>

በግ ልገዛ ነዉ !!! (አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ)

በግ ልገዛ ነዉ !!!
አንዱአለም ቦኪቶ ገዳ
ወይኔ አንድሽ?! እንዴት በግ መግዛት ያቅተኛል?! 17 አመት ሙሉ ከምማር 17 አመት ብታገል ኖሮ ዛሬ ባለፎቅ ባለአክሲዮን ታይላንድ ና ዱባይ ተዝናኚ እሆን ነበር! ዛሬ እንደቀዮ አይነት በግ እጎትት ነበረ፡፡ 
”አንተ አንዲ ተነስ በግ ሳይወደድ ቶሎ ዉጣና ግዛ” አለችኝ ባለቤቴ፡፡ አልጋዬ ላይ ተጋድሜ መጽሀፍ ቅዱስ እያነበብኩ ነበር፡፡ ግን ምን ማለቷ ነዉ በግ ሳይወደድ ግዛና ና ስትል ?! በጊዜ ወደ ኋላ የሚመልስ ታይም ማሽን ቢኖረኝ ወደ ደርግ ሰአት ሄጄ በጌን ገዝቼ ተመልሼ እመጣ ነበር  (እርካሽ በግ ፍለጋ ስንከወከዉ አብዮት ጠባቂዎች ቢደፉኝስ ግን?! ሆ ሆ (ኢሃዲግ ስታይል)
”በግ ኦልሬዲ ተወዶ የለ እንዴ ሳይወደድ ግዛ የምትይኝ ምኑን ነዉ?!” አልኳት፡፡
”ገብቶሃል ባክህ ሳይብስበት ማለቴ ነዉ እንግዲህ በአዉዳ አመት ጭቅጭቅ አትጀምረኝ!” አለችኝ፡፡
”ግን ቆይ ሌላ ነገር መብላት አንችልም?!” አልኩኝ
”በአዲስ አመት መለወጫ በግ አንግዛ ነዉ የምትል?!” አፈጠጠች፡፡ ”ታዉቆሃል ግን?!  በግ ከበላን እኮ ቆይተናል! ለስሙ መጽሃፍ ቅዱስ እያነበብክ ነዉ መጻፉስ ምንድነዉ የሚለዉ?! ”በምድር ላይ ያለ የሚንቀሳቀስ ፍጥረት ሁሉ ምግብ እንዲሆናችሁ ፈቀድኩ” ነዉ የሚለዉ፡፡ አንተ ግን ካላማይንቀሳቀሰዉ የባቄላ ሽሮ ዉጭ የተፈቀደልህ አይመስለኝም፡፡ እንደዉ ቃሉን እንኳን አታከብርም?!” አለችኝ፡፡
”ታዲያ እዛዉ ገጽ ላይ እኮ ”ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፡ የባህር አሶችን የሰማይ ወፎችን በምድር የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዟቸዉ” ነዉ ያለዉ ዝም ብላችሁ በነጻ ብሏቸዉ አላለም!” አልኩኝ፡፡
”ግዟቸዉ ያለዉ አስተዳድሯቸዉ ማለቱ እንጂ ሸምቷቸዉ ማለቱ ነዉ እንዴ? አላበዛኸዉም?!” አለችኝ፡፡ ሚስቴን በታሪክ እንጂ በመጽሃፍ ቅዱስ ዙሪያ መሸወድ አይታሰብም፡፡ ወደ መጽኃፌ አቀረቀርኩ፡፡
”ሌላ ቀን ዞር ብለህ ካላየኸዉ መጽሃፍ ጋር ዛሬ ምን ያጣብቅሃል?! በል ተነስና ዉጣ?!” አለችኝ፡፡
”ቆይ ግን የኔ ፍቅር ጎረቤቶቻችንን እንኳን ለምን አታይም?! ቅድም አንድ ቦዘኔን መንገድ ላይ አግኝቼዉ እንደነገረኝ አሳየና ሚስቱ እንኳን በግ ሊያርዱ ይቅርና በጥዋት ተነስተዉ  ”ለእንቁጣጣሽ ምሳ ባለሁለት እግር ይሁን ባለ አንድ እግር?!” እየተባባሉ ሲጨቃጨቁ ሰማኋቸዉ አለኝ እኮ !” አልኳት
