>

በምክር ሽፋን ውስጠ ወይራ (ከይኄይስ እውነቱ)

በምክር ሽፋን ውስጠ ወይራ

ከይኄይስ እውነቱ

ለዚህ የግል አስተያየት መነሻ የሆነኝ ‹‹ዳያስፖራውና የዜግነት ጥያቄ›› በሚል አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ የሚባሉ በውጭ ኗሪ ኢትዮጵያዊ ያቀረቡት ጽሑፍ/አስተያየት ነው፡፡

የጽሑፉን ርእስ እንዳየሁ ግምቴ የነበረው ዶ/ር ዐቢይ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን በጎበኙበት ጊዜ ኢትዮጵያውያኑ የጣምራ ዜግነት ጥያቄን መንግሥታቸው እንዲያስብበት ያቀረቡትን ጥያቄ መሠረት ያደረገ መስሎኝ ነበር፡፡ ግምቴ በእጅጉ የተሳሳተ ነበር፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን በአገዛዞች ታፍነን ስለኖርን (የመናገርና የመጻፍ ነፃነታችን ለዘመናት ተገድቦ በመዝለቁ) ንግግራችንም ሆነ ጽሑፋችን፣ እንጉርጉሮአችንም ሆነ ሙሿችን በአመዛኙ ሰምና ወርቅ ለበስ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ብዙውን ጊዜ ንግግራችንም ሆነ ጽሑፋችን ውስጠ ወይራ አያጣውም፡፡ በዚሁ ችግር ላይ እግዚአብሔርን አለመፍራት ወይም ቅንነት አለመኖር ሲታከልበት አንባቢ ጸጉር ስንጠቃ ወደሚመስል÷ ቃሉን ብቻ ሳይሆን የንግግሩንና የጽሑፉን መንፈስ ፍለጋ መባዘኑ አይቀሬ ነው፡፡ ይኸው ልማድ መነሻ ሆኖ አንዳንዱም ሆን ብሎ ባቋሙ ስለማይተማመን ወይም ላለማሳወቅ እንዲሁም በሌሎች ዘንድ ቅን አሳቢ መስሎ ለመታየት ነቀፋውን በውስጠ ወይራ ለመሸፋፈን ሲሞክር ይስተዋላል፡፡

በወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት›ም ሆነ የዜግነት ሕጉን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለሚገኝበትም ሆነ ስለሚታጣበት ሕጋዊ ምክንያቶች ጸሐፊው ያገኙትና በጽሑፋቸው ያካተቱት መረጃ ችግር ስለሌለበት እኔም በዚህ ረገድ የተለየ አስተያየት የለኝም፡፡ በሌላ በኩል ተገፍተውም ይሁን በፈቃዳቸው ከአገር የወጡ ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸውን ለውጠው የባዕድ አገር ዜግነትን መያዝ በሚመለከት የግል ምርጫና ፍላጎት በመሆኑ ባከብርም፤ በዚህ ረገድ ጽኑ የሆነ የግል አመለካከት አለኝ፡፡ ለእኔ ነፍስን እንደመነጠቅ፣ ዕርቃንን እንደመቅረት አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ የጣምረ ዜግነት መያዝ ከተቻለ ምናልባት እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ያለዝበው እንደሆነ አላውቅም፡፡ የተውሶ ዜግነት አርቲፊሻል ነው፤ ኢትዮጵያዊነቴን ማንም አይነጥቀኝም የሚል ክርክር የሚያነሱ ወገኖች እንዳሉ አውቃለኹ፡፡ ራስን ማታለል ካልሆነ በስተቀር ባዕድ በሆኑበት አገር ዜግነትን መቀበል የራሱ የአፈጻጸም ሥርዓት (ለምሳሌ ቃለ መሐላ የመፈጸም) እና በዓል አለው፡፡ ያለፋችሁበት ታውቁታላችሁ፡፡ በሕግ አግባብ ስናየው ግን ሙሉ ክብርና ጥቅም ብቻ ሳይሆን ግዴታና ኃላፊነትን እንደሚያስከትል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ዜግነት ለሰጠው መንግሥትና ለሰንደቅ ዓላማው ታማኝ ለመሆን ቃል የመግባት ግዴታ (Pledge of Allegiance)፡፡ በትውልድም (birth) ሆነ በሕግ የሚገኝ ዜግነት (naturalization) በሕጋዊ ውጤት ረገድ ልዩነት የላቸውምና፡፡ አሜሪካ ውስጥ  በሕግ ዜግነትን ያገኙ አሜሪካውያን በሕግ የተቀመጡ መሥፈርቶችን እስካሟሉ ድረስ የአገሩን የመጨረሻ የሥልጣን መንበር – ፕሬዚዳንት – የሚሆኑበትም ዕድል አለ፡፡   

