>

ኦሮሞ - አማራ - አዲስ አበቤው ስማ! (ዘውድአለም ታደሠ)

ኦሮሞ – አማራ – አዲስ አበቤው ስማ!
ዘውድአለም ታደሠ
እናት ሐገራቸው ወደአመድነት ስትቀየር ለማየት የቋመጡ፣ የታላላቆቹ ሁለት ብሔሮች ውህደት እንቅልፍ የነሳቸው በፕሮፌሰር መስፍን አጠራር ሐገር ሻጭ ባንዳዎች እኛ በስስትና በስጋት የምናያትን ሐገር በአሉባልታና በሴራ ለማፈራረስ አሁንም እየሰሩ ነው!!
ሐገር ውስጥ አንድ ችግር ሲፈጠር ሐገሪቱ የነሱ እንዳልሆነች ሁሉ በደስታ ሲፍነከነኩ ታዝበናል። የአብዲ ኢሌ ዱርዬዎች በሶማሊ ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉና ህፃናቶች ሲደፍሩ እነሱ ግን “አብዲ እንዳይነካብን፣ ጀግናው የሶማሊ ወታደር የኢትዮጵያን ሰራዊት አሸነፈ” ብለው በአደባባይ ሲናገሩ ነበር። አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጣ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ እነሱ በደስታ ባህር ሰጥመው ነው ሚመለከቱት። ደም ሲፈስ ልባቸው በሃሴት ይሞላል። ሰው ከሰው ጋር፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር ሲባላ ህልውናቸው በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ተደላድሎ የተቀመጠ ይመስላቸዋል። ለዚህ ነው ትናንት በአዲስ አበባ የተፈጠረችውን ችግር በደስታ ተውጠው እያጋነኑና የኦሮሞና የአዲስ አበባን ልጅ እየመሰሉ የጥላቻ ሃሳባቸውን ሲያስፋፉ ያየናቸው!!!
መቼም በየትኛውም ዘመን ሐገር ሻጭ ባንዳ የሰው ጉድፍ ከየትውልዱ አይታጣም። ትናንት ከጣሊያን ጋር ሆነው ወገኖቻቸውን የወጉ፣ ለጠላት መንገድ መርተው ወገናቸውን ለሞት አሳልፈው የሰጡ፣ ባንዳና ሹምባሽ ሆነው በሺህዎች ሬሳ ላይ ኑሯቸውን የመሰረቱ፣ የሰው አረሞች ልጆቻቸው ዛሬም ለኢትዮጵያ አንድነት እንቅፋት ሆነው እኛ ሲጨንቀን ሲስቁ እኛ ስንስቅ ሲያለቅሱ፣ ለኛ ሲነጋ እየመሸባቸው፣ ለኛ ዳመና ሲሆን ለነሱ ፀሃይ እየወጣላቸው እስካሁን አሉ!!
ስማኝ ኦሮሞው፣ ስማኝ አማራው፣ ስማኝ አዲስ አበቤው … ለጠላትህ እድል ፈንታ አትስጥ! ስትስማማ ወደር አልባ ጉልበተኛ ስትለያይ የማንም ጭራሮ የሚያንከባልልህ ልፍስፍስ ትሆናለህ! ትናንትህን አትርሳ! ለሃያሰባት አመት የተገረፍከው ከጀርባህ ላይ ያለው ሰምበር ገና አልደረቀም! ገና ለዘመናት የተሰራብህ ወንጀል ቁስሉ አልሻረም! ዛሬ ከምኔው አልፎልህ ለባንዲራ ሽሚያና ለእርስበርስ ጠብ በቃህ? ገና የሞትክና የቆሰልክላትን ዲሞክሪያሳዊት ሐገር መች መሰረትክ? ዛሬ ያገኘኸውን ድል በተራ እንቶፈንቶ ከእጅህ ልትጥለው ፈለግክ? በቃ እቺ ነበረች አላማህ? በቃ ለዘመናት ሲቀልዱብህ የኖሩ ሰዎች ዳግም እንዲቀልዱብህ ፈቀድክ?
አንድ ሃቅ አለ! እውነት ነው ብዙ ማያስማሙን ጉዳዮች አሉ፣ ብዙ ሚያጨቃጭቁን ሃሳቦች አሉ። ወዘተ ወዘተ … ነገር ግን በየትኛውም ሚዛን ቢለካ ለኛ ኢትዮጵያውያን ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ የተሻለ ቀን መጥቷል። የኛ ፀሃይ የማይስማማው ሌት ጠብቆ ከጎሬው ለሚወጣ ጅብ ብቻ ነው! በምንም ተአምር ወደቀድሞው ዘረኛ፣ ሌባ፣ ነፍሰገዳይ፣ ስርአት አንመለስም! (ይሄን ቢመራችሁም ዋጡት)
አዎ እዙያም እዚም ተራ ግጭት ሊኖር ይችላል። ይሄ የለውጡ አንዱ ምልክት እንጂ ክፉ አርግማን አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ከፊታችን ብዙ ተስፋ አለ። ገና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ይጠብቃል፣ ገና ነፃ መድረክ ተዘጋጅቶ ለዘመናት ባናቆሩን ታሪኮቻችን ላይ ውይይት አርገን ልዩነታችንን እናጠባለን፣ ገና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አለብን። ገና በነፃነት ወጥተን የመሰለንን መርጠን እንገባለን። ያኔ የኢህአዴግ የከፋፍለህ ግዛ ትርክት ተቆፍሮ ይቀበራል። ኢትዮጵያም ትናንት ፀንታ እንደቆመችው ሁሉ ነገም በፅናት ሊበትናት የሞከረን ሁሉ እየበተነች ትኖራለች! የአንድነት ጠላቶችም ልክ እንደአባቶቻቸው ለዘልአለም ስማቸው በቅሌት መዝገብ ላይ ይሰፍራል!
ስለዚህ አማራውም ሆንክ ኦሮሞው፣ አዲስ አበቤውም ሆንክ ደቡቡ ፣ ከተራ ጭንቀትና ፍርሃት ወጥተህ እጅህ የገባውን እድል ጠብቀህ ያዝ! የማይረባ ክርክርና ሙግትህን ትተህ ሁሉ በእኩልነት የሚኖርባትን ሐገር ሰርተህ ለነዚህ የእፉኝት ልጆች አስተምር! በጠላት ሴራ ተተብትበህ በወንድምህ ላይ ሰይፍ አትምዘዝ! ታገስ፣ ተረጋጋ፣ አስተውል፣ ጠላቶችህ ይስቁብህ ዘንድ እድል አትስጥ!
ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኖራለች! ምኞት አይደለም ታሪክ ያረጋገጠው ሃቅ ነው!
Filed in: Amharic