”ባለሁለት እግርስ ዶሮ ነዉ ባለአንድ እግር ደግሞ ምንድነዉ ስለዉ ካሮት አይለኝ መሰለሽ?!” አልኳት የራሴ ወሬ በጣም ያሳቀኝ ይመስል እየተንከተከትኩ፡፡
በነገራችን ላይ ሚስቴ አሳየን በቀደም አንዷለም ታሰረ ብሎ ስላስደነገጣት ጠምዳዋለች፡፡ እኔ ግን ከሱ መጻፍ በላይ ያስገረመኝ የሷ ድንጋጤ ነዉ ፡፡የአሳየን ፖስት ያነበበችዉ ማታ አልጋችን ላይ ተኝተን ሞባይላችንን ስንጎረጉር ነበር፡፡ አጠገቧ ሆኜ ታሰረ ሲባል እንዴት ትደነግጣለች?! አሁን እኔ እንደዚህ የምረሳ ሰዉ ነኝ?! ሞባይሏን መጎርጎር ከመጀመራ በፊት ያደረግነዉ ነገርስ እንዲህ በአፍታ የሚረሳ ነዉ?! በዛ ላይ ከጎኔ ተኝታ የእኔ የባሏ ጽሁፍ እያለላት የአሳየን እና የአሌክስ አብርሃን ጽሁፍ እያነበቡ መንከትከትስ ከማመንዘር በምን ተለይቶ ይታያል…….?!
”ይሄ መናጢ እንኳን ካሮት ደቼም ቢበላ ደስታዬ ነዉ!” አለችና ፈገግ አለች፡፡\
 ለምን እንደሆነ ባላዉቅም በኛ ማግኘት ሳይሆን በጎረቤቶቻችን ማጣት ደስ አላት፡፡ እኔም ዘዴዬ ሰርቷል ብዬ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ግና ደስታዬን ላፍታ እንኳ ሳላጣጥም ወዲያዉ ፊቷን አኮሳተረችና
”ለማንኛዉም ሰዉ እንደ ቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም እነ አሳዬ መናጢ የሆኑ እንደሆነ እኛም እንደነሱ መሆን የለብንም ተነስና ፍሪዳ ይዘህ ና !” አለች
”ፍዳ ይዘህ ና ነዉ ያልሽኝ?!” አልኳት ያልሰማሁ አስመስዬ፡፡ ኢትዮጲያ ዉስጥ የበዛዉና በቀላሉ የሚገኘዉ  ፍዳ ነዉ እንጂ ፍሪዳ አይደለም፡፡
ክፉኛ ገላመጠችኝና በአንድ ቃል ”ሰምተሃል !” አለችኝ ፡፡
ዉይ ይህቺ አባባል ስታስጠላኝ፡፡ አሁንማ ፋሽን ሆናለች፡፡አሁን ኢትዮጲያ ዉስጥ ጊዜ አጥሮን ነዉ የተናገርነዉን ላለመድገም ”ሰምተሃል!” የምንባባለዉ?! ምነዉ ኢቲቪ ጥዋት አንድ ሰአት ዜና አሰምቶ ሲያበቃ በየሰአቱ ወሸቱን ከሚደጋግምብን ጋዜጠኛዉ ከሁለት ሰአት  ዜና በኋላ ”ሰምቷችኋል!” ብሎ ቢተወን፡፡ ለምሳሌ ሶስት ሰአት ላይ ጋዜጠኛዉ ” ……..ጤና ይስጥልኝ የሰአቱን ዜና እናሰማለን ከዜናዎቹ ጋር ተመስገን በየነ ነኝ ካለ በኋላ” ሰምታችኋል!” ብሎ ቢሄድ…. ኢቲቪዬን ስወደዉ…..አረ እዚህ ሃርድ ላይ ነኝ ወደ ጉዳዬ ልመለስ…..