ዜግነት በአንድ አገር የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ አባል በመሆን ለሚደረግ የፖለቲካ ተሳትፎ ወሳኝ አቋም (status) ነው፡፡ ዜግነት የአገር ባለቤትነት መገለጫም ነው፡፡

አስተያየት አቅራቢው ስለ ጽሑፋቸው ዓላማ ሲገልጡ፤

‹‹ዓላማዬ እነዚህ በገፍ በመመለስ ላይ ያሉት የፖሊቲካ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው የጉዲፈቻ አገሮቻቸው ነቅለው ከወጡ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በተለይም የዜግነታቸውን ጉዳይ አስመልክቶ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መሰናክል በውል የተረዱት ስላልመሰለኝ፣ የሚወስዱት ውሳኔ ሁሉ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው። ››

በማለት ወደ አገር ቤት የገቡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ግለሰቦች (activists) ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ በሕግ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ያመለከቱበት አግባብ ስህተት የለውም፡፡ ችግሩ ወደ አገር ቤት የገቡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ‹አክቲቪስቶች› በሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ስለመቀየራቸው አልገለጹልንም፡፡ ‹እንተዋወቃለን› በሚል አድበስብሰው ለማለፍ የመረጡ ይመስላል፡፡ የጸሐፊው ቅን ልቦና የማጣት አመለካከት ከዚህ የሚጀምር ይመስለኛል፡፡ ዝርዝሩን ጸሐፊው ‹‹መደምደሚያዬና የግል አስተያየቴ›› ባሉት የአስተያየታቸው ክፍል ላይ አንድ ባንድ ለማንሳት እሞክራለኹ፡፡ በእኔ አረዳድና እምነት የጸሐፊው ዓላማ በዚህ ክፍል የተጻፈው ድምዳሜና አስተያየት ይመስለኛል፡፡ ለዚህም እንዲረዳኝ ከጸሐፊው አስተያየት አግባብነት ያለውን መልእክት እየወሰድኩኝ የኔን አስተያየትና የጽሑፉን አንድምታ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

1ኛ/ ‹‹… ዶ/ር ዓቢይ ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያቀረቡት ጥሪ በመጀመርያ ደረጃ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከወሰደ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ካገር ወጥተው ሊመለሱ ያልቻሉትን ግለሰቦች በሰላም ወዳገራቸው እንዲመለሱ ከማሰብ እንጂ፣ የፖሊቲካ ድርጅት መሪዎችን ወይም አክቲቪስቶችን ወዳገር ቤት ተመልሰው ባገሪቷ የፖሊቲካ ሕይወት ንቁ ተካፋይ እንዲሆኑ ታስቦ አይመስለኝም። መሆንም የለበትም።››

ጠ/ሚሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ካደረጉት ንግግር ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ወያኔ ትግሬ በአሸባሪነት ፈርጆአቸው ለነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር ክሳቸውን በማንሳት ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ ዓላማቸውን እንዲያራምዱና በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ እገሌ ከእገሌ ሳይሉ ለኹሉም ግብዣ ማድረጋቸውን ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል፡፡ አቶ ባይሳ ከየት እንዳገኙት ባላውቅም ዶ/ር ዐቢይ በአደባባይ በግልጽ የተናገሩትንና ትርጕም የማያሻውን ንግግር በራሳቸው ፍላጎት ጥሪው የፖለቲካ ድርጅቶችንና አክቲቪስቶችን እንደማይመለከት፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ታስቦ አይመስለኝም፡፡ መሆንም የለበትም ብለዋል፡፡ ‹አይመስለኝም› ማለታቸው ርግጠኝነትን የማያመለክት በመሆኑ ባይናገሩት ይመረጥ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ መንግሥት ዳያስፖራው በሙሉ ዜግነቱን እንዳልቀየረ፤ ስለቀየሩትም መረጃ አለው፡፡ ይህ ሳይታወቅ ጥሪው አልተላለፈም፡፡ ጸሐፊው አይመስለኝም በሚለው ብቻ አላቆሙም ‹መሆን የለበትም› የሚለው ጠንከር ያለ አገላለጽ በስም ባይጠቅሷቸውም የማይፈልጓቸውና አገር ውስጥ በመግባታቸው እንደ ሥጋት የሚያዩዋቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳሉ የሚያሳብቅባቸው ነው፡፡ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አባላት እና አክቲቪስቶች ያሏቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለሌላቸው ነው ወይስ በአመለካከታቸው ስለሚጠሏቸው? ወይስ ዳያስፖራው አሁን በኢትዮጵያ ለሚታየው የለውጥ ጅማሮ ምንም አስተዋጽዖ የለውም ከሚል እሳቤ ስለመሆኑ ምክንያቱን ለባለቤቱ እተወዋለሁ፡፡ ባንፃሩም የጠ/ሚሩን ጥሪ ዳያስፖራው በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና በሙያው ብቻ እንዲሳተፍ የተጋበዘ አድርገው ማስቀመጣቸው አሁንም የተሳሳተ አረዳድ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም ዶ/ር ዐቢይ ዳያስፖራውን ለገንዘቡ ብቻ ነው የፈለጉት ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ እንዳይወስደን እሠጋለሁ፡፡

