>

በንጹሀን ደም መነገዱ እስከመቼ? ማቆምያውስ የት ይሆን??? (ሙሉነህ እዩኤል)

በንጹሀን ደም መነገዱ እስከመቼ? ማቆምያውስ የት ይሆን???
ሙሉነህ እዩኤል
በቅድሚያ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማና እንዲሁም ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሉ ከተሞች በተለይ ደግሞ በቡራዩ ሆነ ተብሎ በዘራቸው ምክንያት ጥቃት ደርሶባቸው ህይወታቸው ለጠፋ፥ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑት ሁሉ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማኝ መግለጽ እፈልጋለሁ። ይህ እንዳይከሰት አስቀድሞ በማሰብ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች የአቅማችንን ሁሉ ማድረጋችንን ለመግለጽ እፈልጋለሁ። ዜጎች ግጭት ውስጥ እንዳይገቡና በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እኔም ሆንሁ ሌሎች አመራሮች ምን አደረግን በዝርዝር መግለጽ የሚያስፈልግ መስሎ ይሰማኛል። ይህን እንድገልጽ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከእሳቸውና ከሚመሩት ድርጅት የማይጠበቅ እጅግ አሰፋሪና ፍጹም በሀሰት የስም ማጥፋት ውስጥ ስለገቡ ይህን በዝምታ ማለፍ ደግሞ የአቶ በቀለን ዋሾነት በይሁንታ እንደመቀበል የሚያስቆጥር በመሆኑ ይህን በግሌ ልቀበለው ባለመቻሌ ነው።
ጥቂት ቃላት ስለአቶ በቀለ ገርባ
ለመጀመሪያም ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ አቶ በቀለ ገርባን ያነጋገርኳቸው ከጥቂት ወራት በፊት ወደአሜሪካን አገር ባቀኑበት ወቅት ነው። እኔና እሳቸው በአካል ተገናኝተንም ሆነ ተያይተን አናውቅም። የተነጋገርነው በስክል ነበር። በእኔ ጠያቂነት ከእሳቸው ጋር በስልክ ያስተዋወቀን አቶ ብርሃነመስቀል አበበ ስኜ ነው። አቶ ብርሃነመስቀል የእሳቸውን ስልክ ለእኔ የእኔን ደግሞ ለእሳቸው ልኮ አስተዋወቀን። ከዚያ በኋላ እኔ ደውዬላቸው ከእንድ ሰአት በላይ ተነጋግረናል። ከዚያም ሚኔሶታ ደርሰው ሲመለሱ ስልክ ደውለው በአካል ተገናኝተን ልንነጋገር ተቀጣጥረን ተለያየን። ከሚኔሶታ መልስ ግን እሳቸውም አልደዎሉልኝም እኔም በሚኔሶታ ቆይታቸው የሰጡት ቃለመጠይቅ በስልክ ባነጋገርኋቸው ወቅት ካጫወቱኝ ነገር በመንፈስም ሆነ በፍሬነገር እጅግ ተቃራኒ የሆነና በጭራሽ ከእሳቸው ያልጠበቅሁት ስለነበር ላገኛቸው እንዳልፈልግ ከለከለኝ።
ትላንትና ደግሞ በአቶ ጀዋር ቴሌቪዥን ቀርበው በአዲስ አበባና አካባቢው ከኦነግ አመራሮች አቀባበል ጋር ተያይዞ በቄሮዎችና በአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ተፈጥሮ ለነበረው ግጭት አርበኞች ግንቦት 7ን ተጠያቂ ለማድረግ ሲሞክሩ ተመልክቼ በጣም አዘንኩ። እኔም ሆንሁ ሌሎች የንቅናቄያችን አመራሮች ይህ እንዳይከሰት ብዙ ደክመን እንደነበር ከእርሳቸው የተሰወረ አልነበረም። ምክንያቱም እሳቸው ያንን ቃለመጠይቅ ሲሰጡ ከጀዋር ጋር ነበሩና። አቶ ጀዋር ደግሞ በእኛ በኩል የነበረውን ጥረት ሙሉ በሙሉ ያውቅ ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው፥