”ግን የኔ  ፍቅር ለአያያዙም ለአሰራሩም ለሁሉም ነገር እንዲመች አነስ ያለች ግልገል ይዤ ልምጣ ይሆን?!” አልኩኝ በማስተዛዘን ድምጽ
”አይሆንም ሙክት ይዘህ ና!” አለችኝ በአጭር ትዛዝ፡፡ የእናት የአባቴ አምላክ ሙክከ ያድርግሽ  አልኩ በልቤ
ልጄን ትምህርት በቤት አስመዝግቤ አዲስ ልብስ ገዝቼ የቤት ኪራይ ከፍዬ ምንም ብር አልተረፈኝም፡፡ ከቀዮ ለመበደር አስቤ ነበር፡፡ የቀዮ ገንዘብ ግን አንዳንዴ ሳስበዉ አኬል ዳማ (የደም መሬት )ይሆንብኛል፡፡ በእርግጥ ሲጋብዘኝ መጋበዜ አልቀረም፡፡ ግን ይሄንን ከደሃዉ ህዝብ ጉሮሮ ላይ በሙስና ነጥቆ ያመጣዉን ገንዘብ ፡የደሃዉን ላብና ወዝ ቀፎ ያመጣዉን የሰዉ ሃቅ ወስጄ ከልጆቼ ንጹኅ ሆድ ለመክተት አልፈልግም፡፡ ለምን እንደሆነ እኔ እንጃ፡ አምላኬ ሆይ እንኳንስ የህሊና ድሃ አላደረከኝ።
 በግ ላለመግዛት የመጨረሻ ሙከራዬን አደረኩ
 ለምን ግን በአሉን ሆድ በመሙላት ብቻ ከማሳለፍ የተለመደ ሽሮአችንን በልተን የታሰሩትን በመጠየቅ የታመሙትን በመጎብኘት በሰፈራችን ያሉትን 40 አመት ሎተሪ የሸጡ አዛዉንት አቶ በርታን  ቤታችን ጠርተን ምሳ በመጋበዝ ምናምን አናሳልፍም?!” አልኳት፡፡ ልቧን ለማራራት የመጨረሻ ቻንሴን(እድሌን) ልሞክር ብዬ….
 እስከ ዛሬ ስንት ቀን መቄዶንያ የአረጋዉያን መርጃ ማእከልን እንኳን እንጎብኝ ስልህ የአዉሮፓዋ ሜቄዶንያ እንሂድ ያልኩህ ይመስል ስትታሽ ከርመህ ዛሬ ደርሰህ በአዉዳአመት የታመሙ ጠያቂ እንሁን የምትለኝ?!” አለች
ሃሳቧን የማስቀየር ምንም ተስፋ የለኝም፡፡ ከቤቴ ወጣሁ . ገና ቤቴ በር ላይ እንዳለሁ ቀዮን በበራችን ላይ ሲያልፍ አየሁት፡፡ እየጎተተ ያለዉን በግ ትልቅነት ቤቢ አይቶ
 ”ምንድነዉ አባዬ?!” አለኝ
”በግዚላ ነዉ?!” አልኩት፡፡ ”ጎድዚላ ” የሚለዉን የዳይኖሰር ፊልም ከቤቢ ጋር አብረን ነዉ ያየነዉ፡፡
”ለእኛም እንደዚህ አይነት በግዚላ ግዛ እሺ አባዬ?!” አለኝ ቤቢ፡፡ ጭራሽ?! አልኩኝ በሆዴ፡፡ ቤቢ አንድ ነገር ይገዛልኝ ካለ አለ ነዉ፡፡
”አይ ቤቢሹ እኛ የምንገዛዉ በግ ነዉ፡ በግዚላ የሙሰኞች እንሰሳ ነዉ ምንም አይሰራልንም!” አልኩት፡፡
ግልገል በግም በተገዛ ! እያልኩኝ ነዉ በሆዴ፡፡
”ስንት ገዛኸዉ ቀዮ?!” አልኩት በቅናት እና በኩርፊያ ስሜት፡፡
 ነገረኝ፡፡
ወርሃዊ ደሞዜ ላይ 1000 ብር ያስጨምራል፡፡
”ወይ ወያኔ አ….ረ ኑሮ ተወደደ የት አንግባ እሺ?!” አልኩኝ ሳላዉቅ ጮክ ብዬ፡፡