2ኛ/ ‹‹ከዳር ሆኜ ካየሁትና ካስተዋልኩት ተነስቼ በርግጠኝነት የሚከተለውን ለማለት እችላለሁ›› በሚል ንዑስ ርእስ ሥር ያነሷቸውን ነጥቦች ላይ ያለኝን አስተያት ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

2.1/ ‹‹ አገራችን ኢትዮጵያ የፖሊቲከኞች ወይም የፖሊቲካ ድርጅቶች እጥረት የለባትም። እንዲያውም ከሚያስፈልጋት በላይ ስለሆነ በጣም መቀነስ አለባቸው። ››

ይህ አባባል ትክክልም ስህተትም ነው፡፡ ትክክልነቱ ብዙዎቹ ወያኔ በቀደደላቸው የመንደርተኝነት ስልቻ ውስጥ ገብተው በጎሣ የተሰባሰቡ፤ የርእዮተ ዓለም÷ፍልስምና እና የሃሳብ መሠረት ስለሌላቸው የፖለቲካ ድርጅት የሚለውን ስያሜ የማያሟሉ የመንደር ማኅበሮች በመሆናቸው ቊጥራቸው በዝቷል፡፡ ለዚህም ተጠያቂዎቹ ወያኔ ትግሬ እና የሱን ፈለግ የተከተሉት ጎሠኞች ናቸው፡፡ ከ80 በላይ ለሆኑ ጎሣዎች 80 ‹ፓርቲ› ብቻ ሳይሆን ለአንድ የኦሮሞ ነገድ 20/30፣ ለአንድ የአማራ ነገድ 20/30፣ ለሌሎቹም የቊጥር ልዩነት እንጂ ቢያንስ ካንድ በላይ አላቸው፡፡ ይሄ ነው የአሁኑ የኢትዮጵያ የድንቁርና ‹ፖለቲካ›፡፡ አቶ ባይሳ በራሱ ማሰብ ያቆመውን ተራ ካድሬ ኹላ ‹ፖለቲከኛ› ካሉን እና ፖለቲካን በዕውቀትና ጥበብ ላይ የተመሠረተ የአገርና ሕዝብ አስተዳደር አድርገን የማናየውና ማንም እንደ አህያ ጆሮ የሚጎትተው  ጉዳይ ከሆነ ብዙ ‹ፖለቲከኞች› አሉን፡፡ ይህንን በግልባጩ ስናየው ግን የአበባላቸው ስህተትነት ገዝፎ ይታየናል፡፡ ባለፉት 27 የወያኔ አገዛዝ ዘመን በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትነት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ/የቆሙለትን ዓላማ በነፃነት ማራመድ የማይቻል እንደነበር ለጸሐፊው መንገር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቹ የ‹ፖለቲካ ድርጅቶች› ከስም ውጭ ምንም ፋይዳ ያልነበራቸውና በአመዛኙ ወያኔ ጠፍጥፎ የሠራቸው ‹ታማኝ ተቃዋሚዎች› መሆናቸው ይታወቃል፡፡

