>

የዘረኝነት አጭር ታሪክ (አሰፋ ሀይሉ)

የዘረኝነት አጭር ታሪክ
አሰፋ ሀይሉ
ይሄ የጆርጅ ኤም ፍሬድሪክሰን «ዘረኝነት – አጭር ታሪክ» መጽሐፍ በአሜሪካ ምድር እስከዛሬም ድረስ ስለዘረኝነት አንጠርጥረው ተንትነው ከተጻፉ መጻሕፍት በቀዳሚነት የሚጠቀስ አስገራሚ መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፉ ስለዘረኝነት አመጣጥ – ሺህዎች ዓመታትን ካስቆጠሩ ጥንታዊ እውነተኛ ታሪኮች በመነሣት – እንዴት በአሜሪካ ምድር – ቀለምን መሠረት ያደረገ ዘረኝነት (the color-coded racism) አቆጥቁጦ፣ ሥር ሰድዶ – እንዴት ለስንት ሺህ ለማሰብ የሚከብዱ – በሰው ልጅ አዕምሮ ተቀባይነት አግኝተው ይፈፀማሉ ተብለው ለማይገመቱ – እጅግ ዘግናኝ ዘረኝነት ያመጣቸው ጦሶች፣ ህጎች፣ ሰብዓዊ ጥፋቶች፣ ግፎች እና ጠባሳዎች – እያስተነተነ – የዘረኝነትን ገመና በገሃድ ፀሐይ አስጣጥቶ በዓይናችን በብረቱ ያሳየናል፡፡
ደራሲው የፕሪንስተን ፕሮፌሰር – ጆርጅ ፍሬድሪክሰን – ከዚህ የቆዳ ቀለምን ልዩነት መሠረቱ አድርጎ ከተቃኘው – እና በበርካታ የ19ኛውና የ20ኛው ክፍለዘመን የዘረ-መል አጥኚ ሣይንቲስቶች ጭምር በሐሰት – እና ለዘረኝነት ፖሊሲዎች ሣይንሣዊ ድጋፍ ለመስጠት በማለም – የተተነተኑ እና እስካሁንም ዘመናችን ድረስ ተቀባይነት አግኝተው – በዓለም ተፅዕኖ ስለፈጠሩ የዘረ-መልና የባዮሎጂያዊ የሰው ልጅ ዘር ትንተናዎችና ልዩነቶች – በሣይንሣዊ መንገድ እያስጣጣ – ያን የመሠለ ሣይንሣዊ ሸፍጣቸውንና ሐሳይ ቲዎሪዎቻቸውን – ጉድ! እስክንል ድረስ እያጋለጠ ያስረዳናል፡፡
በዚህ ብቻም አያበቃም ፍሬድሪክሰን – በቀለም-ልዩነት የተቃኘው ዘረኝነት – ጉልበቱ ሲጣምንባቸው ደግሞ – እነዚያው ሣይንቲስቶች – የነበረውን የዘረኝነት ፖሊሲ ለማስቀጠል የሚመቹ የተለያዩ – እጅግ ኢ-ሰብዓዊ ሣይንሳዊ ግኝቶችን አገኘን በማለት – ለናዚዎቹ እነ አዶልፍ ሂትለር – የቲዎሪና የሣይንሥ ድጋፍ በማበርከት – ዳግም እጅግ በጥላቻ የጨቀየና በጥፋቱ ታይቶ የማይታወቅ ቀለም-ወለድ ሣይሆን – ዘር-ወለድ፣ ሐይማኖት-ወለድ፣ ቋንቋ-ወለድ የሆነ – በዓይነቱ አዲስ የሆነ የፀረ-አይሁድ ዘረኝነት (the antisemitic racism) በመፍጠርና በህዝቦች ዘንድ በማስረፅ – እንዴት እነ ሒትለር፣ እና በህጋዊ መንገድ ያቋቋሟቸው ብሔራዊ ሀገራዊ ተቋሞቻቸውና ሰዎቻቸው፣ ዘረኝነት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችና ህጎቻቸው፣ እና እነዚያን ለማስፈፀም በምን ያህል ሀገራዊ መልክ ባለው አደረጃጀትና ርዕዮተ-ዓለም እየተደገፉ – 6 ሚሊየን ንፁሐን ትውልደ አይሁድ ከምድረገጽ ለማጥፋት እንደተቻላቸው በዝርዝር እየተነተነ ያቀርብልናል – ይህ ድንቅ የታሪክ ፕሮፌሰር – ጆርጅ ኤም ፍሬድሪክሰን፡፡