ሀሙስ መስከረም 3 ቀን ጥዋት አቶ ጀዋርና እኔ ቀጠሮ ነበረን። አቶ ጀዋር ቤቱ ቁርስ ጋበዘኝ። ቁርስ እስከሚቀርብ ድረስ እኛ ስላወጣነው ጋዜጣዊ መግለጫና ያንንም ለማብራራት በእርሱ ቴሌቪዥን አንድ ሰው በአማርኛ አንድ ሰው ደግሞ በኦሮምኛ ማብራሪያ እንዲሰጡ እንዲያመቻች ሃሳብ አቅርቤ እርሱም ፈቃደኛ በመሆኑ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በአማርኛ፥ አቶ አበበ ቦጋለ ደግሞ በኦሮምኛ መግለጫውን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጡ። ከዚህ በተጨማሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከኦነግ አመራር አባላትና ከፖሊስ ኮሚሽነሩ ጋር ሆነው ግጭቶች እንዳይከሰቱ በሁሉም ወገን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አደረጉ። ከዚህ በተጨማሪ እኔና አቶ ጀዋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ክርክር ቢጤ አደረግን። ስለግል ህይወታችንም ጥቂት አውግተን፥በሌሎች ጉዳዮች ላይ የጀመርነውን ውይይት ከተቻለ አቶ ነአምንን ባለበት ልንነጋገር ተቀጣጥረን ተለያየን። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አቶ በቀለ ገርባ ግን እሳቸውንና እመራዋለሁ የሚሉትን ድርጅት የማይመጥን ቃለመጠይቅ ሰጡ።
የቱንም ያህል ግጭት እንዳይፈጠር በእኛ በኩል ያላሰለሰ ጥረት ብናደርግም ከአቶ ጀዋርና በፌስቡክ ላይ ያሰማራቸው የእርሱ ተናካሽ ውሾች (attack dogs) ሲያደርጉት ከነበረው ቅስቀሳ በግልጽ እንደምንረዳው እነርሱ ግጭቱን አበክረው ይፈልጉት ነበር። በተለይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት እንዲቀሰቀስ ፍላጎት እንዳላቸው በግልጽ በሚያሳይ መንገድ ቄሮዎች ኦሮሞ ባልሆኑት የአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚኖሩ የሌሎች ብሄሮች ላይ ጥቃት እንዲደርስ በግልጽ ቅስቀሳ አድርገዋል። የሚፈልጉትን ስላገኙም ጥፋተኝነት ሊሰማቸው አይችልም። ምናልባትም ኦስሎና ሜልበርን ተቀምጠው ቺርስ እያሉ ይሆናል። እነዚህን ወንጀለኞች ግን ህግ ፊት የማቆም ሃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
የእኔ ጥረት ግን በዚህ አላበቃም። ጥረቴ ባይሳካም ኦቢኤን የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችን አቅርቦ በማወያየት ውጥረቱን እንዲያረግብ የእስር ቤት ወዳጄ ከሆነው አቶ ታዬ ደንደአ ጋር ለማመቻቸት ጥረት አድርጌአለሁ። እነጀዋር ውጥረትንም ሆነ ግጭቱን ይፈልጉት ስለነበር ልናስቆም አልቻልንም። የግጭት ነጋዴዎች ትርፋቸውን ብቻ እንጂ የእናንተ ክቡር ህይወት መቀጠፍ ስላላሳሰባቸው መተኪያ የሌለውን ህይወታችሁን የተቀጠፋችሁ የአገሬ ልጆች ነፍሳችሁን ይማር! አቶ ለማ በእርግጥ ኦሮሚያን እየመሩ ከሆነ አጥፊዎችን በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጥሪዬን አቀርባለሁ!
Filed in: Amharic