2.2/ ‹‹ ቄሮና ፋኖ እንዲሁም ሌሎች ለውጥ ፈላጊ ወገኖቻችን ያላንዳች የውጪ ቀጥተኛ ድጋፍ ራሳቸውን አደራጅተው፣ የአግዓዚን ገዳይ ጦር የተጋፈጡና፣ ለለውጡ መሳካት ከመታሰርና ከመሰቃየት አልፎ ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል። ስለዚህ እነዚህ የለውጥ ጀግኖችና ለውጡም ያፈሯቸው መሪዎቻቸው ይህንን ውድ ዋጋ ከፍለው ያገኙትን ድል ለመንከባከብና ከታለመለትም ግብ ለማድረስ የሚያቅታቸው አይመስለኝም። ስለዚህም የዳያስፖራው ሚና እጅግ በጣም ውስን መሆኑ መታወቅ አለበት። ››

በአገራችን የመጣው ለውጥ የሕዝባዊ ዓመፃና ትግል ውጤት መሆኑና ብዙ መሥዋዕትነትም እንደተከፈለበት፤ በዚህም ውስጥ በተለያየ ስም የተሰባሰቡ የኢትዮጵያ ወጣቶች (ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ ወዘተ) ትልቅ አስተዋጽዖ እንደነበራቸው አገር የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ላለፉት 50 ዓመታት በላይ የተበላሸውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዚህም የተፈጠረውን ግዙፍ አገራዊ ምስቅልቅል ባልተደራጁ ወጣቶች ዕውቀትና ልምድ ብቻ እናስተካክለዋለን ማለት እውነታውን አለመረዳት ነው፡፡ ምድር ላይ ያለውን እውነታ ከሕዝባችን ጋር በግፉም፣ በበደሉም፣ በእስሩም ውስጥ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ካገራችን ሳንወጣ ቁምስቀላችንን ያየነው ኹሉ በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ለውጡን ወደተፈለገው ግብ ለማድረስ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይባል ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ላገር መረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተን በጋራ ጥረት የምንደርስበት እንጂ ለእገሌ ተብሎ የሚተው አለመሆኑን (ክትትሎ ከውጭ ቢሆንም) በሚገባ የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ቁም ነገር ኢትዮጵያ ‹ያ› በሚባለው ትውልድ እና በወያኔያዊ ቅኝት ሲመራ የነበረውን የጥላቻና የመጠላለፍ ፖለቲካ ምዕራፍ ዘግታ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመጀመር በመንደርደር ላይ እንደመሆኗ ከእንግዲህ ወዲህ ማረጋገጥ የምንፈልገው ዘር/ነገድ/ጎሣ÷ሃይማኖት÷ፆታ፣ ወዘተ መሠረት ሳናደርግ ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ዜግነቱ እንደ ግለሰብ መብቶቹና ነፃነቶቹ ተከብረውለት፤ እንደ ማኅበረሰብ ታሪካችን÷ባህላችን÷ቋንቋችን ተከብሮ፤ በሕግ የበላይነትና ማኅበራዊ ፍትሕ ላይ የተመሠረተ መንግሥተ ሕዝብ በማቆም ለሁላችን እኩል የምትሆን አገርን መገንባት እንጂ  እኔ የበለጠ ደምቼአለሁ÷ቆስያለሁ ወይም ከሌላው የላቀ መሥዋዕትነት ስለከፈልኩ ለዘላለም የመግዛት መብት አለኝ የሚለው አስተሳሰብ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር አይሠራም፡፡ የወያኔ ትግሬ ይበቃናል፡፡ ጊዜው የኔ ነው በሚል በተረኛ ጨቋኝነት መንፈስ መጓዝ የምንፈልግ ካለን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትም ሆነ ይህ ጅምር ለውጥ እንደሚጣ ውድ ሕይወታቸውን የሠዉትን ወገኖቻችንን ሞት ማቅለል ብቻ ሳይሆን ዓላማውም አልገባንም፡፡ ወያኔንም የምናወግዘው በከንቱ ነው፡፡ ተረፈ-ወያኔነት ወይም ከወያኔ ትግሬ ብሶ መገኘት ነው፡፡ የለውጡ መሪዎች የእነ አቶ ለማ መገርሳ ቡድን ሃሳብም ሆነ ተግባር የሚያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ ባገር ቤት እየታዘብን እንዳለው ወጣቶችን ተጠቅሞ በስሜት ነድቶ ከጀርባቸው ሆኖ ፖለቲካን ወደፈለጉት አቅጣጫ ለመዘወር የሚፈልጉ ኃይሎች በውስጥም በውጭም መኖራቸውን ብናውቅም አብዛኛው ወጣት ለዚህ ዓይነቱ የጥፋት ተልኮ እንደማይንበረከክ እምነቴ የፀና ነው፡፡ ተጋግዘንና ተደጋግፈንም እንኳ ፈተናችን ጥልቅና ከባድ ነው፡፡ እገሌ ያገባዋል÷እገሌ አያገባውም ዐርፎ ይቀመጥ ለማለት መብቱን ማን ሰጠን? ወያኔ ትግሬ የለያየንና የከፋፈለን አይበቃም ወይ?