ፕሮፌሰሩ ከምንም በላይ የሚያስደምመው – እነዚያ ዘረኞች – እንዴት ብለው ያን የመሠለ የ20ኛው ክፍለዘመን ማህበራዊ እብደት – ዜጎቻቸው እና ያለም ሕዝብ እንዲቀበላወቸው – አሊያም በዝምታ እንዲመለከት – እንደቻሉ – ወይም እንዳስቻላቸው ነው፡፡ እና እርሱ – ያ ዳግም ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ያደረበትም ይመስላል፡፡ ከ50 ዓመት በፊት – ጥቂት 10 የማይሞሉ ሰዎች – ድፍን አውሮፓን እንዲያ ጨፍነው ሊያሞኙ ከቻሉ – ወደፊትስ – ያ እንደማይደገም ምን ማረጋገጫ አለን? ያለን ማረጋገጫ – እንደ እርሱ – ዕውቀት ብቻ ነው፡፡ ዘረኝነት ምን እንደሆነ ጠንቅቆ ማወቅ፡፡
ዘረኝነት ውሸት የወለደው – በጥቂት የእውነት ጠብታዎች የታገዘ – ቀንዱን የደበቀ ሠይጣን ነው፡፡ እና ያን ለማሳየት ፕሮፌሰር ፍሬድሪክሰን – ያን ሁሉ ናዚያዊ ተቋማዊ የዘረኝነት የውሸት ፋብሪካ – ከነምስጢራቱ እየተነተነ – እንካችሁ – እዩልኝ – ስሙልኝ- እና ፈጽሞ – በምንም ዓይነት መልኩን ቢቀያይር በናንተ ዘንድ – በጥጋችሁ ድርሽ እንዳይል – ማንነቱን፣ ምንነቱን፣ እና ስይጥንናውን – እዩ፣ ስሙ፣ አሽትቱ፣ አነፍንፉት- እና ገና ከሩቁ ነቅታችሁ – መከላከያችሁን አብጁ ይለናል፡፡
በነገራችን ላይ – በእኛም ሀገር – ከአንዳንድ ቅንጥብጣቢ እውነታዎች በመነሳት – ላለፉት 27 ዓመታት በትውልዳችን ላይ የተዘራው የዘረኝነት ዘረ-መል – አሁን ቀንድና ጥርስ አብቅሎ – ጥቂት በጥቂት እያለ – ሰዎችን ሰለባው ሲያደርግ – ዜጎችን ለሞትና ለስደት ሲዳርግ – እንዲያም ብሎ – ዕውቅናና ትንታኔ ተሰጥቶት – በአደባባይና በመንግሥታችን መሪዎችና ባለሥልጣናት – ከላይ እስከ ታች ድረስ ሌት ተቀን ሲቀነቀንና ሲሰበክ እየሰማን ነው፡፡ የኛ ዘረኝነት – ላለፉት ሶስት አሰርት ዓመታት – ለዘረኝነቱ – ርዕዮተ-ዓለማዊ መሠረት ማበጀት ብቻ ሣይሆን – ለዚህ አደገኛ ለሆነው የዘረኝነት ፖሊሲ – ተቋማዊ አደረጃጀቶችና መሠረቶች ተጥለውለታል፡፡
