>

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም  አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው የወረዱት 44ኛ ዓመት መታሰቢያ

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም  አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው የወረዱት 44ኛ ዓመት መታሰቢያ
ልኡል አምደጽዮን ሰርጸድንግል
ንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው የወረዱት ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት ነበር።
ከዓለም ስመጥር ነገሥታት መካከል አንዱ የነበሩት፣ የሰለሞናዊ ስርዎ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሥ፣ እግራቸው በረገጠበት ምድር ሁሉ የነበረው ሕዝብ የሚሰግድላቸው፣ አንበሳ አጉራሹ … ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የባለቤታቸው የእቴጌ መነን አስፋው፣ የልጆቻቸውና የቅርብ ሰዎቻቸው ሞት፣ የመንግሥታቸው ሹማምንት ንቅዘት፣ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተደማምረው የአስተዳደራቸውን ምሰሶ አናጉት፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ አባላት 13 ሆነው ወደ ቤተ-መንግሥት ሄዱና ጃንሆይ የአገዛዝ ዘመናቸው ማብቃቱን አረዷቸው፡፡ የደርግ አባላት ቤተ-መንግሥት ደርሰው ንጉሱን አስጠሯቸው፡፡ ንጉሱም በዝግታ ከፎቅ ላይ  ወርደው በዙፋናቸው ላይ ሲቀመጡ የደርግ አባላት ደነገጡ፡፡
ሻምበል ደበላ ዲንሳ ደርግ የወሰነውን የውሳኔ ሃሳብ አነበቡ … ‹‹ … ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል በዛሬው ዕለት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ወርደዋል፤ ለደህንነትዎ ሲባልም አስተባባሪው ኮሚቴ ወዳዘጋጀልዎ ቦታ እንዲሄዱ ተወስኗል …›› የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ አነበቡ፡፡ ሻምበል ደበላ ውሳኔውን አንበበው ሲጨርሱ ንባባቸውን ሲጀምሩ የሰጡትን ወታደራዊ ሰላምታ ደገሙ፡፡
ንጉሱም ዝም ብለው ቆዩና መናገር ጀመሩ፡፡ ‹‹ያነበባችሁትን ሰምተናል፤ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም፡፡ ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ላገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት … የኢትዮጵያን ታሪክ ጠብቃችሁ ማልማት ከቻላችሁ የእኛ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃል፤ ካልቻላችሁ የእናንተ ታሪክ ያበቃና የእኛ ይቀጥላል፤ አገራችንንና ሕዝባችንን በምንችለው አገልግለናል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እድል የእኛን መወገድ የሚጠይቅ ከሆነ ስራችንን አቁመን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ‹አሁን ተራው የእኛ ነው› ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ›› በማለት ተናገሩ፡፡
… ከዚያም ንጉሱ ውብ በሆነችው ሮልስ ሮይስ መኪናቸው ሳይሆን ባረጀች ሰማያዊ ቮልስ ዋገን መኪና ተጭነው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ተወሰዱ፡፡
Filed in: Amharic