2.3/ ‹‹ …በኔ ግምት፣ ለሩብ ምዕተ ዓመት ልዩነቱን አቻችሎ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ባንድ ላይ የተሰለፈውን፣ ሕዝብ ዛሬ ከውጪ ተመልሰን ያልቸገራቸውን እንደቸገራቸው በማቅረብ “ክልሎች ይጥፉ፣ ፌዴራሊዝም ይወገድ፣ ይኸኛው ሐውልት ይፍረስ ይኸኛው ይገንባ፣ አንድ ቋንቋ አንድ ሕዝብ” ወዘተ እያልን ሕዝቡን ባንከፋፍል ጥሩ ይመስለኛል። ለወደፊት ኑሮውን የሚኖሩት እነሱ ናቸውና እናት አገራቸውን እንዳመቻቸው እንዲገነቧት ይህንን የሥራ ድርሻ የትግሉ ባላቤት ለሆነው ለወጣቱ ትውልድ እንተወው ማለቴ ነው። ››

እንደሚታወቀው አብዛኛው በጎሣ የተደራጁ ቡድኖች ወያኔ ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል ህልውናዋን ለማጥፋት፤ ሕዝቧም ምንም ዓይነት ታሪካዊ÷ ባህላዊ÷ ሃይማኖታዊ÷ ትውፊታዊ÷ ምጣኔ ሀብታዊ ÷ ሥነልቦናዊ ወዘተ መስተጋብሮች ኖረውት በፍልሰቱ÷ በንግዱ÷ በጋብቻው ወዘተ እንዳልተዛመደና በግድ አንድ መልክዐ ምድር ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱ ‹የባዕዳን ሕዝቦች› በወያኔ ትርጕም አልባ የማጭበርበሪያ ቋንቋ ‹ብሔር÷ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› ጥርቅም አድርጎ የዘረጋውን አፓርታይዳዊ የጎሣ ፖለቲካና የውሸት ፌዴራላዊ ሥርዓት (የጎሣ ፌዴራላዊነት)፤ ይህንኑም መሠረት አድርጎ ሥልጣንን ለማደላደል በዚህም የሚገኘውን ቅጥ ያጣ ዝርፊያ ለማስቀጠል በደቡብ አፍሪቃው የባንቱስታን ግዛት አምሳል ያዋቀረውን መርዘኛ ‹ክልል› የሚባል የአትድረሱብኝ አጥር፤ ለዚህም ‹ሕጋዊ› መደላድል የፈጠረውን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› የሚቀበሉ ሲሆን፤ ከወያኔ ጋር የሚለያቸው ወያኔ ትግሬ እወክለዋለሁ ብሎ የተነሳው ጥቂቶችን በመሆኑ ሥልጣኑ አይገባውም ከሚል በቀር ጉልህ ልዩነት የሌላቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ አቶ ባይሳ እርስዎ ለኢትዮጵያ እንግዳ ኖት እንዴ? በሁሉም ማዕዘናት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ልጆቻቸውን ሳይቀር በአረመኔው ወያኔ ያስበሉት÷ ለመናገርና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ግፍና በደል የተቀበሉት፣ ባገራቸውም ሆነ በዓለም ፊት የመጨረሻውን ተዋርዶ የተዋረዱት እኮ እርሶ በተራ ቋንቋ ‹ያልቸገራቸውን› ብለው የገለጹት ነገር ግን በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ትልቁ ማኅበራዊ ካፒታላችን የሆነውን – ባህላዊና ሃይማኖታዊ መሠረት ያለውንና በዘመናት ሂደት ተከባብረን ተስማምተን ለኅብረታችንና አንድነታችን ዋልታና ማገር የሆነውን  – ግብረ ገብነት በእጅጉ ሸርሽሮ የሞራል ልሽቀት ያደረሰብን ወይም ማኅበራዊ ድቀት ያስከተለብንን ቆሻሻ አገዛዝና የዚህም መገለጫዎቹን ነው፡፡ ኧረ ዕድሜ ለማስተዋል ነው፡፡ ኧረ ያስተዛዝባል፡፡ ኧረ ዘላቂውን በጊዜያዊ፣ ቋሚውን በኃላፊ ጠፊው አንቀይር፡፡ ያልሰከነው÷መሠረት ጉልላቱ ድንቁርናና አግላይነት የሆነው የዘር ፖለቲካ የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደማያዋጣንና ማለፉም እንደማይቀር ልቦናችን ያውቀዋል፡፡ የሥልጣኔ ቁንጮ የሆነ ዓለም ውስጥ እየኖራችሁ ተወልጄበታለሁ የምትሉትን አገርና ሕዝብ የሥልጣኔ ትሩፋቶች ተቋዳሽ እንዳይሆን በራሳችሁ ትውልድ ሳያበቃ አሁንም ወደኋላ ቀርነት ትጎትቱታላችሁ? እናንተ የመጥፎ አስተሳሰብ ባሪያ ሆናችሁ ወገናችሁን እንዴት አድርጋችሁ ነፃ ታወጡታላችሁ? የጥላቻ÷ የመለያየት÷ የቂም በቀል÷የስግብግብነት÷የእኔ ቡድን/ጎሣ የሚል ጠባብነት ሐውልት/ግድግዳ ይፍረስ፤ የፍቅር÷ የመተባበር÷ የኅብረት÷ የአንድነት/የአብሮነትን ድልድይ እንገንባ እየተባለ አይደለም እንዴ? የለውጡ አመራር ወንድሞቻችንስ ይኸው አይደለም እንዴ የለት ተዕለት መዝሙራቸው? የእነ ኦቦ በቀለ ገርባና ዶ/ር መራራ ስለ ነፃነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት እንዴት አድርገን እንረሳለን? ወንድሞቻችን እነ እስክንድርና አንዱዓለም በግፍ የታሠሩትና የተሰቃዩት ወያኔ በ‹ሕገ አራዊቱ› የተከለውን አሽክላ ለመንቀል አይደለም እንዴ? እነዚህ ወንድሞቻችን በራሳቸው አንደበት ደጋግመው እንደገለጡት ወያኔና ሲያራምድ ከቆየው አሁንም ተረፈ-ወያኔዎች እያራመዱ ከሚገኙት ከመንደርተኝነት/ጎሣዊ አስተሳሰብ ጋር ኅብረት የላቸውም፡፡ እኔ ይህን አስተያየት የምሰጠው እንደ አንድ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያንገበግበው፤ የወያኔ ትግሬን የግፍ አገዛዝ በሚችለው ኹሉ ሲታገል የቆየ፤ አሁንም በመታገል ላይ የሚገኝ፤ ወያኔ ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረው ቢሮክራሲ ጋር አልተባበርም ብሎ ራሱን ከሥራ አግልሎ በዚህም የደረሰበትን በደልና የወያኔ ካድሬዎችን ወከባ ኹሉ ችሎ እንዳለ፤ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አባል ያልሆነ፤ የሥልጣን ፖለቲካ ዝንባሌ እስከነአካቴው የሌለው አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡

