>

ዶ/ር ዓብይ እንደ ክርስቶስ ሳምራ! (አስራት አብርሃ)

ዶ/ር ዓብይ እንደ ክርስቶስ ሳምራ!

አስራት አብርሃ

ዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የሆኑ ነገሮች በቀና ልቦና ከተመለከትናቸው፣ በእውኑ ይህ ሁሉ በሰው ልጅ አቅም የሚቻል ነውን? ብለን እንድንጠይቅ ነው የሚያደርገን። በትናንትና የአዲሱ ዘመን መጀመሪያ ዕለት በሁለቱም አገራት በተነሳ ጦርነት ምክንያት ለ20 ዓመታት ያህል ተለያይተው የነበሩት በሁለቱም ወገን ያሉት ትግርኛ ተናጋሪ ብተሰቦች፣ አፋሮች፣ የኢሮቦች ወይም ሳሆዎች፣ የኩናማዎች ተወላጆች ቤተሰብ ለቤተሰብ ተገናኝተዋል፣ተቀላቅለዋል። ቅልቀሉ ደግሞ ዶ/ር ዓብይ እና አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በአካል ተገኝተው አብስሮውታል፤ በእዉነቱ ይህ ከትውልዱ ወደ ትውልድ በበጎ መልኩ ሊነገር የሚችል ድንቅ ነገር ነው። ይህ ቅድስት ክርስቶስ ሳምራ እንኩዋን አሰባ ያልተሳካላት ነገር ነው። ክርስቶስ ሳምራ ዓለሙን ሁሉ በእግዚሄርና በዲያብሎስ ጠብ ምክንያት መከራና ጥፋት ከሚሆን ለምን ሁለቱንም አላስታርቃቸውም ብላ በመጀመሪያ ወደ እግዚሄሩ ሄደች፣ እሱ እሺ አይልም እንጂ እኔማ እታረቃለሁ ብሎ ፍቃደኝነቱን ገለፀላት፤ ከዚያ ወደ ዲያብሎስ ሄደች የእኔ እህት እኔ በፀብ በውስጥ መሆኑ ጠቅሞኛልና አልታረቅም ብሎ መለሳት። ዶ/ር አብይ ግን ኢሳይያስ አፈወርቂን የመሰለ ትልቅ ዲያብሎስ በፍቅር ማርከው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አስታርቆውታል፤ አቶ ኢሳይያስ ከዲያብሎስ ለየት የሚያደርጋቸው ለእርቅ ፍቃደኛ መሆናቸው ነው፤ እንግዲህ ዶ/ር አብይ በጀመሩት የይቅርታ መንገድ ወደ መቀሌ ሸሽተው እዚያ ያለውን ህዝብ እያሸበሩ ያሉትን መለስተኛ ዲያብለሶችም በይቅርታና በፍቅር ማርከው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዲቀላቅሉዋቸውና የለውጡን አጋዥ እንዲሆኑ እንዲያደርጉዋቸው ምኞታችን ነው።


በበኩሌ ይህ ሲሆን በዓይኔ ከተመለከቱ በኋላ የተጀመረው ለውጥ ያልታሰበ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚል የነበረኝ ጥርጣሬና ስጋት ሙሉ ለሙሉ ቀርፎልኛል። ኢትዮጵያን ታግለው ለውጥ ያመጣሉ እንጂ የተገኘውን ለውጥ በበጎነቱ የማስቀጠል ችግር አለባቸው የሚለው ታሪኩም በመደመር ፍልስፍና እየተሻገርነው ይመስለኛል። እንደሚታወቀው 1966ቱ አብዮት ተከተሎ ደርግ በንጉሱ ዘመን የነበሩትን ጥሩ ነገሮች ሁሉ አጥፎቶ በሁሉም ነገር እንዳዲስ ነው ከዜሮ እንዲጀመር ያደረገው፣ ኢህአዴግም እንደዚሁ ደርግን አሸንፎ ስንጣን ሲይዝ ከዜሮ ነው የጀመረው፣ ዶ/ር አብይ ግን ባለፉት ዓመታት የነበሩትን መጥፎ ነገሮች በማስወገዱ በጎ የሆነውን ደግሞ አዳዲስ በጎ የሆኑ ነገሮች በመጨመር ነው ማስቀጠል የፈለጉ የሚመስለው። ለእኔ መደመር ማለት ይህ ነው፤ በበጎ ነገር ላይ መደመር ደግሞ መልካም ነው። 

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊ ሌላው ኢትዮጵያዊ የማይገድልበት፣ ዜጎች ብሄር ወይም በሃይማኖት ወይም በሌላ ምክንያት የማይፈናቀሉበት፣ ህግና ስርዓት የሚከበርበት፣ ሰላምና ፍቅር፣ እድገትና ብልፅግና የሚታይበት ዓመት ይሁንልን!

እናመሰግኖታለን!

Filed in: Amharic