>

ያ የማውቀው መልካም የኦሮሞ ወጣት ሁሉ ወደየት ሄደ? (አሰፋ ሀይሉ)

ያ የማውቀው መልካም የኦሮሞ ወጣት ሁሉ ወደየት ሄደ?
አሰፋ ሀይሉ
ዕድሜ ልካችንን – ከየሀገሩ የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ጋር ኖረናል፡፡ ከኦሮሞ ልጆች ጋር አብረን ተጫውተን ተጣልተን አድገናል፡፡ ከኦሮሞ ወጣቶች ጋር አብረን ተራግጠን ዕድሜያችንን አሣልፈናል፡፡ ከኦሮሞ እናቶች፣ ከኦሮሞ አባቶች ጋር – ክፉን በጎን ጊዜ – በቤታቸው፣ በቤታችን፣ በሀገራቸው፣ በሀገራችን – አሣልፈናል፡፡
እኔ በግሌ – በዚህች ዕድሜዬ – ለተለያዩ ዓመታት – በእድገቴ፣ በኑሮዬ፣ በሥራዬ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እግር እየጣለኝ – ከተለያዩ የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ጋር ኖሬያለሁ፡– ከሐረር እስከ ጉርሱም – ከበደሌ እስከ ባሌ – ከቦረና እስከ ሞያሌ – ከአርሲ እስከ አዋሽ – ከሠላሌ እስከ ድሬ – ከወሊሶ እስከ ጅማ – ከወሎ እስከ ወለጋ – ከሸኖ እስከ ኔጌሌ ድረስ – ብዙ ዓይነት የኦሮሞ ማኅበረሰቦችን አይቼያለሁ፡፡ ከእጃቸው በልቼያለሁ፡፡ ንፁህ ወተት ከእጃቸው ጠጥቼያለሁ፡፡ ተመርቄያለሁ፡፡ የምስኪኑንም እምባ – ልቤን አስተክዤ – አብሼያለሁ፣ ሐዘኑን ተጋርቼያለሁ፣ በደስታው አብሬ ሆሆ ብዬ ጨፍሬያለሁ፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ – የኦሮሞ ማኅበረሰብ – እጅግ መልካም፣ እጅግ ለሰው ገር፣ እጅግ ለጋስ፣ እጅግ ታጋሽ፣ እጅግ ከማንም የፈጠነ ይቅር-ባይ፣ እጅግ ሆደ-ሰፊ፣ እጅግ ባህሉን የማይለቅ፣ እጅግ ፈሪሃ እግዜሩን የማይለቅ፣ እጅግም መክፋት እጅግም መጠፋፋት የማይወድ – ለኢትዮጵያችን የባህል መልካም ሽቱውን ሲነሰንስ የኖረ – ታላቅ፣ የጀግናም፣ የዘካሮችም፣ የጎበዛዝትም፣ የሽማግሎችም፣ የመልካሞችም ሕዝብ ነው – የኦሮሞ ሕዝብ – እንደ ሕዝብ ከታየ፡፡ ይሄ የትም ሂድ የት – በአይንህ በብረቱ አይተህ የምትፈርደው እውነት ነው፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል – ለራሱ የመልካምነት የባህል ልጓም አበጅቶ – ስታለቅስ ካዬ አብሮህ አንጀቱ እንስፍስፍ ብሎ እንባውን የሚያረግፍልህ – ስትራብ ቢያይ እንዳላየ ሆኖ ማለፍን ሆዱ የማይችልለት – ድንቅ ሕዝብ ነው፡፡ እኔ የማውቀው የኦሮሞ ሕዝብ ያ ነው፡፡ እኔን ያሣደገኝ የኦሮሞ ሕዝብ ያ ሕዝብ ነው፡፡
እነዚህኞቹስ ከወደየት መጡ? እውን እነዚህኞቹ የገዛ ወገኖቻቸውን እንደሽፍታ በሌሊት ቤቱ ገብተው እናት አባት፣ ልጅ እህት ወንድም፣ ሚስት ባል፣ ጎረቤት አሮጊት ሽማግሌ የሚያርዱ፣ የሚቀጠቅጡ፣ የሚገድሉ – እውን እኒህን – የደጋጎቹ የኦሮሞ እናት ማህፀን የፈጠረቻቸው – የኦሮሞ ልጆች ናቸው?? እውን እነዚህ የቁጣ ስሜታቸውን ባገኙት ንፁህ ወንድማቸው ላይ የሚወጡ – ያውም ክቡሩን ህይወቱን በጠራራ ፀሐይ የሚቀጥፉ – እውን የእዚያ ጠንቅቄ የማውቀው የደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች ናቸው?? እውን ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ለወገኖቻቸው የሚከፍሉት ውለታ ይሄ ነው??