አቶ ባይሳ፤ የመከፋፈል መርዝ የሚረጨው (ከውጭ ወደአገር ቤት ከገቡትም ሆነ በአገር ቤት በይስሙላ ተቃዋሚነት ካሉ) ማን እንደሆነ እርሶም ሆነ እዚህ ኢትዮጵያ የምንኖር ወገኖችዎ በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ የመርዙ ምንጭና ቀማሚ ወያኔ ትግሬ ሲሆን፣ ‹በብልቃጥ› ያደላቸውን በሕዝብ ውስጥ እየረጩ ያሉት ደግሞ የወያኔን አገርና ሕዝብ አጥፊ ፈለግ እየተከተሉ ያሉት ተረፈ-ወያኔዎች÷ የፖለቲካ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች÷ሆድ አደሮችና የድል አጥቢያ አርበኞች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያውያን ገጸ ድሮች የተጻፉ በርካታ ቁምነገር አዘል ጽሑፎችን እንዳነበቡ እገምታለሁ፡፡

2.4/ ‹‹ብዙዎቻን የዳያስፖራ አባላት፣ አገር ቤት ካሉት ወገኖቻችን የተሻለ ዕውቀት ወይም ልምድ ያለን ይመስለናል። የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የተወለደ ልጅ ዛሬ ፒኤች ድግሪ እንዳለው እንኳ ለማሰብም አንሞክርም። የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትም ወድቋል ተብሎ ስለታመነበት አገሪቷ ከኛ በኋላ ምሁር ያፈራችም አይመስለንም። ይህም የተሳሳተ ግምት ነው። ኢትዮጵያ ብዙ የተማረና የተመራመረ ዜጋ አላት። ያገሪቷ ዋና እጥረት የተሳሳተው የመንግሥት ፖሊቲካ ያስከተለው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመኖር ነው። እሱን ደግሞ ራሱ ሕዝቡ በሂደት እያስተካከለው ነው። ስለዚህ በማህበራዊው ሚዲያ ላይ ብቅ እያልን ራሳችንን ስላስተዋወቅንና የተሻለ እንግሊዝኛ በማውራታችን ብቻ ከነዚህ አገር በቀል የፖሊቲካ መሪዎችና ምሁራን የተሻልን ነን ብለን ራሳችንን መሸንገሉን ብናቆም የተሻለ ይመስለኛል።››

ማን የተሻለ ዕውቀትና ልምድ አለው የሚለው ጉዳይ ውስጥ ዳኝነት አልገባም፡፡ ራሱን ችሎ በበቂ መረጃና ማስረጃ መደገፍ ስለሚገባው፡፡ ይሁን እንጂ አነስተኛ የትምህርት ዝግጅትና ከ20 ዓመት ያላነሰ የሥራ ልምድ እንዳለው ዜጋ የማውቀውን እንድናገር ከፈቀዱልኝ እነሆ፡፡ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በተቀላቀልኩበት የደርግ የመጨረሻዎቹ ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት በእጅጉ እየወደቀ ያለበት፣ የናንተ ትውልድና ደርግ በሚከተለው ግራ የተጋባ ርእዮተ ዓለም የትምህርት ሥርዓቱ የተቃኘበት ጊዜ ቢሆንም፣ አንዳንድ ከምሥራቁ ዓለም ከመጡ ‹የተማሩ ካድሬዎች› ጋር ‹ጦርነት› ቀረሽ ሙግት ብናሳልፍም፣ በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩና ሠፋ ያለ አገራዊ ምልከታና አስተሳሰብ ያላቸው በጎ መምህራንንም ለማግኘት ችለናል፡፡