”ደግሞ ይሄንንም በወያኔ ልታሳብብ ነዉ እንዴ?! በጉን እኮ ሜቴክ አላመረተዉም፤  የገዛ ወገንህ ነዉ የጨከነብህ ! እኛ ዋጋ ጨምር አላልነዉ! እንቁላሉንም ቢሆን መስፍን ኢንጂነሪንግ አይደለም የሚያመርተዉ፡ ማማረር ካለብህ ከመሃልህ የሚገኘዉን ስግብግብ ነጋዴ ነዉ ማማረር ያለብህ ፡ሁሉም መንግስትን ያማርራል ቖይ እኛ ምን እናድርግ?!” አለና በጉን እየጎተተ እየሳቀ ሄደ ፡፡
ወይኔ አንድሽ?! እንዴት በግ መግዛት ያቅተኛል?! 17 አመት ሙሉ ከምማር 17 አመት ብታገል ኖሮ ዛሬ ባለፎቅ ባለአክሲዮን ታይላንድ ና ዱባይ ተዝናኚ እሆን ነበር! ዛሬ እንደቀዮ አይነት በግ እጎትት ነበረ፡፡ ምነዉ እናቴ በልጅነቴ ት/ቤት ወስዳ ከምትዶለኝ በረሃ ወስዳ  በጣለችኝ ኖሮ! ይሄኔ  ዛሬ የእሷም ሆነ የቅርብ ዘመዶቿ ሕይወት ተለዉጦ ነበር?! ትምህርቱንም(ማስተርሱን) ቢሆን በግዢስ አገኘዉ አልነበር…. ኤዲያ
ቤቢሹ ”አባዬ በግ ቶሎ ግዛ” ብሎ በሚያሳዝን አይን ይለምነኛል፡፡ ያቺ ነዝናዛ ከዉስጥ ”እሰከ አሁን አልሄድክም እንዴ?!” ትላለች፡፡
”ጌታሆይ በግን ለምን ፈጠርክ?!” ብዬ በታላቅ ድምጽ ወደ ሰማይ ጮህኩ፡፡
ወዲያዉ ዞር ስል አንድ ነጭ በግ በአትክልት ዉስጥ ቆሞ አየሁ፡፡አሰብኩ፡፡ አብርሃም ልጁን ይስሃቅን ለአምላኩ ሊሰዋለት ሲል እግዚያብሄር ”አብርሃም ሆይ እምነትህ ምን ድረስ እንደሆነ አይቼዋለሁ ልጅህን ተዉና ይሄንን በግ ሰዋልኝ!” ብሎ በመላኩ በኩል በግ የላከለትን ጥዋት ያነበብኩት የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡
ተአምር ይሆን እንዴ?! ብዬ በጉን በፈገግታ እያየሁ እያለ የጎረቤታችን ሰራተኛ ”ምነዉ ጋሽ አንዷለም በጉ አትከልት ሲያበላሽ ዝም ብለዉ ያዩታል?! የጋራ ግቢያችንም አይደል?! ምነዉ እቴ?!” ብላ ነጩን በግ ወገቡን በፍልጥ ዠልጣ ከአትክልቱ ዉስጥ አስወጣችዉ ፡፡ ከምኞቴ ባንኜ ወደ እዉነተኛዉ ኑሮዬ ተመለስኩ፡፡
ወይ በግ?! ግን ከሩቅ ለሚያያት የዋህ እንሰሳ ትመስላለቸ ሲገዟት ግን ዋ……ይ ….ጠላኋት፡፡ ለነገሩ አሁን አሁን በግ በቀላሉ የምትበላ እንስሳ መሆኗ አክትሟል፡፡ ልክ እንደ ኢሰመጉ(የኢትዮጲያ ሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ) አይነት ተቋም(አሁንም አለ ግን ይሄ ተቋም? ) ኢበመጉ (የኢትዮጲያ በጋዊ መብቶች ጉባኤ) የሚባል ተቋም ቢኖር የሚከተለዉን መግለጫ የግንቦት ሃያ በአልን አስታኮ ለኢቲቪ የሚልክ ይመስለኛል
 ከኢ.በ.መጉ የተሰጠ መግለጫ