እውን የእዚህ በቁጣ የገነፈሉ ወጣቶች አያቶችና ቅድመ አያቶች በዚህች ሀገር ሁላችንም ተስማምተን፣ እናት ሀገራችንን ከጠላት በወንድማማችነት ተያይዘን ቆመን እየተከላከልን ልጆቻችንን በሠላም በጋራ እያሳደግን በሠላም እያረስን በሀገራችን በነፃነት እንድንኖር ሲሉ – እልፍ አዕላፍ የኦሮሞ ጀግኖች አያቶቻችን – ፈረሶቻቸውን ሸምጥጠው፣ ጋሻ ጦራቸውን አንግበው – ለዚህች ሀገር ሕዝቦች ነፃነትና ሠላም፣ ፍትህና አንድነት – ነፍሳቸውን አልሰጡም…..??
እውን ከኦሮሞ ደጋግ እናቶች ማህፀን የወጡ የኢትዮጵያ ጀግኖች «አቢቹ ነጋ ነጋ!» እያሉ ለዚህች ሀገር አንገታቸውን ለሠይፍ አልሰጡም? ለሚወዱት ወገኖቻቸው ለእኛ ለሁላችን ደማቸውን በጠላት ፊት አላዘሩም?? ከደጋጎቹ የኦሮሞ እናቶች – ከጀግኖች አያቶቻችሁ የወረስነው – ይሄን አቅመ-ደካማን በቤቱ ከተኛበት ገብቶ ማረድን ነው? ይሄ ነው የኦሮሞ ግብሩ?? የት ሄደ ያ የማውቀው ስጠማ ውሃ ስለው ወተት ያጠጣኝ የኦሮሞ ደግነት?! የት ሄደ ኦሮሞ?! የት ሄደ መልካምነት?! የት ሄደ ያ ሆደ-ሰፊነት?! የት ነው የጣልነው ያንን የኦሮሞ አባቶች ምክርና ቁጣ?!
ዛሬ እኛ ሠላም ሆነን፣ ወደምንሻው የእፎይታ መንገድ እየሄድን ያን ሁሉ የአባት የእናቶቻቸውን የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ታላቅ ውለታና መስዋዕትነት ወደ ጎን ብለው – የዛሬ በቁጣ የነደዱ የኦሮሞ ወጣቶች – የገዛ ንፁህ ወገናቸውን – እንዲህ የዘርማንዘር ቂም እንዳለበት እንደክፉ ጠላት – ምን አድርጓቸው ነው – እንዲህ የሚጨፈጭፉት?? እውን ይሄ ነው ወይ የእናት አባቶቻችን ቃልኪዳን?? ይሄ ነው ወይ የእነ አብዲሣ አጋ፣ የእነ ጃጋማ ኬሎ፣ የእነ….ስንትና ስንት ሺህዎቹ የኦሮሞ ጀግኖች ቃልኪዳን?? እውን ይሄ ነው አዲሱ የኦሮሞ ወጣቶች ኢትዮጵያዊነት??!! ይሄን ነው ተምረን ያደግነው??
ያ የማውቀው የኦሮሞ ሕዝብ ወደየት ሄደ?? ያ አብረን ጥርስ የተሳበርነው፣ አብረን አጋም ቀጋ ለቅመን የበላነው፣ አብረን ችቦ ያበራነው፣ አብረን «ፎረሮ ፎረሮ» ብለን ዝናብን ከሠማይ አንጋጠን የለመንነው – ያ የማውቀው የኦሮሞ ሕዝብ፣ ያ የማውቀው ደጉ የኦሮሞ ወጣት፣ ያ የማውቀው መልካሙ የኦሮሞ ጓደኛዬ – ወዴት ሄደ? ምን ጅብ በላው ደጉን ኦሮሞ??!!!! ምን ጉድ መጣብን??!!
አምላካችን መስሚያውን መስማሚያውን ይስጠን፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ አምላክ ለኢትዮጵያውያን ልጆች ሁሉ – የማይቻለውን የሚችሉበትን ወገናዊ ልብ ስጥ፡፡ የብዙሃን እናት – ምስኪኗ እናት ሀገራችን – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር በልጣ – ትኑር፡፡
Filed in: Amharic