የደናቁርቱ የወያኔ አገዛዝ ከማይታማበት አያሌ አገርና ሕዝብ አውዳሚ ተግባሮች አንዱ ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲው፤ ከዕውቀት ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑ፤ የተማረንና የተለየ አማራጭ ሃሳብ ያለውን አጥብቆ የሚጠላ፤ ማሰብን የመንጋ ተግባር ያደረገ፤ እጅግ በሚያሳዝንና በሚቆጭ መልኩ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ‹መምህራን› (በተለይም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች) ከተማሪዎቻቸው ጋር በየመሸታ ቤቱ ካቲካላ የሚጠጡበት÷ ጫት የሚቅሙበት÷ ሐሺሽ የሚያጤሱበት÷ መምህራንና ተማሪዎች የሚባልጉበት ወዘተ በማድረግ እንኳን ዕውቀትን ከሥነ ምግባር÷አገር መውደድን ሕዝብን በቅንነት ከማገልገል የተሟላ ስብእና ያላው ዜጋ ማፍራት ቀርቶ በአመዛኙ አቋራጭ መንገድ ፈላጊ፣ ስግብግብ፣ ሌባ፣ ነውርን እንደ ክብር የሚያይ ወዘተ ትውልድ እንደ እንጉዳይ የሚፈሉባቸው ማዕከላት ሆነዋል፡፡ ነጮቹ “garbage in, garbage out” እንደሚሉት በርካታ ወገኖቻችንን ከዕውቀትና ከሥነ ምግባር ‹ጨዋ› አድርገዋቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከባቄላ ንፍሮ ውስጥ ገንትረው እንደሚወጡት ፍሬዎች፣ ከእንክርዳዱ ወያኔ (በሽፋን ስሙ ‹ኢሕአዴግ›) አገዛዝ ውስጥ መልካም ዘር ሆነው እንደተገኙት እነ አቶ ለማ÷ ዐቢይና ገዱ፣ ከተበላሸው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ በግል ጥረታቸውና ትጋታቸው፣ በወላጆቻቸውና ጓደኞቻቸው እገዛ ነጥረው የወጡ ወጣቶችን አይተናል፡፡ ግን እጅግ ጥቂት በመሆናቸው አጠቃላዩን ሥዕል ወካይ አይደሉም፡፡ ልዩ ሁኔታውን (the exception) ከአጠቃላዩ ደንቡ (the rule) ጋር ማምታታት የለብንም፡፡ ወደድንም ጠላንም ምድር ላይ ያለውን መራር እውነታ መካድ የለብንም፡፡ ለአገር ዕድገትና ልማት መሠረት የሆነው ትምህርትና ዕውቀት በአሸዋ ላይ ሲመሠረትና ለፕሮፓጋንዳና አጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ፍጆታ ሲውል አገርና ሕዝብን በዘለቄታው መግደል መሆኑ ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡ በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ጥላቻ ስላለን ወይም የማይታረቅ ቅራኔ አለን ብለን ስላመን ወይም በውጭው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እጅግ ዘቅጦ ወርዶ በእምነት ጉዳይ ጭምር በጎሣ ሲቧደን በማየታችን ብቻ ኹሉንም ባንድ ሳጥን ውስጥ አስገብቶ መፈረጅና አገር ውስጥ ስላለው ፖለቲካና ማኅበረ ምጣኔያዊ ሁኔታዎች በቂ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ሳይኖሩ ንጽጽር ማድረግ ሚዛናዊ አይመስለኝም፡፡