ላለፉት ዓመታትም እነዚህኑ የዘረኝነት አረንቋዎች – ከሕገ-መንግሥት ጀምሮ እስከ ተለያዩ ሕጎች – ዘረኝነት-ላይ ተመሥርተው ህጋዊ እውቅና ካገኙ የክልላዊ አስተዳደር ተቋማትና ህጎቻቸው እና ተቋሞቻቸው አንስቶ – የተለያዩ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው የዘረኝነት ፖሊሲዎች – ህጋዊ መሠረትና ሽፋን ተሰጥቶአቸው – ሲራመዱ፣ ሲራገቡ፣ እና እግር አውጥተው ለመቆምና ለመናከስ ሲውተረተሩ – ላለፉት ዓመታት በዓይናችን በብረቱ – በዚሁ በኢትዮጵያችን ምድር – ያየነው እውነታ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ – የዘረኝነት መቅሰፍት – በስተመጨረሻ በምን እንደሚደመደም – እስቲ – ከእነጂም ክራው የአሜሪካኖች ዘመን አንስቶ – እስከ ደቡብ አፍሪካዎቹ አፓርታይድ – ከናዚ ጀርመኒ የሴማውያን የዘር ፍጅት አንስቶ እስከ ሩሲያኖቹ ጥንታዊ ፖሮግሮሞች – ከሐይማኖታዊ ግንድ ከሚመዘዙ ዘረኝነቶች – እስከ ፀጉር ዞማነትና ከርዳዳነት – አፍንጫ ሰልካካነትና ድፍጥጥነት – እስከ ቅጥነትና የዓይን ቀለም – ከቋንቋ ልዩነት እስከ ቋንቋ ዘዬና ቅላፄ ልዩነቶች ድረስ – ዝርዝረ ቅንጭብጫቢዎች ላይ ተንጠላጥለው – እሥር ድረስ ዘልቀውና ወርደው – በሰው ልጆች ላይ የተረጩ አደገኛ የዘረኝነት መርዞች – በየዘመኑ ያስከተሏቸውን ዘግናኝ – እጅግ ዘግናኝ – አውሬያዊ ጥፋቶች – እጅግ አውሬያዊ የጭካኔ ተግባራት – እጅግ አሣፋሪ የግፍ ፖሊሲዎችና ሰብዓዊ ጠባሳዎች – እስካሁንም ያልተረሱ እና እንደአደገኛ ቫይረስ አመቺ ጊዜ ካገኙ ኢራፕት ሊያደርጉ ወደሚችሉ አደገኛ ኢቦላዊ አስተሳሰቦች እንዳደረሱን እና እንደዳረጉን – እያስተነተነ – በቀላል ቋንቋ – በ207 ገጾች ብቻ ቅልብጭ አድርጎ ያቀርብልናል፡፡ /በነገራችን ላይ ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ለፈለገ – ኢ-ሜይሉን – ኮመንት ቦክስ ላይ – ፔስት ያድርግልኝ – በ ፒዲኤፍ እልክለታለሁ!/
እስቲ – እንደ እነ ፕሮፌሰር ጆርጅ ኤም ፍሬድሪክሰን የመሣሠሉትን – ለሰው ልጅ በጎነትና የአዕምሮ ብልጽግና ታላቅ ሥራን አበርክተው ያለፉትን ምሁራንና ተመራማሪዎች ሥራዎች አንብበን – ራሳችንን እንፈትሽ! ምናልባትም – ከደረሰው ይልቅ – በእኛ ላይ ያንዣበበው – የባሰ ሆኖ ይታየን ይሆናል፡፡ እስቲ እንወቅ – እና ራሳችንን እንፈትሽ – እና ራሳችንን በራሳችን እናርም!!! አበቃሁ፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ የብዙሃን እናት – እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አሜን፡፡
Racism: A Short History, by George M. Fredrickson, 2002
Filed in: Amharic