>

 .... ከምር ደስ ይላል!!! (ዘመድኩን በቀለ)

እምጷጷጷ ! እምጷጷጷ ! ከምር ደስ ይላል!!!
ዘመድኩን በቀለ
* የጥል ግድግዳው የፈረሰላችሁ እንኳን ደስስ አላችሁ። እናንተም እንዲህ ደስ እንዳላችሁ ሁሉ ሌሎችም ደስ ይላቸው ዘንድ በሌሎች ልብ ውስጥ የገነባችሁትን የጥል ግድግዳዎችን ዛሬውኑ አፍርሱ። 
*አድዋ በእምዬ ምኒልክ፣ 
* የአፍሪካ አንድነት በጃንሆይ፣ 
* የካራማራ ድል በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራርና በኢትዮጵያውያን ሁሉ ተሳትፎ ታሪካዊ ክስተት  የተመዘገበባቸው የኢትዮጵያ እውነቶች ናቸው። 
* እናም የዛሬው ታሪካዊ ክስተትም በአብያችን ስም ተመዝግቧል። አከተመ።
~ የሟቹ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠሚ የአቶ መለስ ዜናዊ አመራርም ለ20 ዓመታት የአንድ ቤተሰብ ሁለት አካላትን ለያይቶ ለመከራ ዳረገ። ” የአይናቸው ቀለም ያላማሩ ኤርትራውያንም ከኢትዮጵያም ተባረሩ “። ማዶ ለማዶ አባትና ልጅ፣ ወንድምና እህት በዝሆኖች ጠብ ምክንያት ተለያዩ። በዚህ ዓይነት መንገድ 20 የሰቆቃ ዘመን አሳለፉ። ይሄም የትናንት ታሪክ ነበር። ታሪክም መዝግቦ አስቀምጦታል።
~ ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን፣ ሌላ ዘመን፣ ሌላም ታሪክ የተጻፈበት ቀን መጣ። ወዳጄ ይሄን ከማድነቅ በቀር ምንም ማድረግ አይቻልም። የዛሬው ዕለት ለአቢቹ በወፍራም የወርቅ ቀለም ተጽፎ ከትውልድ ትውልድ የሚዘከር ታሪካዊ ክስተት በስሙ እንዲጻፍም ግድ የሆነበት ዕለት ነው። አቢቹአችን ታሪክ ሠራ አይገልፀውም። የኤርትራንና የኢትዮጵያን የጥል ግድግዳ ደርምሶ፣ የተቀበረ ፈንጂ አስጸድቶ የትግራይና የኤርትራን ወንድማማች ህዝቦች አገናኛቸው። አዋሐዳቸው፣ አሳሳማቸው፣ አስተቃቀፋቸው፣ በፍቅርና በናፍቆት አላቀሳቸው። እናም ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። በአብቹ ላይም አድሮ ይኽን ታላቅ ሥራን ለሠራ ለሠራዊት ጌታ ክብር ምስጋና ይግባው።
 እናቶች ናቸው። ምን ያህል እንደተነፋፈቁ ተመልከቱልኝማ። በመሳም እንኳ ናፍቆት እንደማይወጣ ያስታውቅባቸዋል። ቢውጧቸውም የሚረኩ አይመስሉም። እናም ለጠሚዶኮ ዐብይ ክብር ይገባዋል። አከተመ።
እህትማማቾች ናቸው አሉ። የአንድ እናትና የአንድ አባት ልጆች። ዝሆኖቹ ሲጣሉ አንዷ ራሷን ኤርትራዊ ሆና አንዷም ኢትዮጵያዊ እንደሆነች ቀሩ። ዘመን ዘመንን ተክቶ ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ ሀገራቸውን ለማገልገል ወደ ውትድርናው ዓለም ገቡ። እናም አንዷ የኤርትራ፣ አንዷም የኢትዮጵያ ወታደር ሆኑ።
~ በቀደመውም ጊዜ በዘመነ መለስ ወኢሳይያስ ጊዜም እንዲሁ ሆኗል ይባላል። ወንድማማቾች አንዱ ከዚህ አንዱ ከዚያ ሆነው ተዋግተው ወንድም ወንድሙን ገድሏል። አሁንም ይሄ የአቢቹ ዘመን ባይመጣ ኖሮና ጦርነት አይቀሬ ሆኖ ቢጀመር እነዚህ የአንድ እናት ልጆች መጠፋፋት ዕጣ ፈንታቸው ነበር። እግዚአብሔር ግን ታሪክ ቀየረ። ዘመን አመጣ። ይኸው ሁለቱ እህትማማቾች በሁለት ሀገር ዩኒፎርም ያለጦርነት በፍቅር አስተቃቀፈ።
እናም ይሄ ታሪክ ለትውልድ ሲተላለፍ፣ ባለታሪኩም ስሙ ለትውልድ ሲዘከር ልክ እንደ ዓድዋው ያለምንም ተቀናቃኝ ኢህአዴግ፣ ቅብጥርስዬ ምናምን ሳይባል የታሪኩ መሪና ባለቤት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ኮሎኔር ዶክተር ዐብይ አህመድ ብቻና ብቻ ነው የሚሆኑት።