በሌላ በኩል ይህ አስተያየት አቅራቢ በኃላፊነት ይሠራበት በነበረ የመንግሥት መ/ቤት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የወጡ ‹ተመራቂዎችን› ለመቅጠር የቃልና የጽሑፍ ፈተና ባደረግንባቸው አጋጣሚዎች ኹሉ አብዛኛው አመልካቾች ወያኔ ትግሬ ከሚሰጣቸው ‹የወጣት ፎረም› አባልነት ከማቅረብ በዘለለ በሚያሳዝንና በሚያስደነግጥ መልኩ የተሠማሩበትን የትምህርት መስክ መሠረታውያን የማያውቁ በርካቶች አጋጥመውናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ 3ኛ ድግሪ ‹ማስረጃ› አቅርበውና ስሙን ተሸክመው ባግባቡ ማመልከቻ የማይጽፉትንም ታዝበናል፡፡ በየመ/ቤቱ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ በሙያዊ ጉዳዮች ‹የጥናት ወረቀቶችን› ባቀረብኩባቸው መድረኮች፣ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በነበሩኝ ተሳትፎ እና በከፍተኛ ት/ት ተቋማት ከሚያስተምሩ ጓደኞቼና ተንዝቤአለሁ፡፡ ወያኔ በትምህርቱም ዘርፍ ልጆቻችን ተግተው ዕውቀትን እንዲገበዩ ከማድረግ ይልቅ ሥርቆትን ‹ባህል› እንዲያደርጉ አስተምሯቸዋል፡፡ የትምህርት ማስረጃዎችን ያለብቃት ከሚያድሉ ተቋማት (diploma mills) መግዛት ዛሬ ነውር አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የውስጥ አእምሮ ፍልሰት (internal braindrain – ቢሮክራሲውን ጨምሮ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ተቋማት ብዙዎች ያለ ብቃት ተሰግስገውበታል) ከውጩ በላቀ የአገራችን ፈተና ሆኗል፡፡  

በመጨረሻም ጸሐፊው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገቡትንና ኢትዮጵያዊ ዜግነት የላችሁም ያሏቸውን ወገኖቻቸውን በጅምላው ‹‹በሰው አገር ፖለቲካ ውስጥ ገብታችሁ አትፈትፍቱ›› ሲሉ ‹መክረዋል›፡፡ ፖለቲካው ቀርቶ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የትውልድ አገራቸው አይደለችም እንዴ? ባገሪቱ ሥራ ላይ ባለው ሕግ መሠረት ኢትዮጵያዊ ዜግነትን አግኙ ማለት የአባት ነው፡፡ የበለጠ ቅንነቱ ካለ ደግሞ በበርካታ የዓለም አገራት ሕጎች እንደተከበረው የጣምራ ዜግነት መብት ሕጋዊ እንዲሆን ድጋፍ ሰጥቶ እርስዎም ሆኑ ሌሎች ወገኖቻችን የመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢያንስ መመኘት፤ ካለፈም አቅም የፈቀደውን ማድረግ ደግሞ የእናት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ኹሉ የቅን ልቦና ጉድለት (bad faith) ወይም ምቀኝነት ከሚባል ውጭ ለጊዜው ሌላ ትርጕም አላገኘሁለትም፡፡

Filed in: Amharic