>

የኢትዮጵያችን ፖለቲካ ቄሰ-ገበዟን  አገኘች!!!! (መስከረም አበራ)

የኢትዮጵያችን ፖለቲካ ቄሰ-ገበዟን  አገኘች!!!!
መስከረም አበራ
በሃገራችን ፖለቲካዊ ታሪክ ከባድ ሚዛን ፖለቲከኞችን በዘመናቸው ከኖረው ህዝብ ይልቅ ቢወድቅ ቢነሳ ሊያገኛቸው የማይችለው የኋለኛው ትውልድ ይበልጥ ጥቅማቸውን ያውቃል፡፡ እነ አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ ራስ ቢተወደድ መኮንን እንዳልካቸው፣እነ አቶ ይልማ ደሬሳ፣አቶ ከተማ ይፍሩ ፣ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሌ፣ እነ ገርማሜ ነዋይ፣ጌታቸው ማሩ፣ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ወዘተ ሁሉ በዘመናቸው ነብይ በሃገሩ(ነው በዘመኑ?) አይከበርም አይነት ነገር ያጋጠማቸው፤ እኛ የኋለኞቹ ደግሞ አጥብቀን የምንናፍቃቸው ፖለቲከኞች ይመስሉኛል፡፡
ያለፉትን የምንናፍቅ፣የሞተን ብቻ ማመስገን የሚሻለን እኛም በጎ አይናችንን ከፍተን ማየት ከቻልን ፖለቲካችንን መላ የሚል ንድፈ-ሃሳብ ከተግባር አጣጥሞ የቀመረ ከበድ ያለ ፖለቲከኛ  አልጠፋም፡፡
ፕ/ሮ ብርሃኑ እንዲህ ካሉት አንዱ ይመስለኛል፡፡ እሱ ሲያወራ የሚሰለች አለ ቢሉኝ ይገርመኛል፡፡ በንባብ ንግግር ሲያደርግ ሃሳቤን ሰብስቤ የማዳምጠው ብቸኛው ሰው እሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሰው (አስተማሪም ጭምር) ማንበብ ሲጀምር የኔ ቀልብ ቤቱ ውስጥ ባሉ መስኮቶች ሁሉ ወጥቶ ያልቅብኛል፤ከዛ (የሚቻል ከሆነ) ራሴም በበር ወጣ ደስ ይለኛል፡፡ ተማሪዎቼም እንደኔው ይሰለቻሉ ብየ ስለማስብ ሳስተምር አንብቤ አላውቅም፤ወረቀት ባላይም ደስ ይለኛል፡፡
ፕ/ሮ ብርሃኑ እያነበበ ሲያወራ ግን አይኔን ከእሱ ላይ ነቅየ መሬት መሬት እያየሁ በልቦናየ የሃሳቡን ጎርፍ ለመከተል እሮጣለሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ ያላዳመጥኩት ንግግሩ ትዝ አይለኝም፡፡የሃሳቡ ፍሰት ይገርመኛል፤በሚያፈሰው ሃሳብ ውስጥ ግር ያለኝን ነገር በሚቀጥለው ዓረፍተ-ነገር ያብራራዋል፡፡አድማጭ ሊያነሳ የሚችለውን ጥያቄ ያውቃል፤ዝግት አድርጎ መልሶ ያልፋል፡፡ሁሉ ጊዜ እንዲህ ነው! የበቀደሙ ደግሞ ልዩ ነበር፡፡ የተናገረው ነገር ቢያፍታቱት አንድ ዘናጭ የፓርቲ ፕሮግራም ይወጣዋል፡፡
የፖለቲካ መሪ እንዲህ ወንበሩ ሲጠበው ደስ ይላል፡፡እድሜ ለወያኔ ወንበር የሰፋው ካድሬ ሲዘውረን በመኖሩ እንዲህ ያለው ብቃት ብርቅ ነው፡፡ እውቀት እወዳለሁ፤አዋቂ ማክበርም ግድ ነው፡፡ ማዕረግ ያለው ሁሉ አዋቂ ነው ብየ አላስብም፡፡ እውቀት ከማእረግ ጋር ሁል ጊዜ ላይገጥም ይችላል፡፡ እንደ ፕ/ሮ ብርሃኑ ልክክ ብሎ ሲታይ አለማመን ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ሰውየው ሰው ነውና ፍፅምና አይኖረውም ይሆናል፡፡ ግን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዝ ነው፡፡ ቢያንስ እኔ የሚሰማኝ እንዲህ ነው፡፡
“የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ግቢ እና የቻልሽውን አበርክቺ” የሚል ግብዣ አልፎ አልፎ ሲቀርብልኝ የምሸሸው ቦታውን የምገምትበት ሚዛኔ እንዲህ  ገዘፍ ባሉት ሰዎች ስለሆነ ነው፡፡ እነሱን በሰማሁ ቁጥር ገና ብዙ እንደሚቀረኝ አስባለሁ፡፡የንባባቸው ስፋት ሁልቀን ሲናገሩ ያስታውቃል፡፡ከታላቆች በሰማሁ ቁጥር የራሴን ገናነት አገናዝባለሁ፡፡ ብዙ ብዙ ይቀረናል ….. !!!!!
 በተለይ መለኪያችን ትልቅ ሰው ከሆነ  የሃገር እጣፋንታ የሚወስነውን ማዕከላዊ መንግስት ስልጣን  የፓርቲ አመራርነትን ልጓም መጨበጥ ራሱ ከብዶ መታየት አለበት – ዘለው ቢቀመጡበት ወንበሩም ይሰፋል ሃገርም ትጎዳለች፡፡ እናም አዋቂ ብቻ ወደፊት ይሁን፤ የኔ ቢጤው ቁጭ ብሎ ይማር ……..https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1828258833909004&id=100001747156685
Filed in: Amharic