ኢሳይያስ አፈውርቂ ሳይቀር ማመስገን ያለበቻው አቢቹን ነው። ዶር ደብረ ጽዮን ያለ አቢቹ ብቻውን መቼም ቢሆን የኢሳይያስን እጅ የመጨበጥ ዕድልም አያገኝም ነበር። ኤርትራም ድህነቷ በወታደሮቿ ተክለ ሰውነት ተጋልጧል። ጥቂት ዓመታት ያለ ጦርነት ብትቆይ ኤርትራ በቁሟ ትፈራርስ እንደነበር በገሃድ የሚታይ ሀቅ ነው። ለኤርትራም፣ ልትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለሁለቱ በዝሆኖች ፀብ ምክንያት ለተጎዱ ሳሮች ፈጣሪ ዐቢይን አስነስቶ ትንሣኤውን ዘርቶባቸዋል። እናም አቢቹ ሆይ ገለቶሚ።
ምክር ቢጤ ለትግራዋዮች፦ 
ከፀብ፣ ከክርክር፣ ከጦርነት ምንም ጥቅም እንደሌለ፣ እንደማይገኝም የዛሬው ቀን ክስተት ምስክር ነው። እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። ከዛሬው ቀን በፊት በግላችሁ የኤርትራን ድንበር ተሻግራችሁ ዕርቅ ለመፍጠር ብትሞክሩም የኤርትራ መንግሥት በፍጹም ይሄ የሚሆነው በሕግና በሕግ ብቻ ነው ብሎ ኤርትራውያን ድንበር እንዳይሻገሩ አድርጎ ሊያስተምራችሁ ሞክሯል።
 መንግሥት ከመንግሥት ጋር እንጂ ክልል ከመንግሥት ጋር መገናኘት እፉ ነው አይቻልምም ብሎ አሳይቷችኋል። እናም ዛሬ ግንኙነቱ መንግሥት ከመንግሥት ጋር ሲሆን ይኸው የሆነውን ሁሉ አይታችኋል። እናም ሕግ አክብሩ። በስሜትና በትዕቢት አትመላለሱ። በባዶ ሜዳም አትፎክሩ። ፍቅር ያሸንፋል። ሕግ ማክበርም ያስከብራል።
ሁለተኛው ደግሞ የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ ለመሆን አትሞክሩ። መጀመሪያ ከአፋሩም ከወንድማችሁ ከዐማራውም ታረቁ። የቀማችሁት የወሰዳችሁት ካለም መልሱ። ያስቀየማችሁት ፣ ያስኮረፋችሁትም ካለ በጨዋ ደንብ ይቅርታ ጠይቁ። ልጆቻችሁን ተቆጡ፣ ገስፁ፣ ምከሩም። ከሁሉ ተጣልታችሁ አትዘልቁትምና ለምንድነው ከሁሉ ጋር የምታጣሉን የምታናቁሩን ብላችሁ ገስጹ። አቢቹ ሆይ ይሄንንም ሞክር ስምተህ ከዐማራም፣ ከአፋሩም፣ ከሌሎቹም አስታርቃቸው።
ሦስተኛ የብሽሽቅ ቦለጢቃችሁን በአስቸኳይ አቁሙ። ልክ በኢኮኖሚ ጣራ እንደነካ ምእራባዊ ሀገር አትጎርሩ። ጤፍ ከጎጃም፣ እንጨትና ስንዴ ከጎንደር፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከወሎ እየተጠቀመ እንደሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁኑ እንጂ በባዶ ሜዳ አታቅራሩ። ትግራይ ያለዐማራ፣ ያለኦሮሞ፣ ያለ ኢትዮጵያም ዜሮ ናት። በቃ ዜሮ ናት አልኳችሁ። ይኽን እውነታ ቢመራችሁም ዋጡት። ደግሞም ከኤርትራ ጋር ታረቃችሁ ማለት በኤርትራ እንደፈለጋችሁ ትዘላላችሁ ማለት አይደለም። በዚያ ሕግና ሥርዓት የሚሉት ነገር አለ። እናም ሕግ ይከበር። በባዶ ሜዳ አንድን ወንድም ህዝብ እየሰደባችሁ እኛ ካልተከበርን ሞተን እንገኛለን ማለት ፈጽሞ አይቻልም። ያዋረደ ይዋረዳል። ያከበረ ይከበራል። ሁሉም እንደየሥራው የእጁን ያገኛል። እናም የሰላምን ጣዕም አውቃችኋልና፣ አይታችኋልና፣ ዛሬም ጣዕሟን ቀምሳችኋልና ይሄን ጣዕም ሌሎችም ይቀምሱት ዘንድ ጣሩ፣ ልፉ፣ ሞክሩም። ይኸው ነው።
★ በመጨረሽታም፦ የዘመናት የጥል ግድግዳ ጋርዶአችሁ፣ ፈንጂ ተቀብሮ፣ መትረየስ ተደቅኖ እንዳትገናኙ በመካከላችሁ የባቢሎን ግንብ የተተከለባችሁና በናፍቆት ስትሰቃዩ ከርማችሁ ዛሬ ያ ግንብ ፈርሶላችሁ የተገናኛችሁ ወገኖቼ ከምር እንኳን ደስ ያላችሁ። አቢቹ ሆይ አንተም ተባረክ።
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic