>

እ ን ቁ ጣ ጣ ሽ  እ ን ኳ ን  መ ጣ ሽ !!!  (አሰፋ ሀይሉ)

እ ን ቁ ጣ ጣ ሽ፡ እ ን ኳ ን፡ መ ጣ ሽ ! ! ! 
አሰፋ ሀይሉ
የነፃነት አየር ሰውን ብቻ ሣይሆን – ዛፍ ቅጠሉን – አሮጊት ኮረዳውን – አዛውንት ኮበሌውን – ሁሉንም ሲያወዛውዝ ታያለህ፡፡ ሁሉም ይነፍሳል፡
ምን ልበልህ? በቃ – የአዲስ ዓመት ሽታ – በየሄድክበት – መንፈስህን በደስታ መንፈስ ያውደዋል፡፡ በረገጥክበት ሥፍራ ሁሉ በክረምቱ ዝናብ ምችት ያላቸው ያጎጠጎጡ የአበባ ከንፈሮችን በየመንገዱ ግራና ቀኝ በተለያዩ ቀለማት ፀዳል እያበሩ እይታህ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሣርና የፀደይ አበባ ዝምድናቸውን አድሰው በየመስኩ ሲፈነድቁ ታያቸዋለህ፡፡ የቡሄው ችቦ አመድ ገና ከደጃፋችን ወለል ላይ አሻራው አለ፡፡ እንቁጣጣሽ እየተጠጋ ነው፡፡
ያች ቀንህን ብልጭ ድርግም ልታደርግ ብቅ-ጥልቅ የምትል መለሎ የነሃሴ ዝናብ እንኳ ራሷን በአፍቅሮተ-ፀሐይ ልታላቅቅ አልቻለችም፡፡ ክረምት ቢገባም – ዝናብ – ከአፍቅሮተ ፀሐይ ራሷን ማላቀቅ አቅቷታል፡፡ የጸሐይና የዝናቡ ጋብቻ – ወርቃማ እይታን ይወልድልሃል – ጅብ ትወልዳለች – ህፃናት በጩኸት ግርር ብለው ይሯሯጣሉ – ሠማይና ምድር ሸብ-ረብ ብላለች፡፡  ታቦታት በብዙ ነጭ ነጠላ – ነጭ ጥበብ – ነጭ ጋቢ በለበሱ – በብዙ ምዕመናን ተጥለቅልቀዋል፡፡ ቤተመቅደሶች ቅዳሴያቸውን – መስጊዶች አዛናቸውን – ሙዚቃ ቤቶች ዘፈናቸውን – ጎረምሶች ሣቃቸውን – ህጻናት ጩኸታቸውን – ሁሉም – ጮክ አድርገው ላላፊ አግዳሚው ያሰማሉ፡፡ ኢትዮጵያ እርጥብ ህይወትን – ትኩስ ትንፋሽን – ደግማ ደጋግማ የወለደች ይመስልሃል፡፡
የነፃነት አየር ሰውን ብቻ ሣይሆን – ዛፍ ቅጠሉን – አሮጊት ኮረዳውን – አዛውንት ኮበሌውን – ሁሉንም ሲያወዛውዝ ታያለህ፡፡ ሁሉም ይነፍሳል፡፡ ይወዛወዛል፡፡ ያነባል፡፡ ያነበንባል፡፡ እና በትንሽ በትንሹ – ሁሉም በቃ – እብድ ይላል – ሽው – እልም – ክንፍ ይላል፡፡ የነሃሴ ብርድ ራሷ – ገላን ኩምትር፣ ሽምቅቅ፣ ስትር የማድረግ ኃይሏን ሁሉ አጥታለች፡፡ የትኩስ ገንፎና የለጋ ቅቤ ሽታ አካባቢውን ሞልቶታል፡፡ በዚህ ላይ – የበርበሬም ሽታ ጨምሮ ከሸተተህ ነገር አለ፡፡ ትኩሱን – ለብርድ – ባፍ ባፍህ ማለት ነው እሱን፡፡
ለወትሮው ወላድ የማይጠፋው – በኛ ሰፈር ነው፡፡ ሰው ሁሉ ይወልዳል – ይዋለዳል – አበባው – አረሙ – የተዘራው ሁሉ ይበቅላል፡፡ ሀገሩ ሁሉ ሲበዛ – ሲሰፋ – ታላቅ የፍጥረታት ሆታ ሀገር ምድሩን ሁሉ ሲያቀልጠው ይታወቅሃል፡፡ ምድሩ ሁሉ – አረንጓዴ ለብሷል፡፡ ሰዉ ሁሉ እንድ ቢጫ የፀደይ አበባ ፈክቷል፡፡ አረንጓዴ – ቢጫ – ቀይ – ባንዲራ – ሀገር ምድሩን ሁሉ – ፎቁን ጎጆውን ሁሉ አጥለቅልቆታል፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝባዊ መነቃነቅ ላይ ነች፡፡ አዲስ አበባ ታላቅ ድግስ ልትደግስ ሽር ጉድ ሆኗል ሥራዋ፡፡ ሁሉም ይገባበዛል፡፡ ይዘባበታል፡፡ በነፃነት ይተራረባል፡፡ ያሽካካል በነፃነት፡፡ እና – በነፃነት – ይሳደባል፡፡ ‹‹እነሱ!›› እያለ፡፡ ‹‹እነሱ!›› ብቻ ናቸው መሠለኝ – ከዚህ ሁሉ ፌሽታ የተገለሉት፡፡ ወይም ራሳቸውን ያገለሉት፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል ግን – በቃ አንተ ‹‹ነቄ›› ከሆንክ – ከሆንክ ግን – ማድረግ ያለብህን አንድ ቀላል ነገር – ማወቅ አለብህ፡፡ ያው ሰሞኑን  – ‹‹መደመር!›› – የሚባል ነገር መጥቶ የለ?!! እና በቃ፡፡ አንተ ማለት ‹‹ኢሱ›› ነህ!!! ምን ይጎትትሃል?!! በቃ – ተነስና ተደመር፡፡ የምን መደበር ነው? ‹‹እነሱ››ህን አቁም – እና ባንዲራ ያለበት ቲሸርት – ወይ ኬፕ – ወይ ሻርፕ – ወይ በቃ የሆነ ነገርህን ያዝና – ውጣ!!! ባንዲራ ባትይዝም – በቃ – በልብህ አለ – እሱን ይዘኸው ውጣ!! ‹‹እየተሰናኘ ዳሌና ዳንኪራ፣ እየተሰናኘ ዘፈን ከጭፈራ፤ ምን ትጠብቃለህ፣ ፋኖ ተሰማራ! ፋኖ ተሰማራ!›› ትለዋለህ ራስህን፡፡ እና ከለስላሳዋ ዝናብ ጋር ትደራደራለህ፡፡ እና ውሃ እንዳትጠጣበት፡፡ የገንፎ ማንኪያህን ጥለህ – ወደ ሆነ ቤት ጎራ በል!!! ዛሬ ላይ ነበር ያቆምኩት፡፡
ዛሬ ብዬ አልነበር ጨዋታዬን መንዛት የጀመርኩት (ጨዋታን እንደ ጉራ – መንዛት)? አዎ፡፡ አልዋሽህም፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ነው፡፡ ነገ እሁድ ነው፡፡ ‹‹ነው!›› የሚለው ቃል እንደናፈቀኝ አገኘሁት ሰሞኑን፡፡ ‹‹ነው›› እና ‹‹አይደለም›› ማለት መቻል እኮ ራሱ ተመስገን እኮ ነው፡፡ እውነት ሲነግስ ብቻ ነው እነዚህን ቃላት በሰው አፍ የምታገኛቸዋ፡፡ ሁላችንም እኮ ሳናውቀው – ‹‹ማለት ይቻላል!›› ‹‹አርጎ መውሰድ ይቻላል›› ‹‹ያለበት ሁኔታ!›› ‹‹መሰለኝ!›› ‹‹የሚታይ ይሆናል!›› በሚሉ ቃላት እኮ አልቀን ነበር፡፡ አሁን ‹‹ተመስገን›› እንበለው እንጂ ፈጣሪን፡፡ ትንፍስ አልን፡፡ ይሄ ሰውዬ ይቀፈኛል! ማለትም እኮ አንድ ነገር ነው፡፡ እፎይ የሚያሰኝህ፡፡ እንደህፃናቱ ፍንደቅ እርፍ የሚያደርግህ፡፡
ህፃናቱ እኮ በደስታ የሚቦርቁት – ሆዳቸው የሚያስቀሩት ነገር ስለሌላቸው ነው፡፡ የተሰማቸውን ያወጡታል፡፡ አሁን ስቀው – አሁኑኑ ያለቅሳሉ፡፡ አሁን ተራግመው – አሁን ይቦርቃሉ፡፡ በቃ ሰሞኑን – የነጻነት አየር በመዲናይቱ ሲነግስ – በትንሽ በትንሹ – ሰዉ ሁሉ – በቃ – እንደ ህጻናቱ የሆነ ይመስላል፡፡ ሁሉም – ዕድሜው እየታደሰ ነው፡፡ በወጣትነት ስሜት እየወረዛ ነው፡፡ በዚህ ክረምት – በታክሲ ውስጥ ስትገባ – የሞቀ የሰዉ ትንፋሽ ይጠብቅሃል፡፡ ሰዉ ሁሉ ሞቆታል – እንደህጻናቱ – እንደእኔ እንደራሴ – እንደሁላችን – ሙቀት – ሙቀት – ብርድ – ብርድ – ሙቀት – ሙቀት…. – አንድ ላይ – በቃ – መደመር!!! ሃሃሃሃሃ!!!
ሠፈሬ የህጻናት ጩኸት በዝቷል፡፡ እነሱ ደሞ ያበዙታል – ቆይ አሁን እንዲህ ደስስስ የሚያሰኛቸው ነገር ምን ተገኘ?!! ሲያስቀኑ! አትቅና፡፡ አንተም ተነስና ተቀላቀል፡፡ ሕዝቡን፡፡ እነታማኝን ሊቀበል – አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ለብሶ ከወጣው ህዝብ ጋር ተቀላቀል፡፡ በቃ መደመር ማለት እኮ ሌላ ተዓምር የለውም፡፡ ዘለህ – ዘራፍ ብለህ – ግርግር ውስጥ ድብልቅ ማለት፡፡ እና አብረህ ከወገንህ ጋር – ‹‹ሀገሬ ኢትዮጵያ – ተራራሽ አየሩ – ፏፏቴሽ ይወርዳል – ከየሸንተረሩ – ልምላሜሽ ማማሩ – እንዲህ – እንዲያ – እልልልልልልልልልል…..!!!!›› ማለት ነው – እንጂ!!
አምላክ እምዬ ኢትዮጵያ ሀገራችንን፣ ትውልዳችንን፣ ምድር ሠማያችንን፣ እንስሳት ቡቃያችንን፣ ገበታ ጎተራችንን – ኪሳችንን – ጉርሻችንን – ሳቃችንን – ትውልዳችንን – ወተቱን ማሩን ዝናቡን አደይ አበባውን ሣሩን ቅጠሉን እልልታውን ሁሉ አብዝቶ አብዝቶ አብዝቶ አባዝቶ ይባርክልን፡፡  
ኢትዮጵያዬ ኑሪልኝ እንዲህ ለዘለዓለም ፈንድቀሽ!!!
መልካም በአል፡፡
Filed in: Amharic