥፋት መሆኑን ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያን እያጠቀሱ ብዙዎች ማስጠንቂያ ሰጥተዋል፣ ተንትነዋል ጽፈውበታል።

ህወሃቶች ከዘረፋና አፈና ባሻገር ለማሰብ ባለመቻላቸው ዘረኝነትን ህገ መንግስታዊ ሽፋንና ክልላዊ ቅርጽ ሰጥተው ህዝቡን እንደጠላትና ባይተዋር እንዲተያይ አድርገውታል። በውሸት ፕሮፓጋንዳ እያደናገሩና እጃቸውን በደም እያጨቀዩ በዝርፊያ ደልበው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል እሳቤ አገሪቷን ጫፍ ላይ አድርሰዋታል።

በዘር ምክንያት መፈናቀሉና መገደሉ ዛሬ ወደ መሃል አዲስ አበባ መምጣቱ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያጘን አደረገው እንጂ በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች በየግዜው የሚያገረሽ ለቡዙ ድሆች ህይወት ወጥፋትና ቤተሰቦች ህይወት መመሰቃቀል ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። 

በጄኔቫ የሚገኘው የውስጥ መፈናቀል ተከታታይ ማእከል (Internal Displacement Monitoring Center) ከጥቂት ቀናት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በስድስት ወር ብቻ በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ህዝብ ተፋናቅሎ አገራችን እነ ሶሪያን ቀድማ አንደኛ ሆናለች። 

ይህ ሁሉ እንግዲህ የዘር ፖለቲካ አስከፊ ገጽታ ነው። ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ እያዛቡ የጥላቻ ፖለቲካ እያራጋቡ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱ ጽንፈኞች አደብ እንዲገዙና በህግ ካልተዳኙ ካልተደረገ ይቺ አገር ወደ ከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ማምራቷን ለመተንበይ ነብይ መሆን አይስፈልግም። 


አሁንም ለዚች አገር የመጨረሻው እድል ህዝብን ከዘር ፖለቲካ እና ስካር መመለስ ነው። የሁለተኛው የአለም ጦርነትን ጨምሮ በጣም አውዳሚ ግጭቶችና ጦርነቶች የተለኮሱት በጽንፈኛ የዘር ብሄረተኞች ምክንያት ነው።


በሌሎች አገሮች አንዱን ህዝብ በሌላ ላይ የሚያነሳሳ የጥላቻ ቅስቀሳ (hate speech) በህግ የታገደ ወንጀል ነው። እነ ዶክተር አብይ አገሪቷ ከዚህ እርስ በርስ ከሚያባላ የዘር ፖለቲካ እንድትወጣ መስራት ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ መንደር ሳትሆን አገር ነች። አገርን መንገባት ከባድ ነው፤ ማፍረስ ግን ቀላል ነው። እንኳን በአገሩ ላይ ይቅርና በስደት የሚኖር ሰው እንኳን “ሰፋሪ መጤ…” እያሉ ማሸማቀቅ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። ከዚህ አስነዋሪ ቅስቀሳ በስተጀርባ ዛሬም አትራፊዎቹ የጥላቻ ፖለቲካ ነጋዴዎች መሆናቸው እየታወቅ ችላ ሊባል አይገባም።

Filed in: Amharic