 ”እኛ የኢትዮጲያ በጎች  በሰዉ በላዉ የደርግ ስርአት ከሰዎች እኩል ስንጨፈጨፍ የቆየን መሆኑ ከማንም የተደበቀ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡በዛ አስከፊ ስርአት እናት ልጇ ከቤት ወጥቶ ይመለስ ይሆን ብላ በምትሳቀቅበት በዛ አረመኔ አገዛዝ እኛ በጎችም እንደዋዛ በደሃዉም በሃብታሙም የህበረተስብ ክፍል ስንጨፈጨፍ እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትዉስታ ነዉ፡፡
 የአዲስአበባ በጎች እንደአሁኑ ክብራቸዉን ሳይቀዳጁ በፊት በጋዊ ማንነታቸዉ ተረግጦ  በ50 እና በ60 ብር በአስተማሪዎችና በተራ የመንግስት ሰራተኞች ሁላ እየተገዙ በየበአላቱ በስንቱ ማድቤት የቢላዋ እራት ሆነዋል፡፡
የማያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ እንዲሉ ሆነና ጀግናዉ የኢሃዲግ ሰራዊት ባደረገዉ እልህ አስጨራሽ መራራ ትግል ዛሬ ያ አስከፊ የበጎች የመከራ ዘመን ላይመለስ ተቀብሯል፡፡ የማንም መናጢ ድሃ ማንም የመንግስት ሰራተኛ ከዚህ በፊት ያለምንም ዲዩ ፕሮሰስ ኦፍ ሎዉ የአንድን በግ ህይወት የሚቀጥፈበት ዘመን አክትሟል፡፡
ዛሬ በጎች ኢሃዲግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ቀስ በቀስ ባደረገዉ የኑሮ ዉደነትን የማባባስ ስራ የመጨረሻዉ የክብራችን ጣራ ላይ ልንደረስ በቅተናል፡፡ በቅርቡም ጫፋችን የማይነካበት ጊዜ ላይ እንደምንደርስ አንጠራጠርም፡፡ በጣም በቅርቡ አንድም በግ በቢላዋ ህይወቷን አታጣም የሚባልበት ዘመን ላይ ደርሰን በካራ ሳይሆን በእድሜ መግፋት ይህቺን ምድር በክብር የምንሰናበትበት ጊዜ ላይ እንደምንደርስ አንጠራጠርም፡፡
በእዉነቱ ከዚህ በላይ ምን እንፈልጋለን?! ሰብኣዊ መብቶች በማይከበሩባት ሀገር በጋዊ መብቶች ተከብረዉ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሰደስት ነገር አለ?! አንዲት በግ ልጇን በወግ በማረግ ድራ የልጅ ልጅ አይታ ከመሞት በላይ ምንስ ትሻለች?!” ስልጣን አታጋሩን፡፡
ፓርላማ እንግባ አንልም sometimes we feel that some of our own are already in
ጸሃዩ መንግስታችን ዉሎ ይግባልን፡፡
ሞት “የኑሮ ዉድነት ይቀንስ” ብለዉ ለሚጠይቁ ጸረ ሰላም ሃይሎች!
ድል ለሰፊዉ ህዝብ! ፍየሎች ይዉደሙ( እሰቲ አሁን ፍየሎች ምን አደረጓቸዉ ? )
በጉ ይገዛ ይሆን?!
ይመቻችሁ
Filed in: Amharic