..
በአሁን ወቅት እየታየ ያለው ለውጥ በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት የተገኘ ነው ሲሉ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ አዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ::
አቶ ዳዉድ እንዳሉት ግንባራቸው ከ26 ዓመታት በሗላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው መንግሥት ባደረገው ጥሪ በሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ ላይ ለመሳተፍና በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል::
በቀጣይ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድርግ ከመንግሥት: ከአባሎቻቸው: ከደጋፊዎችና ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል::
በረጅም ጊዜም በመላው ሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ሕዝቡም በሁሉም ደረጃ በምርጫ መሪዎቹን ለመምረጥ የሚያስችል ሥርዓት በመገንባት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል::
በሃገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በመስራት በኩልም ኦነግ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አቶ ዳዉድ ገልፀዋል::
የኦሮሞ ነጻነት ግምባር አመራሮች በመስቀል አደባባይ በርካታ ሺህ ህዝብ በተገኘበት ደማቅ የአቀባበል ስነስርአት ተደርጎላቸዋል።
• የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ በመስቀል አደባባይ ካደረጉት ንግግሮች የተወሰዱ ዋና ዋና ነጥቦች:-
• ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለ ምንም ቅድሚያ ሁኔታ አብረን እንሰራለን!!!
• የዶ/ር ዐቢይ መንግስትን አመሰግናለሁ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን አመሰግናለሁ፡፡
• አገራችን እኩልነት የሚሰፍንባትና የህዝብ ድምጽ የሚከበርባት አገር እንዲትሆን እንሰራለን፡፡
• ከመንግስት ጋር ያደረግነው ስምምነት እንዲሳካ የኦነግና የህዝባችን ፍላጎት ነው፡፡
• ከዚህ በኋላ ህዝቡ የመጣውን ለውጥ ያስጠብቃል ብለን ለህዝቡ አደራ እንላለን፡፡
• እውነትና፣ አንድነት ሁሌም ያሸንፋል፣ ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡
• ኦነግ በአገር ግንባታ ውስጥ የድርሻውን እንደምወጣ ማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
• ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለ ምንም ቅድሚያ ሁኔታ ጋር መስራት የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለን እናምናለን፡፡
• በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊና ዴሞክራሲያ መብቶች እንዲከበሩ ከመንግስት ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